ባለፉት ቀናት ኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን በአዲስ አበባ ሲያደርጉት የነበረው የሕዳሴ ግድብ የሦስትዮሽ ድርድር ያለ ስምምነት መጠናቀቁን ግብፅ እና ኢትዮጵያ አስታወቁ።

ሦስቱ አገራት በሕዳሴ ግድብ ውሃ አሞላል እንዲሁም ዓመታዊ ኦፕሬሽን የተመለከተ መመሪያ ላይ ድርድር ሲያደርጉ ቆይተዋል።

ይኹን እንጂ በአራት ዙር ሲካሄድ የቆየው “የመጨረሻ” ድርድር በአገራቱ መካከል ባሉ ልዩነቶች ስምምነት ላይ መድረስ አልተቻለም።

ለድርድሩ አለመሳካት ኢትዮጵያ እና ግብፅ አንዳቸው ሌላኛቸውን ተጠያቂ አድርገዋል።

የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በድርድሩ ወቅት ግብፅ የቅኝ ግዛት ዘመን አስተሳሰቧን በመያዟ ስምምነት እንዳይደረስ እክል ሆናለች ብሏል።

የግብፅ የውሃ ሃብት እና መስኖ ሚንስቴር በበኩሉ ኢትዮጵያ የሦስቱንም አገራት ጥቅም ሊያስጠብቅ እና ሊያስማማ የሚችል የሕግም ሆነ የቴክኒክ መፍትሄዎችን ለመቀበል ዝግጁ አይደለችም ብሏል።

አራተኛው ዙር የመጨረሻው ድርድርም በአዲስ አበባ ባለፉት ሦስት ቀናት ሲካሄድ የቆየ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር አስታውሶ በድርድሮቹ ላይ ኢትዮጵያ ከግብፅ እና ሱዳን ጋር በግድቡ ግንባታ፣ ውሃ አሞላል እና ኦፕሬሽን በተመለከተ ያሏትን መሠረታዊ ልዩነቶችን በድርድር ለመፍታት ጥረት አድርጋለች ብሏል።

ይኹን እንጂ የግድቡ የመጀመሪያ አሞላል እና ዓመታዊ ኦፕሬሽን የተመለከተ መመሪያ እና ደንቦች ላይ ሲደረግ የነበረው ድርድር ግብፅ የቅኝ ግዛት ዘመን አቋሟን በመያዟ ስምምነት እንዳይደረስ እክል ሆናለች ብሏል።

የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ኢትዮጵያ የአባይን ውሃ በፍትሃዊ እና ምክንያታዊ በሆነ መርህ ላይ በመመስረት የዜጎችን ፍላጎት ለማሟላት የምታደርገውን ጥረት እንደምትቀጥል ማሳወቅ ትፈልጋለች ብሏል።

ግብፅ በበኩሏ የግድቡን አሞላል እና ኦፕሬሽን በቅርበት በመከታተል መብቴን አስከብራለሁ ስትል ጠንከር ያለ መግለጫን አውጥታለች።

የግብፅ የውሃ ሃብት እና መስኖ ሚንስቴር ባወጣው መግለጫ በግድቡ ምክንያት “ግብፅ የትኛውም አይነት ጉዳት ቢደርስባት በዓለም አቀፍ ቻርተሮች እና ስምምነቶች መሠረት የውሃ ድርሻዋን እና ብሔራዊ ደኅንነቷን የመጠበቅ መብቷ የተጠበቀ ነው” ብሏል።

ኢትዮጵያ በበኩሏ ይህ ግብጽ ከድርድሩ መጠናቀቅ በኋላ ያወጣችው መግለጫ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ቻርተር እና የአፍሪካ ኅብረት ሕገ-መንግሥታዊ ድንጋጌን የሚጻረር ነው በማለት መግለጫውን እንደማትቀበለው አስታውቃለች።

ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ እየገነባች ያለችው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከግብጽ እና ከሱዳን ጋር ሲያነጋግራት ቆይቷል።

ኢትዮጵያ ሦስቱ አገራት በናይል ወንዝ ላይ ባላቸው የውሃ ድርሻ ላይ መስማማት ከቻሉ ከሕዳሴ ግድብ የሚለቀቀውን የውሃ መጠን በተመለከተ አሳሪ ስምምነት ላይ መድረስ እንደሚቻልም አቋሟን ስትገልጽ ቆይታለች።

ግብፅ በበኩሏ የግድቡ ግንባታ ከናይል ወንዝ የማገኘው የውሃ መጠን አቅርቦት ላይ አደጋ የጋረጠ እንዲሁም የታችኛውን ተፋሰስ አገራት ችላ ያለ ነው ስትልም ቅሬታዋን አቅርባለች።

በግድቡ የውሃ ሙሌት እና ከግድቡ በሚለቀቀው የውሃ መጠን ላይ ሕጋዊ እና አስገዳጅ ሦስትዮሽ ስምምነት ካልተፈረመ ኢትዮጵያ የውሃ ሙሌቱን ማከናወን እንደሌለባትም ግብጽ ስትወተውት መቆየቷ ይታወሳል።  ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *