የትግራይ ክልል ባለሥልጣን በክልሉ የተከሰተው ድርቅ ከዚህ ቀደም ካጋጠመው ከ1977ቱ ድርቅ የከፋ ነው ሲሉ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ደግሞ ተጎጂዎችን ለመርዳት ግብረ ኃይል አቋቋመ።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የአደጋ መከላከያ እና ዝግጁነት ኮሚሽን ኮሚሽነር ገብረሕይወት ገ/እግዚአብሔር (ዶ/ር) ድርቁ በአምስት የትግራይ ክልል ዞኖች ተከስቷል ብለዋል።

ኮሚሽነሩ “በትግራይ የከፋው ድርቅ የተከሰተው በ1951 እና በ1977 ነበር። አሁን ያጋጠመን ከዚህም በላይ ነው። በዚህ ድርቅ ምክንያት 2 ሚሊዮን ሕዝብ ተርቧል። 400 የሚሆኑ ሰዎች ባለፈው ወር ብቻ (ኅዳር) ከ400 በላይ በረሃብ ምክንያት ሕይወታቸው አልፏል” ብለዋል።

ከድርቁ ጋር በተያያዘ ሕይወታቸው ማለፉ ከተነገው 400 ሰዎች መካከል 25ቱ ሕጻናት መሆናቸውን ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።

በክልሉ በተከሰተውን አስከፊ ድርቅ የተጎዱትን ለመርዳት የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ አንድ ግብረ ኃይል አቋቁመዋል።

የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት “ሰብዓዊነት የሚሰማው ሁሉ” የእርዳታ እጁን እንዲዘረጋ ጠይቀዋል።

ለሁለት ዓመታት በአስከፊ የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ የቆየው የትግራይ ክልል በዝናብ እጥረት በተከሰተ ድርቅ እና የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት መቋረጥ ምክንያት ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ ለምግብ ዋስትና ደኅንነት አደጋ ተጋላጭ ሆኖ ቆይቷል።

የክልሉ ባለሥልጣናት እንደሚሉት ከሆነ በአሁኑ ወቅት ከ2 ሚሊዮን የማያንሱ የክልሉ ነዋሪዎች ለረሃብ አደጋ ተጋልጠዋል።

“በአበርገለ የጭላ 83፣ በአጽቢ 66፣ በኢሮብ እና በጋንታ አፈሹም 77 እንዲሁም በአንዳባሻህ 208 ሕይወታቸው አልፏል” ሲሉ ለክልሉ ቴሌቪዥን ተናግረዋል።

ህወሓት እና የፌደራል መንግሥቱ ለሁለት ዓመታት የተካሄደውን ደም አፋሳሽ ጦርነት ያስቆመ የሰላም ስምምነት ፈርመው ጦርነት ቢቆምም ክልሉ በተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ ችግሮች ከገባበት ሰብዓዊ ቀውስ መውጣት አልቻለም።

በርካታ የክልሉ አርሶ አደሮችም ጦርነቱ ካበቃ ከአንድ ዓመት በኋላ በክልሉ በርካታ ቦታዎች ላይ ባጋጠመ ድርቅ እና የእርዳታ አቅርቦት መቋረጥ ምክንያት ሕይወታቸው አደጋ ላይ መውደቁን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በመላው አገሪቱ ለተረጂዎች የሚቀርብ የምግብ እርዳታ ላይ መጠነ ሰፊ ዝርፊያ ተፈጽሟል መባሉን ተከትሎ የዓለም ምግብ ፕሮግራም እና የአሜሪካ መንግሥት ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) የእርዳታ ሥራቸውን ለወራት አቋርጠው መቆየታቸው ይታወሳል።

የተራድኦ ድርጅቶቹ የእርዳታ አቅርቦት ባቋረጡበት ወቅት የእርዳታ ምግብ የተከማቸባቸው መጋዝኖች በክልሉ ውስጥ እያለ ነዋሪዎች ግን በረሃብ መሞታቸውን የትግራይ ክልል ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

የ1977ቱ ድርቅ በሰሜናዊ የአገሪቱ ክፍል ዜጎች ላይ እጅግ የከፋ ሰብዓዊ ቀውስ ከመፍጠሩም በላይ አሁንም ድረስ አገሪቱን የረሃብ መገለጫ አድርጎ በምዕራባውያን ዘንድ እንድትታወስ አድርጓል።

በወቅቱ ሥልጣን ላይ የነበረው መንግሥት በአገሪቱ የከፋ ረሃብ መኖሩን አምኖ ለመቀበል በተገደደበት ረሃብ 1 ሚሊዮን ሰዎች ሕይወታቸው አንዳለፈ ይነገራል።

ቢቢሲ የድርቁን ስፋት ለዓለም ያሳየ ዘገባ ካወጣ በኋላ ተጎጂዎችን ለመርዳታ ዓለም አቀፍ ርብርብ እንዲደረግ አስችሎ ነበር።   ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *