በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን እሁድ ኅዳር 30/2016 ዓ.ም. በተፈጸሙ ሁለት የድሮን ጥቃቶች በርካታ ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናገሩ።

በዞኑ መሀል ሳይንት ወረዳ ልዩ ስማቸው መሳለሚያ እና ቀይ ዋሻ በተባሉ አካባቢዎች ላይ በተፈጸሙት የድሮን ጥቃቶች የተገደሉ ሰዎችን በተመለከተ ትክክለኛ አሃዝን ለማወቅ ባይችልም የሟቾች ቁጥር 40 እንደሚደርስ ቢቢሲ ያነጋገራቸው አምስት የአካባቢዎቹ ነዋሪዎች ገልጸዋል።

ከወረዳው ዋና ከተማ ደንሳ በግምት 10 ኪ.ሜ ይርቃል በተባለው እና ልዩ ስሙ መሳለሚያ ወይም ወርቅ ማውጫ በተባለ ስፍራ በተሽከርካሪ “ለፋኖ ስንቅ እያቀረቡ ነበር የተባሉ ያልታጠቁ በርካታ ወጣቶች” መገደላቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል።

በጥቃቱ “ቢያንስ በትንሹ 30 የአካባቢው ወጣቶች” መገደላቸውን የምትናገረው ስሟን ለደኅንነቷ ሲባል እንዳይገለጽ የጠየቀች የአካባቢው ነዋሪ፤ የድሮን ጥቃቱ ‘ኤፍኤስአር’ በተባለ የጭነት ተሽከርካሪ እየተጓዙ እያለ ምሽት 12 ሰዓት ገደማ መፈጸሙን አመልክታለች።

“አብዛኞቹ [የተገደሉት] በአስራዎቹ እና በ20ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች ናቸው” ስትልም በድሮን ጥቃቱ ስለተገደሉት ወጣቶች ገልጻለች።

በአካባቢው ፋኖ ለአንድ ወር ገደማ መቆየቱን የሚናገሩት ሌላው ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የአካባቢው ነዋሪ ቅዳሜ እና እሁድ በቡድኑ እና በመከላከያ ሠራዊት መካከል “ከባድ ውጊያ” ነበር ብለዋል።

በአማራ ሳይንት እና መሀል ሳይንት መገንጠያ ላይ በለጩማ በተባለ አካባቢ ውጊያው መካሄዱን የተናገሩት ነዋሪው፤ ወጣቶች ለፋኖ እገዛ ለማቅረብ በሚል ሲንቀሳቀሱ እንደነበር ጠቁመዋል።

“ፋኖ ያኔ [ጥቃቱ በደረሰበት ቀን] ከተማ ውስጥ አልነበረም። መኪናው ውስጥ አብረው ሁለት ሦስት [የታጠቁ ሰዎች] አይተናል። ሌላው ግን መኪና ላይ የነበረው ሁሉም ያልታጠቀ ወጣት ነው” በማለት ስለ ጥቃቱ ሰለባዎች ተናግረዋል።

ጥቃቱ በተፈጸመበት ዕለት ሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) በከተማው እና በአጎራባች ቀበሌዎች አሰሳ እያደረገ ነበር የሚሉት ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች፤ ሰዎች ድሮንን ከአውሮፕላን ጋር በማመሳሰል “ቆመው እያዩ ነበር” ብለዋል።

“ከስምንት ሰዓት ጀምሮ ድምጿ መቅብ ጀመረ። ድምጿ ይሰማ ነበር። ‘ፎቶ እያነሳች ነው’ የሚልም ነበር፤ ፈርቶ ወደ ሱቆች የተጠለለም ነበር” ያሉት አንድ ነዋሪ፤ በጥቃቱ ከ30 እስከ 35 የሚደርሱ ሰዎች ሳይገደሉ አልቀረም ብለዋል።

አንድ በመንግሥት ሥራ ላይ የተሰማሩ የአካባቢው ነዋሪ ደግሞ የሟቾቹ ቁጥር 40 ይሆናል ያሉ ሲሆን፣ ሌላ ቢቢሲ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪ ደግሞ የሟቾች ቁጥር “ከ15 እስከ 20 ይደርሳል” ብለዋል።

ነገር ግን ቢቢሲ ካነጋገራቸው የሁለቱ አካባቢ ነዋሪዎች ግምት በመነሳት ባገኘው አሃዝ መሠረት በጥቃቱ የተገደሉት ሰዎች ብዛት ከ40 በላይ ሊሆን ይችላል።

ከተገደሉት ሰዎች በተጨማሪ ሦስት ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸው ለሕክምና ወደ ደንሳ መወሰዳቸውንም ነዋሪዎች ተናግረዋል።

በጥቃቱ የተገደሉ ሰዎች ቤተሰቦች የሰለባዎቹን አስከሬን ለመለየት ተቸግረው ነበር የሚሉት አንድ ነዋሪ “በመታወቂያቸው እና ኪሳቸው ውስጥ በተገኙ ወረቀቶች ለመለየት ተሞክሯል” ሲሉ የጥቃቱን ክብደት ተናግረዋል።

በጥቃቱ ሕይወታቸው የለፉ ሰዎች ቀብርም በተመሳሳይ ዕለት ዕሁድ ሌሊት ቤተሰቦች እና የአካባቢው የተወሰኑ ሰዎች በስጋት ውስጥ ሆነው መፈጸማቸውም ተገልጿል።

አንድ ነዋሪ “ድሮኗ እስከ ንጋት ነበረች፤ አልሄደችም። ይህ በፈጠረው ስጋት የተወሰኑተን ሌሊት ነው የቀበሯቸው። ከስድስት ሰዓት ጀምሮ ሲቀብሩ ነበር። ቤተ-ክርስቲያን ትመታለች በሚል ስጋት አፋፍሰው ነው በጥድፊያ የቀበሯቸው” ብለዋል።

በመሀል ሳይንት ወረዳ ቀይ ዋሻ በተባለ አካባቢም እሁድ ዕለት 11 ሰዓት አካባቢ የድሮን ጥቃት መድረሱን የተናገሩት ነዋሪዎች፤ በርካታ አርሶ አደሮች ሳይገደሉ አልቀረም ብለዋል።

የቀይ ዋሻ ነዋሪ እንደሆኑ የገለጹ አንድ የዐይን እማኝ የከባድ መሳሪያ ድምጽ ሰምተው ከቤታቸው የወጡ 20 አርሶ አደሮች በጥቃቱ ሳይገደሉ እንዳልቀሩ ተናግረዋል።

“አንድ 20 ገበሬዎች ሞተዋል። 30 የሚሆኑ ሰዎች ተጎድተዋል። ቁስለኞቹን ስናነሳቸው የሚተርፉ አይመስለኝም። [የተገደሉት] ታጣቂዎች አይደሉም፤ ታጣቂዎችማ አይገደሉም። ተኩስ ሲሰማ በግርግር የሸሹ ሰዎች ናቸው የሞቱት” ብለዋል።

በጥቃቱ ወቅት በቀይ ዋሻ አካባቢ እንዳልነበሩ የተናገሩ አንድ ነዋሪ ስምንት ሰዎች እንደተገደሉ እና አንድ ሰው እንደቆሰለ ሰምቻለሁ ብለዋል።

ከጥቃቱ ማግስት በወረዳው ምንም አይነት እንቅስቃሴ አልነበረም ያሉት ነዋሪዎች “ተዘግተው የማያውቁት ባንኮችም ተዘግተዋል፤ ትምህርት ቤቶችም ተዘግተዋል። መከላከያ ሲገባ በአካባቢው ምንም ነገር አላገኘም” ብለዋል።

ደንሳ በተባለችው የመሀል ሳይንት ወረዳ መቀመጫ መከላከያ ሰኞ ዕለት ከ10 ሰዓት በኋላ መግባቱን ተከትሎ መረጋጋት እንዳለ ነዋሪዎች ተናግረዋል።

በአማራ ክልል በፋኖ ታጣቂዎች እና በመከላከያ ሠራዊት መካከል ለወራት እየተካሄደ ባለው ግጭት ውስጥ በሚፈጸሙ የድሮን ጥቃቶች ምክንያት በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት እየደረሰ መሆኑን የመንግሥታቱ ድርጅት እና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን መግለጻቸው ይታወሳል።

እነዚህ የድሮን ጥቃቶች እያደረሱ ያሉትን ጉዳት በተመለከተ አስካሁን ከመንግሥት በኩል የተባለ ነገር ባይኖርም የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ለፋና ቴሌቪዥን ሠራዊታቸው ሰው አልባ አውሮፕላኖቹን እየተጠቀመባቸው መሆኑን አረጋግጠዋል።

“ድሮን የገዛነው ልንዋጋበት እንጂ፤ አለን እያልን በሚዲያ ለመግለጽ አይደለም” ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ ነገር ግን ሕዝብ በሚሰበሰብበት አካባቢ እና በመኖሪያ መንደር ጥቅም ላይ አይውልም ብለዋል።

“ከጽንፈኛ ጋር አትደባለቁ” ሲሉ ለሕዝብ ማሳሰቢያ የሰጡት ኢታማዦር ሹሙ፤ የድሮን ጥቃቶቹ እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል።

ወራት ያስቆጠረው በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለው ግጭት የተቀሰቀሰው መንግሥት የክልል ልዩ ኃይሎችን በማፍረስ መልሶ ለማደራጀት እና ሌሎች ታጣቂዎችን ትጥቅ ለማስፈታት መወሰኑን ተከትሎ ነበር።

የተለያዩ የአገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች ወደ ድርድር እንዲመጡ እና በውይይት ችግራቸውን እንዲፈቱ ጥሪ እያቀረቡ ቢሆንም፣ እስካሁን የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች ስለመኖራቸው የሚጠቁሙ መረጃዎች የሉም። ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *