ባለፈው ጥቅምት ወር ይፋ የሆነው የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ውጤት ብዙዎችን ያስደነገጠ እና አስካሁንም መነጋገሪያ የሆነ ጉዳይ ነው።

በ2015 ዓ.ም. የማትሪክ ፈተናን ከወሰዱት ከ800 ሺህ በላይ ተማሪዎች መካከል 27 ሺህ ያህሉ ብቻ ከ50 በመቶ በላይ ውጤት አስመዝግበዋል።

በቀደመው 2014 ዓ.ም. ደግሞ ወደ 900 ሺህ ከሚጠጉ ተማሪዎች መካከል 30 ሺህ ያህሉ ብቻ ከ50 በመቶ በላይ አምጥተዋል።

ያለፉት ሁለት ዓመታት የ12ኛ ክፍል የመልቀቂያ ፈተና ውጤት በርካቶችን አስደንግጦ መነጋገሪያ ከመሆኑ ባሻገር፣ በአገሪቱ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ ያለውን ድክመት ይፋ ያወጣ ነው በማለት ባለሙያዎች ተናግረዋል።

በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ ያለው እነከን መንስዔ ከፖለቲካዊ፣ ከማኅበራዊ እና ከተቋማዊ ተጽእኖዎች ጋር ይያያዛሉ የሚሉ አሉ።

በሌላ በኩል በልጆች እና በወላጆች መካከል ለረጅም ጊዜ የቆየ ደካማ የማንበብ ልማድ በዓመታት ሂደት ውስጥ አሁን ለሚታየው ቀውስ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንዳለው የሚጠቅሱም ጥቂት አይደሉም።

ከተወሰኑ ዓመታት በፊት ዩኤስኤአይዲ ያካሄደው ጥናት በኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ሦስተኛው የሁለተኛ ክፍል ተማሪዎች እና ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ የሦስተኛ ክፍል ተማሪዎች ምንም ማንበብ እንደማይችሉ አመልክቷል።

እነዚህ መሠረታዊ ክህሎቶችን በማዳበር ረገድ ትልቅ ሚና የሚጫወቱት ደግሞ መጻሕፍት ናቸው።

ይህንን እውነት ከተረዱት መካከል አንዷ ኤልሳቤጥ ድንቁ ነች።

መምህርት፣ ጋዜጠኛ እና የሕፃናት መጽሐፍ ደራሲ ኤልሳቤጥ፣ ችግሩን በራሷ መንገድ ለመፍታት እርምጃዎችን መውሰድ እንደጀመረች ትናገራለች።

በግሏ በምዕራብ ኢትዮጵያ ወንጪ ወረዳ በጨቦ መንደር የሚገኙ ሕጻናትን ከቤተ መጻሐፍት ጋር አስተዋውቃለች።

በተለይ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ያሉ ልጆች “ትምህርት ቤት ከመሄድ እና መምህራኖቻቸው የሚጽፉላቸውን ከመገልበጥ የዘለለ ነገር” አያገኙም ትላለች።

እነዚህ ልጆች የማንበብ ልማዳቸውን እንዲያዳብሩ እና ከታች ጀምሮ እንዲሠሩ ብንረዳቸው “በዚህ ዓመት የታየው አሳዛኝ እና አገርን የሚያሳፍር ውጤት አይኖርም ነበር” ስትል ከልጆች ጋር መሥራት ያለውን ጥቅም ትገልጻለች።

ልጆችን በማስተማር በርካታ ዓመታትን ያሳለፈችው ኤልሳቤጥ፣ የሚያነቡ ሕፃናት ቁጥር በእጅጉ እየቀነሰ እንደመጣ ማስተዋሏን ትናገራለች።

“እኛ ጋዜጦችን እና መጽሔቶችን በየሜዳው በየግድግዳ ላይ የምናገኘውን ማንኛውንም ነገር እናነብ ነበር” ስትል ያደገችበትን ጊዜ ታስታውሳለች።

“አሁን ግን ወላጆች መጽሐፍ ይዘው ከመምጣት፣ ሞባይል ስልክ ወርውረው መገላገል የሚፈልጉበት ጊዜ ላይ ደርሰናል። በቁም ነገር መጽሐፍ ገዝተው ለልጆቻቸው ለልደት ወይም ለተለያዩ ዝግጅቶች የሚሸልሙ ወላጆች በጣም ጥቂት ናቸው።”

ይኹን እንጂ ልጆቻቸውን ወደ ከፍተኛ ደረጃ የሚያደረሰው የንባብ ባህል መሆኑን ትሞግታለች።

ወላጆች ራሳቸው እንደ አንባቢ ጥሩ አርዓያ በመሆን እና ልጆች ስልክ፣ ቴሌቪዥን እና ሌሎች ኤሌክትሮኒክስ ነገሮች ላይ የሚያሳልፉትን ጊዜ ቀንሰው ከመጽሐፍት ጋር ጥሩ ጓደኛ እንዲሆኑ በተቻለ መጠን ቤታቸው ውስጥ መጽሐፍት የሚገኙበት ሁኔታ እንዲያመቻቹ ትመክራለች።

ነገር ግን ይህ በገጠር ቀላል እንዳልሆነ ኤልሳቤጥ ታምናለች፤ ለዚህም ነው በገጠር ላሉ ሕፃናት በተለይ የሕፃናትን ቤተ መጻሕፍትን ለማቅረብ ጥረት እያደረገች የምትገኘው።

በየትምህርት ቤቶች በሚገኙ ቤተ መጽሐፍት እና በልጆች ቤተ መጻሕፍት መካከል ልዩነት አለ።

በትምህርት ቤት ውስጥ ያሉ ቤተ መጽሐፍት ዋና ዓላማ ሥርዓተ ትምህርቱን መደገፍ ሆኖ፣ ከዚህ ጋር የሚጣጣሙ አካዳሚያዊ መጽሐፍት እና ሌሎች ግብዓቶችን ማቅረብ ላይ ያተኩራሉ።

ነገር ግን የልጆቹ ቤተ መጽሐፍት ትኩረት በትናንሽ ልጆች ውስጥ የማንበብ እና የመማር ፍቅርን ማሳደግ ነው።

ለጀማሪ አንባቢ የሚሆኑ፣ በሥዕል የተደገፉ መጽሐፍት፣ ተረት ተረት እና ሌሎች ይዘቶችን የሚያቀርቡ ናቸው። እና ብዙውን ጊዜ የቤተሰብን መርሃ ግብሮች ከግምት ውስጥ ያስገባ የአገልግሎት ሰዓታትም ይኖሩታል።

ከዚህ በመነ ሳት ነው መምህርት ኤልሳቤጥ ድንቁ በልጆች ቤተ መጻሕፍት ላይ ትኩረት አድርጋ እየሠራች የምትገኘው።

ዕቅዷን እውን ለማድግ ጥረት

የኤልሳቤጥ ወላጆች ተወልደው ያደጉት በምዕራብ ኢትዮጵያ ወንጪ ወረዳ ውስጥ በወንጪ ሐይቅ አቅራቢያ በምትገኝ ጨቦ መንደር ውስጥ ነው።

ኤልሳቤጥ ተወልዳ ያደገችው አዲስ አበባ ቢሆንም፣ በተለያዩ አጋጣሚዎች የወላጆቿን የትውልድ መንደርን መጎብኘቷ አንድ ነገር ለመታዘብ አስችሏታል።

በመንደሩ ውስጥ በትምህርታቸው ስኬታማ የሆኑ ልጆች እምብዛም አይገኙም የምትለው ኤልሳቤጥ “ልጃገረዶች 8ኛ ክፍል ሲደርሱ ወደ ትዳር ይገባሉ ወይም ከተማ ሄደው የቤት ሠራተኛ ይሆናሉ። ወንዶቹም 12ኛ ክፍል ሳይደርሱ ሹፌር ለመሆን ወደ ከተማ ይሰደዳሉ።”

ወደ ተለያዩ ከተሞች ከሄዱ በኋላ ለተለያዩ “ችግር እና ስቃይ” መጋለጣቸውን እና “በቤት ሠራተኝነት ጉልበታቸው እየተበዘበዘ” መሆናቸውን አስተውላለች።

“ከመንደሩ ማን ዩኒቨርሲቲ እንደገባ ብጠይቅ ማንም ተማሪ የለም” የምትለው መምህርቷ “ምን ላድርግ?” በማለት ማሰብ ጀመረች።

ያኔ ነው የሕጻናት ቤተ መጽሐፍት የመክፈት የረጅም ጊዜ ህልሟን እውን ለማድረግ በምታውቃት መንደር ለመጀመር የወሰነችው።

ነገር ግን ከማስተማር እና አልፎ አልፎ በጋዜጠኝነት ከምትሠራው የትርፍ ሰዓት ሥራ የምታገኘው ገቢ ቤተ መጽሐፍትን መክፈት ይቅርና የቤተሰብ ወጪን ሙሉ በሙሉ አይሸፍንም።

“እኔ ግን የተግባር ሰው ነኝ፤ አንድ ነገር ካሰብኩ ሳላደርገው እንቅልፍ አይወስደኝም” በማለት ድጋፍ ለማግኘት ተሯሯጠች።

በመጀመሪያ ያማከረቻቸው በመንደሩ ተወልደው ያደጉ ባለሀብቶችን ነበር። በመንደሩ ውስጥ የታዘበቻቸውን ችግሮች በበለጠ የሚያውቁ “በእኔ ዓላማ ደስተኛ ይሆናሉ” ያለቻቸውን ሰዎች “የባለቤትነት ስሜት እንዲሰማቸው” የዕቅዷ ተሳታፊ እንዲሆኑ ጋበዘቻቸው።

ይሁን እንጂ ብዙ ያልጠበቃቸው ሰዎች “ምን ማለት እንደሆነ አልገባቸውም” ትላለች፤ ድካሟ እና ሩጫዋ ከንቱ እንደሆነ ነገሯት።

ኤልሳቤጥ ግን እጆቿን አጣጥፋ አልተቀመጠችም። ጉዳዩን ለቤተሰቦቿ እና በአገር ውስጥ እና ከአገር ውጪ ያሉ የቅርብ ጓደኞቿን ስታማክር በደስታ ተቀበሏት።

ወላጆቿ በመንደሩ ውስጥ ከወረሱት መሬታቸው ላይ የተወሰነ ቆርሰው ሰጡ። ሌሎች የሚችሉት በገንዘብ የማይችሉት ደግሞ በመጽሐፍት፣ በቁሳቁስ እና በሃሳብ ደገፏት።

ንባብ እና ጨዋታ ለልጆች

ኤልሳቤጥ እርምጃ ከመውሰዷ በፊት ግን አንድ ጥያቄ መመለስ ነበረባት።

የገጠር ትምህርት ቤቶች ትንንሽ ቤተ መጽሐፍት ሊኖራቸው ይችላል፤ ነገር ግን ተማሪዎች የሚጠቀሙባቸው በትምህርት ሰዓት ብቻ ነው። በገጠር የሕፃናት ቤተ መጽሐፍት ብዙም አልተለመደም።

ልጆችም ጊዜያቸውን ከትምህርት ቤት ውጪ በተለያዩ የቤተሰብ ሥራዎች ላይ ነው የሚያሳልፉት። ስለዚህ “መጽሐፍ ለማንበብ እንዴት ብለው ይመጣሉ?” ብላ አሰበች።

“ምግብ እናዘጋጅ” የሚል ሐሳብ ተነስቶ ነበር፤ ኤልሳቤጥ ግን “ለምግብ ብለው እንዲመጡ አልፈለኩም” ብላለች። ጊዜ ወስዳ ካሰበችበት በኋላ የልጆች ቤተ መጽሐፍት እና መጫወቻ አንድ ላይ ለመክፈት ወሰነች።

“ልጆቹ ያነባሉ፤ ከዚያም ወጥተው ይጫወታሉ” በማለት ውሳኔው ልጆች እንዲመጡ እንዳበረታታ ትናግራለች።

በመሆኑም በሐምሌ ወር መጀመሪያ ላይ በጨቦ የሕፃናት ቤተ መጽሐፍት እና መጫወቻ ቦታ በአንድ ላይ ተከፈተ።

የመጀመሪያ የልጆች መጽሐፉን በእንግሊዘኛ ያሳተመው ታላቅ ወንድሟ ይስሃቅ ድንቁ በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቶ ስለነበር ቤተ መጽሐፍቱ እና መጫወቻ ቦታው ለእሱ መታሰቢያ እንዲሆን በስሙ ተሰይሞ እና ለመንደሩ ማኅበረሰብ በስጦታ መልክ ተሰጠ።

ቤተ መጽሐፍቱ ሁለት ክፍሎች እና የመጫወቻ ሜዳ አለው፤ በተጨማሪም በአካባቢው ቋንቋ በኦሮምኛ፣ በአማርኛ እና በእንግሊዘኛ የተጻፉ የመማሪያ መጽሐፍትን እንዲሁም ፊደልን የሚለማመዱባቸው እና የንባብ ልምዳቸውን የሚያዳብሩ በሁለት ቋንቋ የተዘጋጁ መጽሐፍትን ያካትታል።

አገልግሎቱ በክረምቱ ወቅት ስለተጀመረ ከተጠበቀው በላይ ልጆች መጥተዋል። ትምህርት ሲጀምር ቁጥራቸው ይቀንሳል የሚል ስጋት የነበራት ቢሆንም፣ አሁንም ብዙ ሕጻናት እየመጡ እንደሆነ ትናገራለች።

ልጆቹ ተማሪዎች ናቸው፣ የቤት ሥራ አላቸው፣ የቤተሰብ ሥራዎችን ለማገዝ ጊዜ ያስፈልጋቸዋል። እነዚህን ከግምት ውስጥ በማስገባት የልጆች ቤተ መጽሐፍቱ እና መጫወቻ ቦታው በሳምንት ሁለት ቀናት ቅዳሜ እና እሁድ ብቻ ነው አገልግሎት የሚሰጠው።

ቅዳሜ እና እሁድ ልጆቹ “በጉጉት የሚጠብቋቸው” ቀናት ናቸው፤ ወላጆችም ጥቅሙን ተረድተው ልጆቻቸውን እየላኩ እንደሆነ ትጠቅሳለች።

በእነዚያ ቀናት “ልጆች ‘ወዴት እየሄዳችሁ ነው?’ ሲባሉ ‘ወደ ቤተ-መጽሐፍት’ ብለው ሲመልሱ መስማት – ትልቅ እርካታ እና ደስታን የሚሰጠኝ ነገር ነው” ስትል ኤልሳቤጥ ትናገራለች።

አክላም “የተለያዩ በጎ አድራጊዎች ድጋፍ ስላደረጉልን የተለያዩ መጽሐፍትን እና መጫወቻዎችን ለመጨመር አቅደናል” ትላለች።

በጨቦ መንደር የከፈተችው ይህ የሕጻናት ቤተ መጽሐፍት እና የመጫወቻ ሜዳ “መነሻ ነው። በዚህ ብቻ አያቆምም” በማለት በኢትዮጵያ በተለይም በገጠር ላሉ ሕጻናት የሕጻናት ቤተ መጽሐፍት ለመክፈት ዕቅድ እንዳላት ትገልጻለች።

“ዓላማዬ እነዚህ ልጆች የማንበብን ጥቅም እና የት እንደሚያያደርሳቸው ማሳወቅ ነው። በልጆች ላይ መሥራት ማለት አገር መገንባት ማለት ነው ብዬ አምናለሁ።”

ኤልሳቤጥ ድንቁ በ2015 ‘ሰማያዊ ዣንጥላ’ በሚል ርዕስ የሕጻናት የተረት መጽሐፍ አሳትማለች። ዝግጅቱ የተጠናቀቀ ሁለተኛ መጽሐፏ ደግሞ በዚህ ዓመት እንደሚታተም ተስፋ አላት።

በተጨማሪ በዩቲዩብ ከአፀደ ሕጻናት እስከ አንደኛ ክፍል ላሉ ሕጻናት የአማርኛ ፊደሎችን፣ ታሪኮችን፣ የተለያዩ መረጃዎችን እና ለወላጆች ምክሮችን ታቀርባለች።

ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *