የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት የሰላም ስምምነቱ የሚጠይቀውን ሁሉ ተግባራዊ እያደረኩ ነው እያለ ባለበት በአሁኑ ወቅት፣ ከትግራይ በኩል ግን መንግሥት ቃሉን ሙሉ ለሙሉ እያከበረ አይደለም የሚል ወቀሳ እየተሰነዘረ ነው። መንግሥት ቅዳሜ ታኅሣሥ 08/2015 ዓ.ም. በኮሙኒኬሽን ጉዳዮች አገልግሎቱ በኩል ባወጣው መግለጫ ላይ የተደረሰውን ስምምነት ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን ገልጾ የነበረ ቢሆንም፣ በህወሓት በኩል ግን ከዚህ የሚቃረን ሃሳብ ተሰንዝሯል።

መንግሥት በመግለጫው “ለአገር እና ለሕዝብ ሲባል በተደረሰው የሰላም ስምምነት የገባውን ቃል ሳይውል ሳያድር እና ሳያንጠባጥብ በመፈጸም ላይ ይገኛል” ብሏል። ነገር ግን የህወሓት ሊቀመንበር እና የክልሉ ፕሬዝዳንት ዶክተር ድብረጽዮን ገብረሚካኤል መቀለ በተካሄደ ጉባኤ ላይ ሲናገሩ የሚጠበቅባቸውን እየፈጸሙ ቢሆንም በመንግሥት በኩል የሚጠበቀው ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ እየሆነ አይደለም ማለታቸውን የትግራይ ክልል መገኛኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

ዕሁድ ታኅሣሥ 09/2015 ዓ.ም. ዶ/ር ደብረጽዮን በትግራይ ክልል ምክር ቤት በተደረገ አስቸኳይ ስብሰባ ላይ የሰላም ስምምነት የአንድ ወር አተገባበርን በተመለከተ አቀረቡት በተባለው ሪፖርት ላይ፣ ስምምነቱ በሚጠበቀው መጠን እየተተገበረ እንዳልሆነ ገልጸዋል። ደብረጽዮን (ዶ/ር) የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመ ወዲህ በትግራይ በኩል ሁሉም የሰላም ስምምነቱ ጥያቄዎችን እየፈጸሙ መሆናቸውን ጠቅሰው “በፌደራል መንግሥት በኩል ከሰብአዊ እርዳታ አንፃር አበረታች ጉዳዮች ቢኖሩም በተቀሩት የሰላም ስምምነቱ ነጥቦች ዙርያ ግን መንግሥት በቃሉ መሠረት አልፈጸመም” ብለዋል።

ሁለት ዓመት ያስቆጠረውን የእርስ በርስ ጦርነት ለማስቆም በመንግሥት እና በህወሓት አመራሮች መካከል በመጀመሪያ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የተደረገውን ድርድር ተከትሎ ዘላቂ ግጭት የሚያስቆም እና ትጥቅ የመፍታት ስምምነት ተደርሶ ነበር። በማስከተልም ኬንያ ውስጥ በሁለቱም ወገኖች ወታደራዊ አመራሮች መካከል የፕሪቶሪያውን ስምምነት ለመተግበር በሚያስችል አጠቃላይ የትግበራ ሰነድ ላይ ስምምነት መፈረማቸው ይታወሳል።

በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት በተደረሰው ስምምነት ግጭት ማቆም፣ የሰብአዊ እርዳታ እንዲቀርብ፣ መሠረታዊ አገልግሎቶች እንዲጀመሩ፣ የህወሓት ተዋጊዎች ትጥቅ እንዲፈቱ እና ከፌደራሉ ሠራዊት ውጪ የሆኑ ኃይሎች ከክልሉ እንዲወጡ ስምምነት ተደርሷል። ከሁለት ሳምንት በፊት ደግሞ የሰላም ስምምነቱን አፈጻጸም በተመለከተ በሁለቱም ወገኖች ወታደራዊ አመራሮች መካከል ትግራይ ሽረ ከተማ ውስጥ ውይይት መደረጉ እና የትግራይ ኃይሎች ከውጊያ ግንባሮች እየወጡ መሆናቸው ተዘግቧል።

በተጨማሪም ሰላም ወርዶ ጦርነት ከቆመ በኋላ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ወደ ተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች ያለችግር እየደረሰ መሆኑን የመንግሥታቱ ድርጅት እና ሌሎች የእርዳታ ተቋማት ገልጸዋል። ከዚህ ጎን ለጎን በጦርነቱ የተጎዱ መሠረተ ልማቶችን በመጠገን ጥቂት በማይባሉ የትግራይ አካባቢዎች የኤሌክትሪክ አገልግሎት መጀመሩ የተዘገበ ሲሆን፣ የስልክ አገልግሎትም የተመለሱባቸው ቦታዎች እንዳሉ፣ በሌሎቹም ቦታዎች አገልግሎት ለማስጀመር ጥረት እየተደረገ መሆኑ ተነግሯል።

በፌደራሉ መንግሥት እና በህወሓት ኃይሎች መካከል ከተፈረመ ከአንድ ወር በላይ የሆነውን ስምምነት አፈጻጸምን በተመለከተ እስካሁን ያለበትን ሂደት በተመለከተ ዝርዝር መረጃ ከአሸማጋዮቹም ሆነ ከሁለቱም ወገን በይፋ የተሰጠ መረጃ የለም። ከዚህ አንጻር ባለፉት ቀናት ሁለቱም ወገኖች በተናጠል የሰላም ስምምነቱን በተመለከተ ያለበትን ደረጃ በየበኩላቸው ገልጸዋል። የፌደራሉ መንግሥት በሰላም ስምምነቱ የሚጠበቅበትን ሁሉ ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን እየገለጸ ያለ ቢሆንም፣ ደብረጽዮን ባቀረቡት ሪፖርት ላይ ደግሞ ከእርዳታ አቅርቦት ውጪ ተግባራዊ ያልሆኑ ጉዳዮች እንዳሉ አንስተዋል።

ዶክተር ደብረጽዮን ጨምረውም “በተደረሰው የሰላም ስምምነት ውል መሰረት የኤርትራ ሠራዊት እና የአማራ ታጣቂዎች በወረራ ከያዙት የትግራይ መሬት ለቀው ሊወጡ ሲገባ አሁንም በትግራይ መሬት ላይ ሆነው የትግራይ ሕዝብን እየጨፈጨፉ ይገኛሉ” ብለዋል። በሁለቱ ወገኖች መካከል በተደረሰው ስምምነት መሠረት በክልሉ ውስጥ ያሉ ከፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት ውጪ የሆኑ ኃይሎች ለቀው እንዲወጡ እና የህወሓት ተዋጊዎችም ትጥቅ እንዲፈቱ ይጠበቃል። ነገር ግን ይህ ስምምነት ተግባራዊ ስለመሆኑ እስካሁን የተባለ ነገር የለም።

ሁለት ዓመት የደፈነው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ የኤርትራ ሠራዊት የፌደራል መንግሥቱን በመደገፍ በግጭቱ ውስጥ ሲሳተፍ መቆየቱ ሲዘገብ የቆየ ቢሆንም፣ በሁለቱ ወገኖች በተደረሰው ስምምነት ላይ ግን የኤርትራ ስም በግልጽ አልተጠቀሰም። ዝርዝር ጉዳዮችን የያዘው የሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ከፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት ውጪ ያሉ ኃይሎች መውጣት በተጨማሪ የትግራይ ኃይሎች ትጥቅ እንዲፈቱ የሚጠበቅ ሲሆን፣ የፌደራሉ ሠራዊትም መቀለን ጨምሮ ወደ ሌሎች የትግራይ አካባቢዎች እንደሚገባ ያመለክታል።

የፌደራል መንግሥቱ ከቀናት በፊት እንዳሳወቀው የመከላከያ ሠራዊት ባልደረሰባቸው መቀለን ጨምሮ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የተደራጀ የዝርፊያ ድርጊቶች እየተፈጸሙ መሆናቸውን በመግለጽ፣ መንግሥት የሕዝቡን ደኅንነት ለመጠበቅ ያለበትን ኃላፊነት ለመፈጸም አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግ አመልክቷል። ይህንን በተመለከተ ደብረጽዮንም ሆኑ ህወሓት በይፋ የሰጡት ምላሽ ባይኖርም፣ ከህወሓት ከፍተኛ አመራሮች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ ግን የመንግሥት መግለጫን አያይዘው በትዊተር ገጻቸው አጭር አስተያየት አስፍረዋል።

“እኛ ልንፈታው የማንችለው፣ ሕዝባችን ሊፈታው የማይችለው ምንም አይነት የደኅንነት ስጋት፣ ማንም ሊፈታው አይችልም” በማለት ጽፈዋል። በሁለቱም ወገኖች በኩል ስምምነት ተደርጎ አስካልተራዘመ ድረስ ስምምነቱ በአንድ ወር ውስጥ ወደ ተግባር እንደሚሸጋገር ተገልጾ ነበር። ነገር ግን ከእነዚህ ወሳኝ ጉዳዮች አንጻር የተደረጉ ተግባራዊ እርምጃዎች ስለመኖራቸው ከየትኛውም ወገን የተባለ ነገር የለም።

ከባድ ሰብአዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ እና ፖለቲካዊ ቀውስን ያስከተለው የእርስ በእርስ ጦርነት ጥቅምት 23/2015 ዓ.ም. በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ፣ በኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት እና በህወሓት መሪዎች መካከል በተደረሰ ስምምነት ከቆመ ወደ ሁለት ወራት እየተቃረበ ነው።

ምንጭ – ቢቢሲ

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *