ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በኢትዮጵያ ያጋጠሙ ግጭቶችን ባህሪ እና መንስኤን ያጠናው ብሔራዊ የግጭት ክስተት ልየታ ጥናት ከ2010 እስከ 2015 ዓ.ም. ድረስ ያሉት ዓመታት ከባድ ግጭቶች የተከሰቱባቸው ዓመታት ናቸው ብሏል።

ከትግራይ ክልል ውጭ ሁሉንም ክልሎች እና የከተማ አስተዳደሮች ያካተተው ጥናቱ የ22 ዓመታትን የግጭት ክስተቶች አጢኖ ያለፉት አምስት ዓመታት ላይ ማተኮሩን አጥኚው ዶ/ር ደሳለኝ አምሳሉ ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢትዮጵያ ጥናት ኢንስቲትዩት ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር ደሳለኝ፣ ባለፉት አምስት ዓመታት በአገሪቱ ውስጥ ግጭቶች በከፍተኛ ደረጃ ጨምረዋል ይላሉ።

የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ላይ ያተኮረው እና አንድ ዓመት ከመንፈቅ ገደማ የፈጀው ጥናት፤ በአምስት ዓመታት ውስጥ 5,300 የሚሆኑ ግጭቶች መከሰታቸውን ለይቷል። ይህም ከ1992 እስከ 2015 ዓ.ም. ድረስ ባሉት ዓመታት ካጋጠሙ ግጭቶች መካከል 58 በመቶዎቹ ባለፉት አምስት ዓመታት የተከሰቱ ናቸው ተብሏል።

እነዚህ በአምስት ዓመቱ ውስጥ በአገሪቱ ያጋጠሙት ግጭቶች ከፍተኛ ቁጥር ላላቸው ሰዎች ሕይወት መጥፋት እና ለከባድ የንብረት ውድመት ምክንያት ሆነው አሁንም እንደቀጠሉ ይገኛሉ።

ይህ አሃዝ ወደ አምስቱ ዓመታት ሲካፈል በየዓመቱ 1,060 ግጭቶች የተከሰቱ ሲሆን፣ ይህ ደግሞ ለወራት ሲከፋፈል በአምስቱ ዓመታት ውስጥ ባሉት 60 ወራት ውስጥ በየወሩ ከ80 በላይ ግጭቶች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ አጋጥመዋል።

ግጭቶች ለምን ጨመሩ?

ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በአገሪቱ ግጭት ያልተከሰተባቸው ክልሎች ባይኖሩም፤ የብሔር እና የሃይማኖት ብዝኃነት እንዲሁም ሀብት ባለባቸው አካባቢዎች ግጭቶች በተደጋጋሚ ተከስተዋል።

ይሁን እንጂ አጥኚው እንደሚሉት ከዚህ ባለፈ ከ2010 ዓ.ም. ወዲህ የግጭት መልኮች እየተቀየሩ ሰፋ ያሉ ግጭቶች በተደራጁ ኃይሎች መካከል እንደተፈጸሙ ገልጸዋል።

“…ከ2010 ዓ.ም. በኋላ የተከሰቱት ግጭቶች የፌደራል መንግሥት ከክልል የፀጥታ ኃይሎች ጋር ወይም በክልል ደረጃ ከታጠቁ ቡድኖች ጋር የሚዋጋባቸው፤ በደንብ የተደራጁ እና ሰፊ ግጭቶች ናቸው። ስለዚህ ግጭቶቹ በተወሰነ አካባቢ ላይ ያለ ሳይሆን፣ ብዙ አካባቢዎች ላይ ይሄ [ግጭት] አለ” በማለት የአገሪቱን የግጭት አውድ ዶ/ር ደሳለኝ ይገልጻሉ።

የግጭቶቹ ባህሪ በዋናነት ፖለቲካዊ ነው የሚሉት አጥኚው፤ የግጭቶቹ ቀስቃሽ ምክንያቶች በአጥኚው አጠራር ጫሪ የሆኑ “ሰበቦች” እንዳሉ አመልክተው፣ ስረ መሠረታቸው ግን ፖለቲካዊ ጥያቄዎች እና ፍላጎቶች ናቸው ይላሉ።

“[የግጭቶቹ ስረ መሠረት] የመንግሥት ሥርዓታችን፤ ፓወር [በትረ ሥልጣን] የተደራጀበት መንገድ እንዲሁም ሥልጣን የሚተገበርበት መንገድ ነው” በማለት የሕገ-መንግሥቱን ንድፍ፣ የፓርቲ ፖለቲካ እና ምጣኔ ሀብታዊ ምክንያቶችን ያነሳሉ።

ግጭቶቹ ለምን ባለፉት አምስት ዓመታት ጨመሩ? ለሚለው ጥያቄ ዶ/ር ደሳለኝ አምሳሉ፣ ልል የሆነ የፖለቲካ ሥርዓትን እና የመንግሥት መዋቅር እጅ መርዘምን ለአብነት ያነሳሉ።

“ሥርዓቱ የሰውን ጣልቃ መግባት ይፈልጋል፤ ኃይል ይፈልጋል። መንግሥት ልል ሲሆን ግጭት ይመነጫል። ሌላው በተደጋጋሚ የሚነሳው ሰላም ቢመጣ ለሁሉም አካል በተለይ ለመንግሥት አካላት እና ለልሂቃኑ እኩል ጠቃሚ ላይሆን ይችላል። ስለዚህ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ሆነው ሰላምን የሚያደፈርሱ፣ የሰላም አደናቃፊዎች የሚባሉት የእነሱ ሚና አንዱ ነው” ሲሉ ችግሩ ከ‘ፖለቲካ ስሪቱ’ ጋር የተያያዘ ነው ይላሉ።

2013/2014 ዓ.ም. የአገሪቱ እጅግ ደም አፋሳሽ ዓመታት ነበሩ። ይህም በአምስቱ ዓመታት ውስጥ ካጋጠሙ ግጭቶች ውስጥ የ35 በመቶ ድርሻ ያለው ሲሆን፤ ለዚህም የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ትልቁ እንደሆነ ተመራማሪው ተናግረዋል።

ከ2010 እስከ 2015 ዓ.ም. ባሉት አምስት ዓመታት ከተከሰቱ ግጭቶች ውስጥ ጦርነት ቁጥር አንደ ነው። ጥናቱ ከአምስቱ ዓመታት ግጭቶች ውስጥ ይህ ጦርነት 44 በመቶው ድርሻ አለው ብሏል።

ከጦርነት በመቀጠል ባለፉት አምስት ዓመታት በንጹሃን ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶች፣ ከተመዘገቡት ግጭቶች ውስጥ በሁለተኛ ደረጃ የተቀመጠ ሲሆን፣ ተቃውሞ ደግሞ በሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ከአገሪቱ ክልሎች ውስጥ ደግሞ የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ ግጭት የሚከሰትበት ቀዳሚው ስፍራ ሲሆን፣ በዋናነት በክልሉ በንጹሃን ላይ የሚደርስ ጥቃት እንደሚፈጸም ጥናቱ ለይቷል። አማራ እና ትግራይ ክልሎች ኦሮሚያን በመከተል በቅደም ተከተል ሁለተኛ እና ሦስተኛ የግጭት ቀጠናዎች ሆነዋል።

በጥናቱ በአገሪቱ የግጭት ተዋንያን ቁጥር መጨመሩ የተገለጸ ሲሆን፤ በዚህም ውስጥ ‘መንግሥታዊ ያልሆኑ’ 38 ቡድኖች ተሳትፎ አላቸው ተብሏል።

ግጭቶቹ የማኅበረሰቡ ወይስ ‘የልሂቃን’?

በግጭቶቹ ተሳፊነት መንግሥታዊ እና የብሔር መሠረት ያላቸው ታጣቂዎችን ጨምሮ ህወሓት እና መንግሥት ሸኔ የሚለው የኦሮሞ የነጻነት ሠራዊትን የመሳሰሉ በርካታ ኃይሎች ይገኙበታል። ከዚህ ጋር ተያይዞ በእርግጥ የግጭቶቹ ባለቤት ማን ነው የሚለው ግን ክርክር ያስነሳል።

የአገሪቱ ግጭቶች በልሂቃን መካከል እንጂ በማኅበረሰቡ ውስጥ አይደሉም የሚሉ ሰዎች የማኅበረሰቡን አብሮነት ለማሳያነት በማንሳት ይከራከራሉ። በሌላ ወገን ደግሞ ቀድሞውኑ በማኅበረሰቡ ውስጥ መከፋፈል አልያም መቃቃር ቢኖር እንጂ ሊሂቃኑ የግጭቶቹ ባለቤት አይደሉም የሚሉ አሉ።

ግጭቶቹ በእርግጥም የማኅበረሰቡ ወይስ የልሂቃኑ ናቸው? ለሚለው ጥያቄ ዶ/ር ደሳለኝ አምሳሉ፤ መጠኑ ይለያይ እንጂ “የሁለቱም ናቸው” በማለት መነጠል ከባድ እንደሆነ ይጠቁማሉ። የባለቤትን ጉዳይ ከሁለት አንዱን ከመምረጥ ይልቅ ቀዳሚው ባለቤት ማን ነው የሚለውን መመልከት የተሻለ ነውም ባይ ናቸው።

“የእኛ ችግሮች የሚመነጩት ከትልቁ ሥዕል [ከልሂቃኑ] ነው። የፖለቲካ አወቃቀሩ፣ የሥልጣን አጠቃቀሙ፣ የአገረ መንግሥት ግንባታው እና አያያዙ የመጀመሪያው ተጠያቂ [Responsive factor] ነው ብዬ አስባለሁ። ይሄ ማለት ግን ግጭቱ ከላይ ብቻ በልሂቃኑ ላይ ተንጠልጥሎ ያለ ነው ማለት አይደለም።

“ማኅበረሰቡ በራሱ ተጽዕኖ ያድርበታል። ስለዚህ ማኅበረሰቡ ግጭቱን የራሱ ያደርገዋል። ማኅበረሰቡ የግጭቱ ተዋናይ ይሆናል። አንዳንዴ ደግሞ ማኅበረሰቡ ለምሳሌ ወጣቱን ብንወስድ በጣም አክራሪ ይሆንና ከላይ ያለውን ጉዳይ [በልሂቃን ያለውን] ለመቀየር፤ ለማጠፍ አስቸጋሪ ይሆናል” ይላሉ።

ፖለቲካዊ ርዕዮተ ዓለሞች ምንጫቸው ከሊሂቃን ቢሆንም፣ ማኅበረሰቡ ዘንድ ከተተከሉ በኋላ ለመቀየር ፈቃድ እንደሚፈልግ በመጥቀስም ለማሳያነት የአገሪቱን ሕገ መንግሥት ማሻሻል ላይ ያለውን ውዝግብ ያነሳሉ።

“ሕገ መንግሥቱ ይሻሻል ቢባል፤፣ ልሂቃኑ ተስማሙ ብንል ሌላው ይስማማል ማለት ላይሆን ይችላል። አክራሪ የሆነ የተወሰነ አስተሳሰብን ተምረው፣ እንደ እውነት ተቀብሎ ያደገ ትውልድ ስላለ እሱ ሌላ ችግር ነው” ይላሉ።

ይህም በመሆኑ ሁኔታው ውስብስብ እንደሆነ የሚያነሱት ተመራማሪው፤ የግጭቶች ጅማሬ እና የባለቤትነት ተጽዕኖው ይገለባበጣል ብለዋል።

ሆኖም ግን መፍትሄ ለማምጣት ማኅበረሰቡን ማሳመን እና ለንግግር እንዲቀመጥ ማድረግ ቀላል ነው የሚሉ ሲሆን፤ ፈተናው ከላይ ያሉትን ልሂቃን ማስታረቅ እንደሆነ ጠቁመዋል።

በግጭቶች ውስጥ የመንግሥት ሚና

በኢትዮጵያ ውስጥ ባጋጠሙ እና እየተካሄዱ ባሉ ግጭቶች መንግሥታዊ ያልሆኑ በርካታ የታጠቁ ኃይሎች ተሳታፊ ቢሆኑም “የመንግሥት መዋቅር ግጭቶችን በመጠንሰስ እና በማበባስ አሉታዊ ሚና እንደሚጫወት” በጥናቱ ውስጥ ተመላክቷል።

የሰላም እና የደኅንነት የሥራ ኃላፊዎችን እና ባለሞያዎችን በመረጃ ምንጭነት የተጠቀመው ጥናቱ የመንግሥት አካላት ከፍርድ ውጪ በሚፈጸሙ ግድያዎች፣ በግዳጅ በማፈናቅል፣ በፆታዊ ጥቃቶች እና ሰብዓዊ እርዳታዎችን በማስተጓጎል ይሳተፋል ብሏል።

ተሳትፎው በግለሰብ ደረጃ የተወሰነ ሳይሆን በተደራጀ እና ስልታዊ በሆነ መንገድ እንዲሁም በከፍተኛ ሹማምንት ትዕዛዝ እንደሚፈጸም የጥናቱ ምንጮች ተናገረዋል።

ዶ/ር ደሳለኝ አምሳሉ “የሰላም አደናቃፊዎች” የሚሏቸው እነዚህ የመንግሥት መዋቅሮች፤ የፖለቲካ ፍላጎታቸውን ለማስፈጸም በግጭቶች ውስጥ በቀጥታ በመሳተፍ፣ በማባባስ እና ኃላፊነትን ባለመወጣት የራሳቸው ሚና አላቸው ብለዋል።

“የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች፣ ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች ጭምር ‘የሰላም አደናቃፊዎች’ እንዳሉ እና ይህም ግጭቶችን ለመቆጣጠር አስቸጋሪ ያደረገው አንዱ ገጽታ ነው። በየአካባቢው ሲኬድ ሕብረተሰቡ በሰፊው የሚያምነው ጉዳይ ‘የሰላም አደናቃፊዎችን’ ጉዳይ ነው። የምጣኔ ሀብት፣ የፖለቲካ እና ሌሎችም ፍላጎት ያላቸው የተለያዩ አደናቃፊዎች እንዳሉ እና [መንግሥት] ይሄን መቆጣጠር እንዳለበት የሚናገሩ አሉ” ይላሉ።

የመንግሥት መዋቅሮች ግጭቶች እንዲባባሱ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል የሚሉት ተመራማሪው፤ በ2010 ዓ.ም. የነበረው የፖለቲካ ሽግግር ትልቅ በር እንደከፈተ እና መንግሥት ግጭትን ለመቆጣጠር የሚወስደው እርምጃ ደካማ መሆኑ ለችግሩ መስፋፋት እንደ አንድ ምክንያት ጠቅሰዋል።

“. . . [ግጭቶች] እየተስፋፉ የሄዱት ምናልባትም ሕግ በማስከበር በኩል መንግሥት መወጣት ያለበትን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት ባለመቻሉ እንደሆነ ግልጽ ነው።”

ግጭቶቹ ስለ አገሪቱ ምን ይነግሩናል?

ኢትዮጵያ እያስተናገደቻቸው ያሉ ግጭቶች ግዙፍ ተጽዕኖ እያስከለተሉ ነው። የግጭቶቹ ባህሪ ውስብስብ በመሆኑ እና መፍትሄ ለማበጀት የሚወሰዱ እርምጃዎች ውስን እና ውጤትን እያስገኙ ባለመሆናቸው ችግሩ ከድጡ ወደ ማጡ እየሆነ ይመስላል።

አገሪቱ ሰላምን ለማምጣት እና ደኅንነትን ለማስፈት ትልቅ ፈተና እየገጠማት እንደሆነ ባለሞያዎች የግጭቶችን አዝማሚያና ስፋት በመጥቀስ ይናገራሉ።

በዶ/ር ደሳለኝ ጥናት በናሙናነት ከተወሰዱ የ22 ዓመታት ግጭቶች ውስጥ ያለፉት አምስት ዓመታት ግጭቶች በዓይነትም ሆነ በባህሪ የተለዩ ናቸው።

የፖለቲካ ሥርዓት ስሪቱ በእግሩ ያልቆመ መሆኑን በአገሪቱ እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች እንደሚያመላክቱ የሚጠቅሱት አጥኚው፤ ለዚህም የሕገ መንግሥቱን ተፈጻሚነት እና ጣልቃ ገብነትን በማሳያነት ያነሳሉ።

“ለ86ቱም ብሔሮች ክልል መስጠትን ሕገ መንግሥቱ ይፈቅዳል። ነገር ግን ይህን መፈጸም አይቻልም፤ ሊተገበር የሚችል አይደለም። ስለዚህ ላለመፈጸም ምን ያስፈልጋል? ጣልቃ ገብነት፣ ኃይል ያስፈልጋል። ‘አይ አይሆንም፤ ክልል አይሰጣችሁም’ እየተባለ ምክንያት ይደረደራል። ይህ ምክንያት ግን ሕገ መንግሥታዊ አይደለም።

“የፌደራል ሥርዓቱ ላይ ምናልባት ሕገ መንግሥቱ ላይ ሌሎችም ተቋማት ላይ የሚያስፈልጉ እርማቶች፣ የሚያስፈልጉ ማሻሻያዎች ሊኖሩ ይችላሉ። እና [ጥናቱ] እነዚህን ክፍተቶች አጉልቶ ያሳየ ነው” ብለዋል።

ግጭቶች በዚሁ የሚቀጥሉ ከሆነ. . .

2013/2014 ዓ.ም. ካለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ ደም የፈሰሰባቸው ዓመታት ተብለዋል። በእነዚህ ዓመታት ከባዱን የትግራይ ክልል ጦርነትን ሳይጨምር ሁለት ሺህ የሚደርሱ ግጭቶች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ አጋጥመዋል።

ምንም እንኳ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በሰላም ስምምነት እልባት ቢያገኝም፣ በወራት ልዩነት አገሪቱ ወደ ሌላ የትጥቅ ግጭት ውስጥ ገብታለች።

በአማራ ክልል ውስጥ በፋኖ ታጣቂዎች እና በመንግሥት ኃይሎች መካከል እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል ዓመታትን ያስቆጠረው በመንግሥት እና በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መካከል የሚካሄደው ግጭት ተባብሷል።

ዶ/ር ደሳለኝ አምሳሉ በአገሪቱ ያሉት ግጭቶች ዘላቂ መፍትሄ ሳይበጅላቸው በዚሁ የሚቀጥሉ ከሆነ የንጹሃንን እልቂት እንደሚያስከትሉ ስጋታቸውን ይናገራሉ።

“ግጭቶቹ ማኅበረሰባዊ እየሆኑ፣ በማኅበረሰቡ ዘንድ እተስፋፉ ብቻ ሳይሆን፣ ማኅበረሰቡ በራሱ ተዋጊ እየሆነ የሄደበት ሁኔታ ነው ያለው። ስለዚህ ይህ ከቁጥጥር ውጭ ሊሆን ይችላል። በኢትዮጵያ ግጭቶች ተለዋዋጭ ናቸው። እንዲህ ይሆናል ብሎ በትክክል መገመት ባይቻልም፤ የሚያሳስበን እና የከፋ ነገር ይመጣል ብለን የምንሰጋው የንጹሃን እልቂትን ነው።”

መፍትሄዎች

ከ340 ገጽ በላይ የሆነው እና የኢትዮጵያን የግጭት አዝማሚያን የለየው ጥናት፣ በአገሪቱ እየተስፋፋ ያሉትን ግጭቶች ለመቆጣጠር የተለያዩ መፍትሄዎችን በምክረ ሃሳብ ምዕራፉ ላይ አስቀምጧል።

ይህንን አሳሳቢ ችግር ለመፍታት አስቸኳይ የመፍትሄ እርምጃ በንግግር እና በምክክር መወሰድ አለበት የሚሉት አጥኚው ዶ/ር ደሳለኝ፤ ለዚህም “የሰው ደም እየፈሰሰ፤ ንብረት እየወደመ” የረጅም ዓመት የቤት ሥራዎችን መጠበቅ የለብንም የሚል ነጥብ ያነሳሉ።

ሆኖም በአገሪቱ ላሉት ግጭቶች መሠረታዊ የሆኑት ምክንያቶች መዋቅራዊ በመሆናቸው፣ መፍትሄዎቹም ይህንን ማገናዘብ አለባቸው ይላሉ።

የሕገ መንግሥት ማሻሻያ፣ የግል እና የቡድን መብት ሚዛንን ማስተካከል፣ የህዳጣን ሕዝቦች የተናጠል እና የጋርዮሽ ሥልጣን ማግኘት፣ የምርጫ ሥርዓትን ማሻሻል፣ ሕገ መንግሥታዊ ፍ/ቤት መመሥረት፣ የወሰን ውዝግቦችን መፍታት፣ በግጭቶች ውስጥ የመንግሥትን አሉታዊ ተሳትፎ መቆጣጠር፣ የጋራ የታሪክ አረዳድ መፍጠር፣ ምጣኔ ሀብታዊ ተጠቃሚነትን ማስፈን የመሰሉ መፍትሄዎች መወሰድ አለባቸው ብለዋል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ለሰላም ተብለው የተቋቋሙ ኮሚሽኖች ከስም አለማለፍን ጨምሮ በግጭቶች ውስጥ የመንግሥታዊ አካላት አሉታዊ ሚና፣ የግጭቶች አያያዝን እና የመንግሥት ቁርጠኝነትን በተመለከተ በርካታ ጥያቄዎች ይነሳሉ።

ነገር ግን ባለፉት ጥቂት ዓመታት ተቋቁሞ በአገሪቱ ያሉትን መሠረታዊ ችግሮች እና ያለመግባባት ምንጮችን በንግግር ለመፍታት ጥረት እያደረገ ያለው አገራዊ የምክክር መድረክ እንቅስቃሴ እያጋጠሙ ላሉት ችግሮች መፍትሄ ለማበጀት አንድ አማራጭ መሆኑን ያምናሉ።  ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *