የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የወይዘሮ ሜላትወርቅ ኃይሉን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢነት ሹመትን አጸደቀ።

ምክር ቤቱ ዛሬ ታህሳስ 9/ 2016 ዓ.ም እያካሄደ በሚገኘው ስብሰባው የወይዘሮ ሜላት ብሔራዊ ቦርድ ሰብሳቢነት ሹመትን በአንድ ድምጸ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ ነው ያጸደቀው።

ከምክር ቤት አባላቱ መካከል የአዲሷን የቦርድ ሰብሳቢ ሹመት የተቃወመ የፓርላማ አባል የለም።

የሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ምሩቋ ሜላትወርቅ ኃይሉ አምስተኛዋ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሆነው በምክር ቤቱ ቃለ መሃላ ፈጽመዋል።

በዚህ ስብሰባ ላይ ከቦርዱ ሰብሳቢ ሹመት በተጨማሪ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን እና የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚዎች ሹመት ጸድቋል።

ለቦርዱ ሰብሳቢነት ሁለት ዕጩዎች ከሁለት ሳምንት ገደማ በፊት ኅዳር 22/2016 ዓ.ም. ለጠቅላይ ሚኒስትሩ መቅረባቸው ይታወሳል።

በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 102 መሠረት የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢን ጨምሮ የቦርዱ አባላት የሚሾሙት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው።

በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅ መሠረት የቦርዱ ሰብሳቢ፤ ቦርዱን ከሦስተኛ ወገኖች ጋር ባለው ግነኙነት የመወከል ሥልጣን አላቸው። ከዚህ በተጨማሪም የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሥራ አመራርን ስብሰባ የመጥራት እና የመምራት ኃላፊነት ተሰጥቶታል።

ለቦርዱ ሰብሳቢ እንዲሆኑ በዕጩነት የቀረቡት ወይዘሮ ሜላትወርቅ ኃይሉ እና አቶ ታደሰ ለማ ናቸው። ሁለቱን ግለሰቦች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በመጨረሻ ዕጩነት ያቀረበው ራሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያዋቀሩት፤ የዕጩ መልማይ ኮሚቴ ነው።

ኮሚቴው ለአስር ቀናት ዕጩዎችን ሲቀበል የቆየ ሲሆን፣ በእነዚህ ቀናት የ56 ዕጩዎች ጥቆማዎች ቀርበውለት ከመካከላቸው አራቱ ብቻ ነበሩ ሴቶች።

የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀሐፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ የሚመሩት ዕጩ መልማይ ኮሚቴ በሦስት ዙሮች አምስት ዕጩዎችን ለይቶ ነበር። ስምንት አባላት ያሉት ኮሚቴው በመጨረሻ ሁለት ዕጩዎችን ለይቶ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅርቧል።

ለቦርዱ ሰብሳቢ ዕጩ ሆነው የቀረቡት ሁለቱም ግለሰቦች ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ኃላፊነት አዲስ አይደሉም። ሁለቱም ዕጩዎች ቦርዱን በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች አገልግለዋል።

ወይዘሮ ሜላትወርቅ ለሁለት ዓመታት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሥራ አስፈጻሚ ሆነው ሠርተዋል። አቶ ታደሰ በበኩላቸው የምርጫ ቦርድ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ናቸው።

ለቦርዱ አዲስ ሰብሳቢ የሚሾምለት ቦርዱን ለአራት ዓመት ከመንፈቅ የመሩት ብርቱካን ሚደቅሳ ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ ጤናቸውን “በሚገባ ለመጠበቅ የረጅም ጊዜ እረፍት” እንደሚያስፈልጋቸው በመግለጽ ከኃላፊነት በመልቀቃቸው ነው።

ብርቱካን ሚደቅሳ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሆነው በመሾም አራተኛው ግለሰብ ናቸወ። ዛሬ ሹመታቸው የጸደቀላቸው ተሿሚ አምስተኛዋ የቦርዱ ሰብሳቢ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥትን መጽደቅ ተከትሎ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የመጀመሪያ ሰብሳቢ ሆነው የተሾሙት አቶ ከማል በድሪ ናቸው። አቶ ከማል ቦርዱን ለአስራ አንድ ዓመታት አገልግለዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የነበሩት መርጋ በቃና በ1999 ዓ.ም. አቶ ከማል በድሪን ተክትው በቦርዱ ሰብሳቢነት ተሹመዋል።

ፕ/ር መርጋ ከአስር ዓመታት የቦርዱ ሰብሳቢነት በኋላ በ2009 ዓ.ም ሥልጣናቸውን ለመጀመሪያዋ የቦርዱ ሴት ሰብሳቢ ሳሚያ ዘካሪያ አስረክበዋል።

የሳሚያ ዘካሪያ የሥልጣን ዘመን ከአንድ ዓመት የዘለቀ አልነበረም። በ2011 ዓ.ም. የቀድሞዋ ፖለቲከኛ ብርቱካን ሚደቅሳ መንበሩን ከሳሚያ ዘካሪያ ተረክበዋል።

በአራት ዓመት ከመንፈቅ የብርቱካን ሚደቅሳ የሥልጣን ቆይታ ቦርዱ ምርጫ ቦርድ ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ እና በደቡብ ኢትዮጵያ ሦስት ሕዝበ ውሳኔዎችን አካሂዷል።  ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *