የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ በትግራይ እና በአማራ ክልል የሚገኙ አወዛጋቢ አካባቢዎችን የተቆጣጠሩት ኃይሎች እስካልወጡ ድረስ ሕዝበ ውሳኔ እንደማይካሄድ ተናገሩ።

አቶ ጌታቸው ይህን ያሉት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ የተመራ የልዑካን ቡድን ጋር ትናንት ማክሰኞ በመቀሌ ባደረጉት ውይይት ነው።

“የታጠቁ ኃይሎች አካባቢውን ለቀው፣ የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ወደ ቀያቸው እስኪመለሱ ድረስ በትግራይ ሕዝበ ውሳኔ (ሪፈረንደም) አይኖርም። እንዲህ ብሎ ማሰብ በራሱ ተቀባይነት የለውም” ብለዋል።

በኢትዮጵያ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በኤክስ ገጹ ላይ ባጋራው መረጃ፤ “አምባሳደር ማሲንጋ በሰሜን ኢትዮጵያ ዘላዊ ሰላም በሚመጣበት መንገድ ዙሪያ ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አቶ ጌታቸው ረዳ ጋር ተወያይቷል” ብሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በቅርቡ በአማራ ኃይሎች ቁጥጥር ስር የሚገኙት አወዛጋቢ አካባቢዎች ዕጣ ፈንታ በሕዝበ ውሳኔ እንደሚፈታ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መግለጻቸው ይታወሳል።

“በትግራይ እና በአማራ ክልል ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ሕዝበ ውሳኔን ያማከለ አካሄድ ብንከተል የተሻለ እንደሚሆን የፌዴራል መንግሥት ያምናል። እኛ መልስ እየሰጠን እንደሆነ ነው የምናምነው፤ መፍትሄ አስቀምጠናል። መፍትሄው ያስማማል ወይስ አያስማማም የሚለው ላይ ግን መነጋገር ይቻላል” ሲሉ ለአገሪቱም ሕግ አውጪ ምክር ቤት አባላት ማብራሪያ ሰጥተው ነበር።

አንድ ዓመት በሞላው የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት በትግራይ እና በአማራ ክልሎች መካከል የይገባኝል ጥያቄዎች የሚነሱባቸው አካባቢዎች በአገሪቱ ሕገ-መንግሥት መሠረት መፍትሄ እንዲሰጠው ከስምምነት ተደርሷል።

ስምምነቱ የፌዴራል መንግሥት ያልሆኑ ኃይሎች ከትግራይ ለቀው እንዲወጡ የሚጠይቅ ቢሆንም የአማራ እና የኤርትራ ኃይሎች በተለያዩ የክልሉ ክፍሎች ውስጥ እንደሚገኙ የትግራይ ባለሥልጣናት ይገልጻሉ።

በዚህም ሳቢያ ከአንድ ሚሊዮን በላይ በምዕራብ ትግራይ ነዋሪ የነበሩ ሰዎች ተፈናቅለው በተለያዩ የትግራይ ክልል ክፍሎች በጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ እንደሚገኙ ተነግሯል።

በቅርቡ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባወጣው ሪፖርት በምዕራብ ትግራይ ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ በኋላ እና በስምምነት ካበቃ በኋላም ሰፊ የጦር ወንጀል እና የዘር ማጥፋት ወንጀሎች ተፈጽመዋል ብሏል።

የትግራይ ጊዜያዊ መስተዳደር አስተዳደር በአማራ ክልል ስር የሚገኙት አካባቢዎች ከጦርነቱ በፊት ወደ ነበሩበት የቀድሞ ይዞታቸው እንዲመለሱ ይፈልጋል።

የትግራይ ቴሌቪዥን ማክሰኞ ዕለት ባሠራጨው ዘገባ “ሕዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ጥያቄው በነጻ ምርጫ ወደ ሚመረጠው የክልል ምክር ቤት መቅረብ አለበት” ሲሉ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ መናራገራቸውን ጠቅሷል።

“በቅርቡ የፌደራል መንግሥት የወሰደው አቋም በምዕራብ ትግራይ ሕዝበ ውሳኔ ሊካሄድ እንደማይችል . . . ለምን ቢባል፤ ትናንት ሕዝባችንን ያፈናቀሉ፣ ወገኖቻችንን የገደሉ፣ ያሰቃዩ እና ያሸበሩት እዚያው በሥልጣን ላይ እያሉ ሕዝባችንን ወደ አካባቢው የመመለስ ጥቅሙ አይታየንም” ብለዋል።

“. . . ስለዚህ የፌደራል መንግሥት በፕሪቶሪያው ስምምነት እና በሕገ መንግሥቱ መሠረት በምዕራብ ትግራይ እና በደቡብ ትግራይ ያሉ ተቋማትን እንዲፈርሱ፣ ከሕግ ውጪ ያሉ ኃይሎች እንዲወጡ ማድረግ አለበት” ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሰላም ስምምነቱን እንዳይደፈርስ ስጋት ያለባቸው አካባቢዎች በሚመለከት በሰጡት አስተያየት የሕዝብ ፍላጎት መስማት እንደሚያስፈልግ አመልክተው ነበር።

“ከሕዝቡ ጋር ተወያይተናል። የሕዝቡን መልስ እናውቃለን። ግን ‘ይህ አማራጭ ብቸኛው አማራጭ አይደለም፤ የአማራ እና የትግራይ ምሁራን፣ የሃይማኖት አባቶች እና የአገር ሽማግሌዎች ተወያይተው ‘ዘላቂ ሰላም የሚያመጣ ሌላ አማራጭ መፍትሄ አለን’ ካሉ በደስታ እንቀበላለን” ብለው ነበር ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

በአገሪቱ የተካሄደውን የ1983 ዓ.ም. የመንግሥት ለውጥን ተከትሎ ክልሎች ቋንቋ እና ማንነትን መሠረት ባደረገ ሁኔታ ሲዋቀሩ ወደ ትግራይ ክልል ተካተዋል በማለት በአማራ ክልል በኩል ጥያቄ ሲቀርብባቸው የነበሩ ቦታዎች የትግራይ ጦርነት ሲቀሰቀስ በአማራ ኃይሎች ቁጥጥር ስር መግባታቸው ይታወቃል።

የእነዚህ አወዛጋቢ ቦታዎች ጉዳይ በእንጥልጥል ያለ ሲሆን፣ በሁለቱም ወገኖች ለንግግር እና ዘላቂ መፍትሄ ለማስገኘት የሚያስችሉ አስማሚ ሀሳቦች አልቀረቡም።  ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *