አቶ ታዬ ደንደአ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከሥልጣናቸው የተሰናበቱት በአገሪቱ ያለው ጦርነት እንዲቆም ጥሪ በማቅረባቸው እንጂ ሌላ ምክንያት እንደሌለ ለቢቢሲ ተናገሩ።

የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ የነበሩት አቶ ታዬ ይህንን የገለጹት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተፈረመ ደብዳቤ ከሥልጣን መነሳታቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ እንደደረሳቸው ይፋ ካደረጉ በኋላ ነው።

“ስለእርቅ ስለተናገርኩ ጦርነት ይቁም ስላልኩ እንጂ ሌላ ምክንያት የለም” በማለት ለቢቢሲ የገለጹት አቶ ታዬ፣ “በጦርነቱ ጊዜ ጦርነቱን ስደግፍ፣ ሲያበረታቱኝ ነበር። ሕዝቡ ይታረቅ ስንል ነው ያመማቸው። ጠርተው አላናገሩኝም። በአካል አልተገናኘንም” ሲሉ ምክንያት ያሉትን ተናግረዋል።

አቶ ታዬ በተረጋተጠ የፌስቡክ ገጻቸው ላይ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የተጻፈላቸውን የስንበት ደብዳቤ አያይዘው እንዳሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩን አምነው እንደተከተሏቸው እና በቃላቸው አለመገኘታቸውን ጠንከር ያሉ ቃላትን አስፍረዋል።

ስንብታቸውን በተመለከተ በፌስቡክ ላይ ያሰፈሩትን ጠንካራ ትችት በተመለከተ የተጠየቁት አቶ ታዬ “ይሄ እውነት ነው። ለሰው አያዝኑም። የሰው ልጅ ሞቶ አውሬ እየበላው ስለ ፓርክ ያወራሉ። ሰው የሚበላው አጥቶ እየሞተ በብዙ ገንዘብ ቤተ መንግሥት ያስገነባሉ” በማለት ጠቅላይ ሚኒስትሩን ወቅሰዋል።

“የተናገሩትንና የፃፉትን የመደመር ዕሳቤ አምኜ ተከተልኩዎት። አሁን ግን በተናገሩት የማይኖሩ ብቻ ሳይሆን በሰው ደም የሚጫወቱ አረመኔ መሆንዎን ተረድቻለሁ” ሲሉ በገጻቸው ላይ አስፍረዋል።

በሕግ ሊያስጠይቃቸው የሚችል ነገር ይኖር እንደሆነ በቢቢሲ የተጠየቁት አቶ ታዬ ለዚህ ዝግጁ መሆናቸውን ጠቅሰው ነገር ግን ይህ የሚሆንበት ዕድል እንደሌለ ጥርጣሬያቸውን ገልጸዋል።

“ይህ [በሕግ መጠየቅ] ምን ችግር አለው ታዲያ። ነገር ግን ሕግ የታለና በሕግ ይጠይቁኛል። ከጠየቁኝ ደግሞ ዝግጁ ነኝ።”

የመንግሥት እና የገዢው ፓርቲ ከፍተኛ ባለሥልጣን ሆነው በጠንካራ ትችታቸው የሚታወቁት አቶ ታዬ ሰሞኑን በተከታታይ የሰነዘሯቸው አስተያያቶች ለስንብታቸው ምክንያት ይሆናል ብለው አያምኑም።

“ከዚህ ጋር የሚገናኝ አይመስለኝም። ከፓርቲያችን መርሆች ውስጥ ነጻነት አንዱ ነው። ከዚህ መርህ በተቃራኒ መቆም ተገቢ አይደለም። እኔ ስናገር የነበረው ይህንን መርህ መሠረት በማድረግ ነው” ብለዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ፊርማ ለአቶ ታዬ በተጻፈው ባለሦስት መስመር የስንብት ደብዳቤ ላይ የሰላም ሚኒስትር ዲኤታ ሆነው ላበረከቱት አስተዋጽኦ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አመስግነው ከዛሬ ታኅሣሥ 1/2016 ዓ. ም. ጀምሮ ከኃላፊነታቸው መነሳታቸውን አመልክቷል።

ከመስከረም 2014 ዓ. ም. ጀምሮ የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ የነበሩት አቶ ታዬ የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት (ጨፌ) አባል ሲሆኑ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እና በመገናኛ ብዙኃን ላይ በሚሰጡት አስተያየት የፌደራሉን መንግሥት እና የኦሮሚያ ክልልን በይፋ በመተቸት ይታወቃሉ።

ሰሜን ሸዋ የኩዩ ወረዳ እና አካባቢ ሕዝብን በመወከል የኦሮሚያ ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ታዬ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሚመራው ገዢው የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ ናቸው።

ስንብቱን ተከትሎ አቶ ታዬ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ በመጸጸት እንዳሰፈሩት “እውነት መስሎኝ በሀገር ህልውና ስም ሲያካሄዱ የነበረውን እና ኢትዮጵያውያንን ከማገዳደል አልፎ ሀገሪቷን ያደቀቃትን ከንቱ ጦርነት ሳዳምቅልዎ በነበረበት ወቅት ሲያወድሱኝ ነበር” ብለዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ደብዳቤ ላይ አቶ ታዬ ከሚኒስትር ዲኤታነት ሥልጣናቸው የተነሱበት ምክንያት ባይጠቀስም፣ እሳቸው ግን ይህ ውሳኔ የተላለፈባቸው ለሰላም በመቆማቸው መሆኑን አስፍረዋል።

“ዛሬ ነገሩ ገብቶኝ የወንድማማቾች መገዳደል ይቆም ዘንድ ለሰላም በመወገኔ ከሥልጣን አነሱኝ። ለወንበርና ለመኪና በመገዛት ኦሮሞን በኦሮሞ ለማጥፋትና ኦሮሞን ከወንድሞቹ ጋር ለማጣላት የሚጫወቱትን ቁማር እያየሁ ዝም ባለማለቴ እጅግ ደስተኛ ነኝ” በማለት ለነበራቸው አጭር ቆይታ አመስግነዋል።

ቢቢሲ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ እና በሰላም ሚኒስቴር ውስጥ ከሚገኙ ምንጮቹ መረጃ ለማግኘት ያደረገው ጥረት ባይሳካም የአቶ ታዬ ከሥልጣን መነሳት ግን እውነት መሆኑን አረጋግጧል።

አቶ ታዬ በግል የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ በመንግሥት ውስጥ ያሉ አመራሮችን በግልጽ በመተቸት እና ለመገናኛ ብዙኃን በሚሰጧቸው ቃለ ምልልሶች ከሌሎች የመንግሥት ባለሥልጣናት በተለየ ይታወቃሉ።

ባለፈው ሳምንት ከቢቢሲ ጋር ያደረጉት ሰፊ ቃለ ምልልስ ላይ በመንግሥት እና በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መካከል ሲደረግ ለነበረው ድርድር መደናቀፍ መንግሥታቸውን ተጠያቂ ያደረጉ ሲሆን፣ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ ስላሉት ግጭቶች፣ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ስለነበራቸው ግንኙነት እና በተለየዩ ጉዳዮች ላይ በሰነዘሩት ሐሳብ መነጋገሪያ ሆነው ሰንብተው ነበር።

በተጨማሪም እሁድ ኅዳር 30/2016 ዓ. ም. አዲስ አበባ ውስጥ ሊደረግ ታስቦ የነበረው እና መንግሥት “ሁከት የመቀስቀስ ዓላማ ያለው ነው” በማለት ያገደው ሰልፍ መከልከል አልነበረበትም በማለት መንግሥትን ተችተው ነበር።

በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ውስጥ እየተካሄዱ ያሉ ግጭቶችን እንዲቆሙ የሚጠይቅ ነው የተባለውን ሰልፍ ለማስተባበር ከሞከሩት ሰዎች መካከል አራቱ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር የዋሉ ሲሆን፣ የፀጥታ እና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል የተባለው መንግሥታዊ አካልም ከሰልፉ ጋር በተያያዘ 97 ሰዎችን መያዙን መግለጹ ይታወሳል።

የሰላም ጥሪ የሆነው ሰልፍ መከልከሉን በተመለከተ አቶ ታዬ ደንደአ ከዚህ በፊት ባልተለመደ ሁኔታ መንግሥት የወሰደውን እርምጃ ተቃውመዋል።

“የጦርነት ከበሮ በመታንበት አደባባይ ዜጎች በሰላማዊ ሰልፍ ጦርነትን እንዳይቃወሙ መከልከል መጥፎ ትርጉም አለው” በማለትም ሰልፉ በመከልከሉ “ለመመለስ የሚከብድ ጥያቄ ሊነሳብን ይችላል” ሲሉም ስጋታቸውን ገልጸው ነበር።

አቶ ታዬ ከተማሪነት ጊዜያቸው ጀምሮ ፖለቲካዊ ጥያቄዎችን በማንሳት የሚታወቁ ሲሆን፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደር እስኪመጣ ድረስም ለበርካታ ዓመታት በእስር ቤት ቆይተዋል።     ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

 

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *