ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ላይ በአማራ ክልል የተፈጠረው ውጥረት ተባብሶ፣ ከሐምሌ ወር መገባደጃ አንስቶ በክልሉ የተለያዩ ከፍሎች ውስጥ በፋኖ ታጣቂ ቡድን እና በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች መካከል ለወራት የዘለቀ ግጭት እየተካሄደ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጥቅምት ወር ማብቂያ አካባቢ በአማራ ክልል ውስጥ እየተካሄደ ያለው ግጭት ያስከተለውን ጉዳት በተመለከተ ባወጣው መግለጫ የንጹሀን ግድያ፣ አስገድዶ መድፈር እና መፈናቀልን የመሰሉ የመብት ጥሰቶች እየደረሱ መሆናቸውን አመልክቷል።

በክልሉ ውስጥ በበርካታ አካባቢዎች ባለው አለመረጋጋት ምክንያት ትራንስፖርት፣ ስልክ እና ኢንተርኔትን የመሳሰሉ አገልግሎቶች በከፊል ወይም ሙሉ ለሙሉ የተቋረጡ ሲሆን፤ ዋና ዋና ከተሞችን ከተለያዩ አካባቢዎች ጋር የሚያገናኙ መንገዶችም መስተጓጎል እንደገጠማቸው ነዋሪዎች ተናግረዋል።

ለቀውሱ መቀስቀስ መንግሥት የክልሉን ልዩ ኃይል በማፍረስ መልሶ ለማዋቀር እና ታጣቂዎችን ትጥቅ ለማስፈታት መፈለጉ ሰበብ ይሁን እንጂ፣ በታጣቂዎቹ በኩል ግን ከዚህም ሰፋ ያሉ ምክንያቶች ይቀርባሉ።

መንግሥት ዓላማ የሌለው “ጽንፈኛ እና ዘራፊ” ቡድን ነው የሚለው ታጣቂው ፋኖ፣ በሕዝቡ ላይ የሚፈጸሙ በደሎችን በመቃወም ጠመንጃ ማንሳቱን በመግለጽ ራሱን “የመብት እና ነጻነት ታጋይ” አድርጎ ይመለከታል።

የፋኖ ኃይል ማን ነው?

“ፋኖ” የሚለው ስም በኢትዮጵያ የጦርነት ታሪክ እና አውድ ውስጥ ትልቅ ስፍራ ያለው ሲሆን መነሻውም ከ19ኛው ክፍለ-ዘመን የሚመዝ ስለመሆኑ ይነገራል።

ፋኖ ሕዝባዊ መሠረት እና ድጋፍ ያለው ነው የሚሉት የታሪክ አጥኚዎች፤ የችግር ጊዜ “በጎ-ፈቃደኛ ተዋጊ” ነው ይሉታል።

ሆኖም ግን የፋኖ ተዋጊዎች ስም የገነነው በ1920ዎቹ መጨረሻ በጣልያን ወረራ ወቅት ነው።

በጣልያን ወረራ የውትድርና ሙያ የሌላቸው ከአርሶ አደር ጀምሮ ያሉ ዜጎች በመሰባሰብ የአገራቸውን ዳር ድንበር ለማስከበር እንደ መደበኛ ጦር በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ተሰልፈው ተዋግተዋል።

ከዚያ ዘመን እንቅስቃሴ ስያሜውን የወሰደው የዚህ ወቅት የፋኖ እንቅስቃሴ በአማራ ክልል ውስጥ በይፋ መታወቅ የጀመረው በ2007/2008 ዓ.ም. በተቀሰቀሰው ፀረ መንግሥት ተቃውሞ ላይ የተሳተፉ ባልታጠቁ ወጣቶች ነው።

የታጠቀው እና በአሁኑ ወቅት በበርካታ የክልሉ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሰው ፋኖ በአብዛኛው የተመሠረተው እና ያለበትን ቅርጽ የያዘው፣ በክልሉ ውስጥ እና ከክልሉ ውጪ በአማራ ተወላጆች ላይ የሚፈጸሙ “ጥቃቶችን ለመመከት” በሚል በተሰባሰቡ ግለሰቦች ከ2010 ዓ.ም. ወዲህ መሆኑን የቡድኑ መሪዎች ይናገራሉ።

ከዚያን ጊዜ አንስቶ በተለያዩ የክልሉ ክፍሎች ውስጥ የተሰባሰቡት የታጠቁ የፋኖ አባላት ከአማራ ክልል ፀጥታ ኃይሎች ጋር በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲጋጩ ቆይተዋል። የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ተስፋፍቶ ወደ አማራ ክልል በተሻገረበት ወቅት ፋኖ በመንግሥት “ይሁንታ እና ድጋፍ” የበለጠ ተጠናክሯል።

የፋኖ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ እንደሆኑ የሚናገሩት አቶ አስረስ ማረ ዳምጤ “የህወሓት ኃይሎች ወደ አማራ ክልል ዘልቀው በመግባት ሕዝቡ ላይ ከፍተኛ ስቃይ እየፈጸሙ በነበረበት ወቅት ነው ይህ አደረጃጀት [ፋኖ] ነሐሴ 6/2013 ዓ.ም. የተፈጠረው።

“በጊዜው የክልሉ መንግሥት ፋኖ ለሚባለው አደረጃጀት ጥሪ እያደረገ በሚዲያም እውቅና እየሰጠ ያታግልም ነበር። ነገር ግን መንግሥት ትግሉን የሚፈልግበት ዓላማ እና እኛ የምንፈልግበት ዓላማ የተለያየ ነበር” ይላሉ።

ተዋጊዎቹም በአብዛኛው የህወሓት ኃይሎች ወደ በርካታ የአማራ ክልል አካባቢዎች በገቡበት ጊዜ የክልሉ እና የፌደራል መንግሥቱ ባቀረቡት የክተት ጥሪ መሠረት ጥሪውን የተቀበሉ ናቸው። በዚህም በተለያየ ሙያ ላይ ተሰማርተው የነበሩ ዜጎች እና ወጣቶች ዘመቻውን ተቀላቀሉ።

በጦርነቱ ወቅት ከክልሉ ልዩ ኃይል እና ከፌደራሉ የመከላከያ ሠራዊት ጎን ሆነው የተሰለፉት የፋኖ ታጣቂዎች፣ የጦርነቱን ማብቃት ተከትሎ ኢመደበኛ ታጣቂዎች ተብለው ትጥቅ እንዲፈቱ እና እንዲበተኑ ሲወሰን ቡድኑ ከመንግሥት ጋር መቃቃሩን መሪዎቹ ይናገራሉ።

ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ላይ የፌደራል መንግሥት የክልል ልዩ ኃይሎች እንዲበተኑ እና ወደ ፖሊስ ወይም ወደ መከላከያ እንዲቀላቀሉ እንዲሁም የፋኖ አባላት ትጥቅ እንዲፈቱ ሲወስን ተቃውሞ እና ግጭቱ ጀምሯል።

በተጨማሪም የትግራይ ጦርነትን ያበቃው የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በጦርነቱ ተሳታፊ የነበሩትን የአማራ ኃይሎችን አለማሳተፉ እና በሁለቱ ክልሎች መካከል አወዛጋቢ የሆኑት ቦታዎች ዕጣ ፈንታ ግልጽ አለመሆኑ የፈጠረው ቅራኔ ውጥረቱን እንዳባባሰው አቶ አስረስ ይጠቅሳሉ።

የኢትዮጵያን ፖለቲካ በቅርበት የሚከታተሉት እና ሂስ በመሰንዘር የሚታወቁት በአሜሪካ ነዋሪ የሆኑት የፖለቲካ ኢኮኖሚ ባለሙያው ዶ/ር ዮናስ ብሩ፣ ባለፈው ዓመት ሐምሌ መጨረሻ ላይ ለተቀሰቀሰው ጦርነት ምክንያት መንግሥት ነው ሲሉ ይወቅሳሉ።

“ሥርዓታዊ ግፍ፣ ግድያ እንዲሁም መፈናቀል” ለጦርነቱ መነሻ ነው የሚሉት ዶ/ር ዮናስ፤ የትጥቅ ፍቱ እርምጃ የደቀነው ስጋት በአፋጣኝ ጦርነት እንዲቀሰቀስ አድርጓል ባይ ናቸው።

“የአማራ ሕዝብ የኅልውና ስጋት ላይ ነው” ብለው የሚያምኑት በሰሜን ሸዋ የሚንቀሳቀሰው ፋኖ መሪ አቶ አሰግድ መኮንን፤ በክልሉ ውስጥ እና ውጭ እየደረሰ ነው የሚሉትን ጥቃት ለአብነት በማንሳት ፋኖ “የአማራ ሕዝብን ሰላም እና ደኅንነት የማስጠበቅ” ዓላማ የያዘ መሆኑን ይናገራሉ።

ለዚህ ዓላማ ታሪካዊውን የፋኖ ስም አዲስ ገጽታ በመስጠት ዘመናዊ አደረጃጀት መዘርጋታቸውን የሚጠቅሱት አቶ አስረስ ማረ፤ ቡድኑ ከዚህ ቀደም ይታወቅበት የነበረውን ቅርጽ እና አቋም በመቀየር “የፖለቲካ አቋም” እንዲኖረው መደረጉን ይገልጻሉ።

የጎጃም ፋኖ ዕዝ ምክትል መሪ እንደሆኑ የሚናገሩት አቶ ማንችሎት እሱባለው፣ ፋኖ የአማራ ሕዝብ ጥያቄ ናቸው ያሏቸውን በማንሳት ‘የሕዝብ ህልውናን ከማስጠበቅ እስከ ሕገ-መንግሥት መሻሻል’ የደረሱ ዓላማዎች እንዳሉት ይናገራሉ።

የክልሉ መስተዳደር እና የፌደራሉ መንግሥት የፀጥታ እና የመከላከያ ሠራዊትን በመሰማራት እየተዋጉት ያሉት የፋኖ ታጣቂዎችን “ዓላማ የሌላቸው፣ ጽንፈኛ እና ዘራፊ” በማለት በክልሉው ውስጥ ለወራት የዘለቀ ዘመቻ እያካሄዱ ነው።

ዶ/ር ዮናስ ግን ፋኖ በመንግሥት ላይ እንዲያምጽ እና ጠመንጃ እንዲያነሳ ያደረገው በቂ ምክንያት አለው የሚሉ ሲሆን፤ የሕዝቡን ጥያቄዎች በሰላማዊ ሰልፎች ጭምር ለመጠየቅ ባለፉት ዓመታት በተደጋጋሚ የተደረጉ ሙከራዎች ሰሚ አልባ ነበሩ በማለት ፋኖን “የመብት ታጋይ” ይሉታል።

ከባለፈው ዓመት አጋማሽ በኋላ በፋኖ ታጣቂዎች እና በመንግሥት መካከል የነበረው መቃቃር ተባብሶ፣ ታጣቂው ቡድን በርካታ አካባቢዎችን በመቆጣጠሩ የክልሉ አስተዳደር የፌደራሉ መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ መጠየቁ ይታወሳል።

ነገር ግን የፋኖ አባላት ይህንን መንግሥት ሕግ የማስከበር ነው ያለው ወታደራዊ እርምጃን “በሕዝብ ላይ የተፈጸመ ወረራ” ነው ይሉታል።

ለዚህም ምክንያት የሚያቀርቡት ሐምሌ 28/2016 ዓ.ም. ከተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አስቀድሞ የፌደራል የፀጥታ ኃይሎች ወደ ክልሉ መግባታቸውን ነው።

ምንም እንኳ ከዚህ ቀደም ስለ ቡድኑ ፍላጎት የተናገሩት የቡድኑ መሪዎች “የአማራን ሕዝብ በደል ማስቆም እና ጥቅሞቹን ማስከበር” እንጂ የሥልጣን ፍላጎት እንደሌላቸው ቢገልጹም፤ ቢቢሲ ያነጋገራቸው የፋኖ መሪዎች ግን የመጨረሻ ግባቸው የአገዛዝ ለውጥ ማድረግ ነው ብለዋል።

ከዚህ አንጻር ወታደራዊ አቅሙን አጋንኖ ያያል በማለት ታጣቂውን የሚተቹት ዶ/ር ዮናስ፤ የሚደርስበትን ግብ ግልጽ በሆነ መንገድ የለየ ጠንካራ የፖለቲካ ኃይል ባለመኖሩም እንቅስቃሴው ሩቅ አይጓዝም የሚል ግምገማ አላቸው።

መንግሥት እና ፋኖ በወታደራዊ አቅም ደረጃ የተለያየ አቋም ላይ የሚገኙ መሆናቸውን የሚጠቅሱት ዶ/ር ዮናስ፣ መንግሥት በድሮን፣ በታንክ እና በትላልቅ መሳሪያዎች የተደራጀ ሠራዊት እንዳለው በመግለጽ ፋኖ ከዚህ ጋር እንደማይነጻጸር ያመለክታሉ።

“የፋኖ አቅም ሕዝብ ነው። የጦር መሳሪያ ኃይል የለውም። ሕዝብ ጋር ያለን አቅም ለመያዝ እና ለማነሳሳት ደግሞ ፖለቲካ እና የሕዝብ ግንኙነት ወሳኝ ነው። ፋኖ ደግሞ የፖለቲካ አቅም መመሥረት አልቻለም” ይላሉ።

አቶ አሰግድ መኮንን ግን የፋኖ እንቅስቃሴ የፖለቲካ ክንፍ እንዳለው ይናገራሉ። በሌሎች ዘንድ ሊታወቅ ያልቻለው ግን የፖለቲካ ክፍሉ ሥራውን እያከናወነ ያለው ምሥጢራዊ በሆነ መንገድ ነው በሚል ዝርዝር መረጃን ከመስጠት ተቆጥበዋል።

የፋኖ እንቅስቃሴ ከአማራ ክልል ባሻገር የአገሪቱን መንግሥታዊ ሥርዓትን የመቀየር ትልም እንዳለው የቡድኑ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አስረስ ማረ ዳምጤ ይናገራሉ።

ይህንንም ግባቸውን ለብቻቸው ሳይሆን “ከሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች ጋር ማለትም ከኦሮሞ፣ ከትግራይ፣ ከአፋር እንዲሁም ከየትኛውም ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ የፖለቲካ ኃይሎች ጋር ተነጋግረን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ሁኔታ መለወጥ እና የተሻለች አገር የመገንባት ዓላማ” እንዳላቸው ገልጸዋል።

ዶ/ር ዮናስ እንደሚሉት ግን የፋኖ አገራዊ የፖለቲካ ፍላጎት መሬት የረገጠ የፖለቲካ ስትራቴጂ እና ፍኖታ ካርታ የያዘ ባለመሆኑ በሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች እምነት እንዲጣልበት አያደርግም ሲሉ ምልከታቸውን አስረድተዋል።

የጦርነቱ ሁኔታ፣ አቅም፣ ድጋፍ እና አደረጃጀት

አራተኛ ወሩን እያገባደደ ያለው በፋኖ እና በመንግሥት ኃይሎች መካከል የሚካሄደው ጦርነት በድሮን እና በከባድ መሳሪያዎች ተደግፎ ያዝ ለቀቅ እያለ እንደቀጠለ ነው።

ምንም እንኳ መግለጫው ከመንግሥት በኩል የገለልተኝነት ጥያቄ ቢነሳበትም፤ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለውን ጦርነት አውድ እና አንደምታ በቃኘበት የቅርብ ጊዜ መግለጫው የንጹሀን ሞት፣ ያለ ፍርድ ግድያ፣ መፈናቀል እና አስገድዶ መድፈርን የመሰሉ ጥሰቶች እየተፈጸሙ ነው ብሏል።

መንግሥት ሕግ ማስከበር በሚለው ዘመቻው ታጣቂ ቡድኑን ወደ “ተራ ሽፍታነት” ቀይሬዋለሁ ሲል ስኬቱን ካሳወቀ ወራት ተቆጥረዋል። በሌላ ጎን ደግሞ ፋኖ ጦርነቱ ጥንካሬዬን ያሳየሁበት ነው በማለት በሁለቱ ወገኖች ግጭት ውጤታማው እኔ ነኝ ይላል።

ቡድኑ በክልሉ ካሉ ወረዳዎች ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑት በቁጥጥሩ ስር መሆናቸውን ለቢቢሲ የተናገረ ቢሆንም፣ መንግሥት አብዛኛውን የክልሉን አካባቢዎች መቆጣጠሩን ገልጾ፤ አንዳንድ ስፍራዎች ላይ “የማጽዳት ሥራ” ብቻ ይቀረኛል ካለ ሰንብቷል።

ለሁለት ዓመት የተካሄደው ጦርነት በትጥቅ እና በወታደራዊ አቋም ለቡድኑ ጥንካሬን እንደፈጠረለት ይታመናል። ነገር ግን በተለያዩ አካባቢዎች እና አመራር የተዋቀረው የታጣቂ ቡድኑ ይህም ደካማ ጎኑ እንደሆነ ሲነሳ ቆይቷል።

የተለያየ መጠሪያ ያላቸው የፋኖ አደረጃጀቶች እንዳሉ ያልደበቁት አቶ አስረስ ማረ ዳምጤ፤ ፋኖ “በአንድ መሪ፣ በአንድ መዋቅር፣ በአንድ አደረጃጀት ውስጥ አልገባም” ይላሉ።

ለዚህም ምክንያት ሲያቀርቡ “ትግሉ ሕዝባዊ ትግል” በመሆኑ አዳዲስ አደረጃጀቶች በመወለዳቸው ነው የሚሉት አቶ አስረስ፤ ለመሰባሰብ መልክዓ-ምድራዊ አቀማመጥ እንቅፋት ቢሆንም “የዓላማ አንድነት አለን በትብብርም እንሠራለን” በማለት ይናገራሉ።

ስንቅ ከሕዝቡ፤ ትጥቅ እና ተተኳሽ በስጦታ እንዲሁም በምርኮ እንደሚያገኙ የሚጠቅሱት አቶ አስረስ፣ በተወሰነ ደረጃ ደግሞ በውጭ አገራት ያሉ የአማራ ተወላጆች ድጋፍ እንደሚያደርጉላቸው ገልጸዋል።

ቡድኑ በተለይም የሥልጠና ድጋፎችን እንደ ኤርትራ ካሉ የውጭ አገራት ያገኛል መባሉን በፌዝ የሚመለከቱት የጎጃም ፋኖ ዕዝ ምክትል መሪ አቶ ማንችሎት እሱባለው “ስም ለማጥፋት የሚቀርብ ውንጀላ ነው” ሲሉ ያስተባብላሉ።

“ሕዝባዊ መሠረት ያለን በሕዝብ የምንመራ ነን፤ ሕዝባዊ ትግል ነው እያካሄድን ያለነው። የሚያበላን፣ የሚያጠጣን ሕዝባችን ነው።…ዝርዝር ወጥቶ ይሄ፣ ይሄ አገር ተብሎ ቢጣራ ከአንዳቸውም ጋር የመረጃ፣ የትጥቅ፣ የስንቅ፣ የሥልጠና ድጋፍ የለንም” ይላሉ።

ፋኖ ስለሚቀርብበት ክስና ውንጀላ

ፋኖ በፌደራል መንግሥቱ እና በሌሎች የክልል መንግሥታት ጥቃቶችን በማቀነባበር እና በመፈጸም ስሙ ከመነሳቱ ባሻገር “ወንጀለኛ፣ ዘራፊ፣ ጽንፈኛ፣ ሽፍታ፣ ጃዊሳ” የሚል ተቀጽላ ይሰጠዋል።

ቡድኑ በመንግሥት የሚቀርቡበትን ክሶች ውድቅ የሚያደርግ ሲሆን፤ ነገር ግን “የፋኖን ስም የሚጠቀሙ እና የክልሉ መንግሥት ያሰለጠናቸውና የተለየ ዓላማ ያላቸው” አደረጃጀቶች እንዳሉ አቶ አሰግድ መኮንን ይናገራሉ።

ይህን ሀሳብ የሚደግሙት የጎጃም ዕዝ ም/መሪ አቶ ማንችሎት፤ “የውጭ አገር ጎብኚዎችን ሳይቀር በማገት ስማችንን ለማጠልሸት መንግሥት ይሠራል” ሲሉ ክሱን ወደ መንግሥት ያዞሩታል።

ቡድኑ በሚቆጣጠራቸው አካባቢዎች የሕዝብ እና የመንግሥት ንብረቶችን በመጠበቅ ኃላፊነቱን የሚወጣ ነው ሲሉ የሚከራከሩት የፋኖ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ፤ ክሱ ዓላማችንና ጥያቄያችን ለማንኳሰስ ሲባል የሚቀርብ ነው በማለትም ውድቅ አድርገውታል።

ከዚህ ባሻገርም ታጣቂ ቡድኑ በአማራ ክልል ውስጥ በሚገኙ የክልል እና የአካባቢ ባለሥልጣንት ግድያ ይከሰሳል።

ኢሰመኮ እና የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ቢሮ ባወጧቸው መግለጫዎች በተለያዩ አካባቢዎች በርካታ የመንግሥት እና የገዢው ፓርቲ ሹማምንት በፋኖ ታጣቂዎች መገደላቸውን አስታውቀዋል።

የመንግሥት እና የአካባቢ ባለሥልጣናት ግድያን በሚመለከት ግን ፋኖ “ሹማምንቶቹ የጦርነቱ አካል እስከሆኑ ድረስ መሳሪያ ከያዘው ወታደር ለይተን አናያቸውም” ይላሉ።

“ለመከላከያ ሎጀስቲክስ ያቀርባሉ፣ መረጃ ይሰጣሉ፣ ፖሊስ እና ሚሊሻ ተመልሶ እንዲቆጣጠር እንዲደራጅ ያደርጋሉ፣ አባሎቻችንን ለማጥፋት ይሰራሉ። ስለዚህ በቀጥታ የጦርነቱ አካል ስለሆኑ ዒላማ መሆናቸው አይቀርም” ብለዋል የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊው።

ድርድርና ቀጣይ ዕጣ-ፋንታ

በአማራ ክልል የጦርነቱ ዳፋ የሕዝቡን በሕይወት የመኖር ዋስትናን ከማሳጣቱ ባሻገር በእንቅስቃሴ ገደብ ምክንያት እንደ መድኃኒት ያሉ መሠረታዊ ሸቀጦች እንዲስተጓጎሉ እና ማኅበራዊ አገልግሎቶች እንዲቆሙ ሆኗል።

በጦርነቱ መሃል መፈናፈኛ ያጡ በርካታ ነዋሪዎች ሕይወታቸውን በስጋት ከመምራት ባሻገር፣ ጥቂት የማይባሉ ከግጭቶች አካባቢ እየሸሹ ለመፈናቀል ተዳርገዋል።

ኢሰመኮ ንጹኃን በጦርነቱ የእሳት እራት እየሆኑ ነው ባለበት የጥቅምት ወሩ መግለጫው፤ ሁለቱ ወገኖች የሰላም አማራጮችን እንዲያማትሩ ጠይቋል።

የክልሉ ባለሥልጣናት ከሕዝብ ጋር ባደረጓቸው ውይይቶች ላይ መንግሥት ለግጭቱ ሰላማዊ መፍትሄ እንዲገኝ ፍላጎት እንዳለው እና በሩም ክፍት መሆኑን በተደጋጋሚ ሲናገሩ ተደምጠዋል።

ፋኖ በበኩሉ ለንግግር መጀመሪያ የመከላከያ ሠራዊት ክልሉን ለቅቆ መውጣት አለበት የሚል ቅድመ ሁኔታ ይዞ የመደራደር ፍላጎት እንዳለው ተናግሯል።

እስካሁን ከመንግሥት በይፋ የእንደራደር ጥያቄ እንዳልቀረበላቸው የሚናገሩት አቶ አስረስ፤ ሊኖር ለሚችል ድርድር ፋኖ ‘ቀይ መስመሮቹን’ የያዘ ሰነድ ማዘጋጀቱን ተናግረዋል።

ጦርነቱ በዚህ የሚቀጥል ከሆነ ከሰብዓዊና ማኅበራዊ ቀውሱ ባሻገር ኢኮኖሚያዊ ቀውሱ ከባድ እየሆነ እንደሚገኝ ቢቢሲ በግብርና፣ በቱሪዝም እንዲሁም በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ ነዋሪዎች አነጋግሮ መረዳት ችሏል።

የኢትዮ ቴሌኮምን 45 በመቶ ድርሻ ለመግዛት ሂደት ላይ የነበረው የፈረንሳዩ የቴሌኮም ኩባንያ በአሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ምክንያት ግዢውን ማቋረጡ የጦርነቱ አንደኛው ዋጋ ነው የሚሉት ዶ/ር ዮናስ ብሩ፤ “መንግሥት ሊወጣው ከሚችለው በላይ ችግር ውስጥ እየገባ ነው” ይላሉ።

ቢቢሲ ለአማራ ክልል እንዲሁም ለፌደራል መንግሥቱ ባለስልጣናት ከፋኖ ጋር በተያያዙ ስለሚነሱ የድርድር እንዲሁም ሌሎች ጥያቄዎችን በሚመለከት ጥያቄዎችን ለማቅረብ ለሚመለከታቸው አካላት ተደጋጋሚ የስልክ መልዕክት ቢልክም ምላሽ ማግኘት አልቻለም።

ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *