የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በወለጋ ዞኖች ውስጥ ባጋጠመው ግጭት ዋነኛ ተሳታፊዎች መንግሥት ‘ሸኔ’ እያለ የሚጠራው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እና የአማራ ታጣቂዎች ናቸው አለ። ባለፉት ጥቂት ቀናት በተለይ በምሥራቅ ወለጋ እና ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞኖች ብሔር ተኮር በሆኑ ጥቃቶች በርካታ ሰዎች ሕይወታቸውን ሲያጡ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ መፈናቀላቸው ተገልጿል።
የኢሰመኮ የምርምርና ክትትል ሪጅናል ዳይሬክተር ኢማድ አብዱልፈታ ለቢቢሲ ሲናገሩ “በሰላማዊ ሰዎች ላይ በሚፈጸሙ ጥቃቶች ውስጥ በዋነኝነት እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ የሚጠራው ቡድን እና የአማራ ታጣቂዎች ዋነኞቹ ተሳታፊዎች ናቸው” ብለዋል። ኢማድ ግጭቶቹን ተከትሎ ባለፉት ቀናት የደረሰውን የጉዳት መጠን ለማወቅ ማጣራት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።
“ሰዎች በማንነታቸው ዒላማ ተደርገው ጥቃት እንደሚደርስባቸው ያሰባሰብናቸው መረጃዎች እና ማስረጃዎች ያሳያሉ” ያሉት የምርምር እና ክትትል ዳይሬክተሩ፤ ከሰሞኑ የተፈጸሙት ጥቃቶች መጠን ከፍ ያለ ሊሆን እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል። ባለፉት ቀናት ያጋጠመው ችግር “ከዚህ በፊት ከተፈጸሙት ጥቃቶች ከፍ ያለ ሊሆን እንደሚችል” በተለያዩ መንገዶች ያስባሰቧቸው መረጃዎችን ይጠቁማሉ ብለዋል።
መንግሥት የዜጎችን ደኅንነት ያረጋግጥ
የፌደራል እና የክልሉ መንግሥታት ዝምታን በመረጡበት ጥቃት በምዕራብ ኦሮሚያ ምሥራቅ ወለጋ እና ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞኖች ብሔር ተኮር በሆኑ ጥቃቶች ሰላማዊ ሰዎች ሰለባ መሆናቸው መቀጠሉ እየተነገረ ነው። መንግሥት በጉዳዩ ላይ ያለው ነገር ባይኖርም ፖለቲከኞች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ማኅበራት ስጋታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ። የኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት በወለጋ ዞኖች በዜጎች ላይ እየደረሰ ያለው ሞት፣ መፈናቀል እና ሰቆቃ በእጅጉ ያሳስበኛል ያለ ሲሆን፣ መንግሥት የዜጎችን ደኅንነት የማረጋገጥ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርቧል።
ምክር ቤቱ ጨምሮም ግጭቱን ተከትሎ የሰብዓዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች በአፋጣኝ እንዲቀርብላቸው እንዲሁም፤ ለጉዳዩ ዘላቂ እና ሁለንተናዊ መፍትሄ እንዲፈለግ ጠይቋል። ፖለቲከኛው ጃዋር መሐመድ ደግሞ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ላለው ቀውስ መፍትሄ ናቸው ያላቸውን ሦስት ምክረ ሃሳቦች በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ላይ አስፍሯል። የኦሮሞ ፌደራሊስ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ከፍተኛ አመራር የሆነው ጃዋር መሐመድ መንግሥት ተኩስ በማቆም ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጋር ንግግር መጀመር አለበት ብሏል።
በተጨማሪም የፋኖ ሚሊሻዎችን ከኦሮሚያ አስወጥቶ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው መመለስ አለባቸው ያለው ጃዋር፣ አጠቃላይ ብሔራዊ የሰላም ሂደት ብቸኛው መፍትሄ በመሆኑ ይህን ለማሳካት አቅዶ መተግበር ያስፈልጋል ብሏል። ፖለቲከኛው በክልሉ ላለው ቀውስ ከታጣቂ ቡድኑ ጋር መንግሥት መነጋገር አለበት ይበል እንጂ፣ ከዚህ ቀደም የኦሮሚያ ክልል መስተዳደር ከታጣቂ ቡድኑ ጋር ለመደራደር እንደማይፈልግ ማሳወቁ ይታወሳል።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ)፣ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) እና ሌሎችም የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉዳዩን አስመልክተው ባወጧቸው መግለጫዎች፣ ወለጋ ውስጥ በዜጎች ላይ የሚፈጸመው ግድያ እንዳሳሰባቸውና መንግሥት ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
ግድያ እና መፈናቀል
ቢቢሲ ያነጋገራቸው በምሥራቅ ወለጋ ዞን ውስጥ በሚገኙት ጊዳ አያና እና ኪራሙ ወረዳ ነዋሪዎች ባለፉት ሳምንታት ጀምሮ ጥቃቶች እየተካሄዱ መሆናቸውናና በጥቃቶቹ በርካቶች ሲገደሉ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ መፈናቀላቸውን ገልጸዋል። ይህን ጥቃት በማድረስ ነዋሪዎች የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት [ሸኔ]፣ የአማራ ታጣቂዎችን እና የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይልን ተጠያቂ ይደረጋሉ።
በዚህም አንደኛው ወገን ለተፈጸሙ ጥቃቶችን በሌላኛው ወገን ያሉ ታጣቂዎችን ሲከሱ፣ የክልሉም ሆነ የፌደራል መንግሥቱ ተጠያቂውን ወገንንም ሆነ፣ ጥቃቶቹን ለማስቆም እና ችግር ላይ ያሉትን ለመርዳት እየተወሰደ ስላለው እርምጃ የተባለ ነገር የለም። ነዋሪዎች እንደሚሉት ከሳምንት ወዲህ እየተባባሰ በመጣው ጥቃት ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ነገር ግን በርካታ ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ከ200 ሺህ በላይ የሚሆኑ ነዋሪዎች ቀያቸውን ለቀው በአቅራቢያ ወደ ሚገኙ ስፍራዎች በመሄድ ለመፈናቀል መዳረጋቸውን እንዲሁም ከጥቃት ለማምለጥ በጫካ ውስጥ ተደብቀው የሚገኙ እንዳሉ ጨምረው ተናግረዋል። ባለፉት ዓመታት በምዕራብ ኢትዮጵያ በሚገኘው የኦሮሚያ አካባቢ በታጣቂዎች በሚፈጸሙ ተደጋጋሚ ጥቃቶች በመቶዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች መገደላቸውን በተለያዩ ጊዜያት ሲዘገብ መቆየቱ ይታወቃል።
ለዚህም በአካባቢው እንደሚንቀሳቀስ የሚነገረው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በዋናነት ሲከሰስ የቆየ ሲሆን፣ አሁን ደግሞ ከአጎራባች የአማራ ክልል አካባቢዎች ይገባሉ የተባሉ ታጣቂዎችም ተሳታፊ ናቸው እየተባለ ነው። ካለፈው ሳምንት አንስቶ በተባባሰ ሁኔታ በሰላማዊ ሰዎች ላይ እየተፈጸመ ያለውን ጥቃት መንግሥት እንዲያስቆምና ደኅንነታቸውን እንዲያስጠብቅ ነዋሪዎች እየጠየቁ ነው።
ምንጭ – ቢቢሲ