ከወለጋ ዞን ሆሮ ጉዱሩ ተፈናቅሎ አሁን አዲስ አበባ የሚገኘው የ37 ዓመቱ ግለሰብ፣ በአካባቢው ያለውን ሁኔታ በቃላት መግለጽ ከባድ ነው ይላል። ለደኅንነቱ ሲል ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገው ይህ ግለሰብ በቅርቡ በአካባቢው የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ በአንድ ቦታ ስምንት የቤተሰቡን አባላት እንዳጣ ለቢቢሲ ይናገራል። “ከቤተሰቦቼ ግማሹ ሕይወታቸውን አጥተዋል፤ በሕይወት የተረፉት ደግሞ ተበታትነዋል፤ የት እንዳሉ የማይታወቁም አሉ።”

በኦሮሚያ ክልል በተለይም በምዕራባዊው ክፍል የታጠቁ ኃይሎች ሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚያደርሱት ጥቃት ከጊዜ ወደ ጊዜ መጠኑ እየጨመረ የሚደርሰውም ጉዳት እየበረታ መጥቷል። ቢቢሲ በተለያዩ ጊዜያት ያናገራቸው ነዋሪዎች ለጥቃቱ ተጠያቂዎች ‘ፋኖ’ የሚሏቸው ኃይሎች እንዲሁም መንግሥት ሽብርተኛ ነው ያለው ኦነግ/ሸኔ እንደሆነ ይናገራሉ። ምንም እንኳ ሁለቱ ኃይሎች ለሚደርሰው ጥቃት ኃላፊነት ወስደው ባያውቁም የፌዴራሉ መንግሥት እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ጣታቸውን ወደ ታጣቂዎቹ ይቀስራሉ።

የኦሮሚያ ክልል ባለሥልጣናት ‘ኦነግ/ሸኔ’ እንዲሁም ‘አክራሪ የአማራ ኃይሎች’ ለፖለቲካ ዓላማቸው ሲሉ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃት እያደረሱ ነው ሲሉም ይወቅሳሉ። ላለፉት አራት ዓመታት በመንግሥትና በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት (ሸኔ) መካከል በተደረጉ ግጭቶች ሳቢያ በርካታ ሰላማዊ ነዋሪዎች ሕይወታቸውንና ንበረታቸውን አጥተዋል፤ ቀያቸውን ጥለው ተሰደዋል።

በኦሮሚያ ክልል ያለው ግጭት ከመገናኛ ብዙኃን ዕይታ የተሸሸገ ይመስላል፤ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ትኩረት ተነፍጎታል። ይህ የሆነው ለምን ይሆን? መንግሥትስ የሰላማዊ ዜጎችን ደኅንነት መጠበቅ ለምን ተሳነው?

ትኩረት የተነፈገው ግጭት

በኦሮሚያ ክልል በተለይም በደቡባዊ እና በምዕራባዊ ክፍሎቹ ውስጥ የሚታየው ቀውስ ላለፉት አራት ዓመታት ዘልቋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ የፖለቲካ ምሕዳሩ እንዲሰፋ በማለት በውጭ አገራት እና ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ አገር ቤት እንዲገቡ ፈቀዱ። በዚህ ወቅት ወደ ፖለቲካው መድረክ ከተመለሱ ፓርቲዎች መካከል ለዘመናት የትጥቅ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የነበረው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) አንዱ ነው።

ይህንን ውሳኔ ተከትሎ ኦነግ ለሁለት ተከፈለ። አንደኛው ክንፍ የትጥቅ ትግሉን አቁሞ በሰላማዊ መንገድ እታገላለሁ የሚለው ሲሆን፣ ሌላኛው ክንፍ ደግሞ በጠመንጃ አላማውን ለማሳካት የሚታገል ነው። እነዚህ ጉዳዮች በአገር ቤት መገናኛ ብዙኃን ቢዘገቡም በዓለም አቀፍ ሚድያ ግን ችላ የተባሉ ነበሩ ይላሉ የአዲስ ስታንዳርድ መሥራች ፀዳለ ለማ። በተለያዩ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን በመቅረብ በኢትዮጵያ ስላሉ ሁኔታዎች ትንታኔ በመስጠት የሚታወቁት ፀዳለ፣ የኦሮሚያ ጉዳይ በተለያዩ ርዕሰ ዜናዎች ምክንያት ተቀብሮ ነበር ይላሉ።

ከእነዚህ ምክንያቶች አንደኛው የትግራይ ጦርነት ነው። የትግራይ ኃይሎች በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መሰንዘራቸውን ተከትሎ በትግራይ ውስጥ ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት፣ ኦነግ/ሸኔ እንዲሁም ህወሓት ሽብርተኛ ቡድኖች ናቸው ሲል ማወጁ ይታወሳል። ይህ የታጠቀ ኃይል በተለያዩ ጊዜያት ሰላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃት ሰንዝሯል በሚል በተደጋጋሚ ወቀሳ ቢደርስበትም ቡድኑ ለደረሱት ጥቃቶች ኃላፊነት ከመውሰድ ተቆጥቧል። ፀዳለ እንደሚሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ የፖለቲካ ምሕዳሩን ሲከፍቱ፣ እሥረኞችን ሲፈቱ፣ የምጣኔ ሃብት ‘ሪፎርም’ እያካሄዱ ሳለ በኦሮሚያ ክልል ግጭት ነበር።

“ምንም እንኳ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እና የመገናኛ ብዙኃን ችላ ቢሉትም፣ የኦሮሞ ነፃነት ኃይል ከኦሮሞ ነፃነት ግንባር ሲገነጠል፤ ግጭቶች ሲጀማምሩ. . . የአገር ቤት ሚድያው ሲዘግብ ነበር።” አክለው እንደሚሉት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ለኦሮሞ ጥያቄ ምላሽ ናቸው” ብሎ ስለሚያስብ በኦሮሚያ ክልል ያለው ሁኔታ ትኩረት ተነፍጎታል። በሰሜን በኩል መንግሥት ከትግራይ ኃይሎች ጋር ጦርነት ላይ በነበረበት ወቅት ጭምር ከኦሮሚያ ክልል የሚወጡ ዜናዎች መልካም አልነበሩም።

የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት፣ ኦሮምያ ክልል ያሉ የአማራ ተወላጆች ላይ ጥቃት እያደረሰ ነው መባሉን ተከትሎ ፋኖ የተባለው ኃይል ጥቃት እያደረሰ ነው የሚል ወሬ መሰማት ጀመረ። ተንታኟ እንደሚሉት ይህ ግጭት ከመገናኛ ብዙኃንና ከሰብዓዊ መብት ቡድኖች ዕይታ ውጪ የሆነበት ሌላኛው ምክንያት ጦርነቱ የሚካሄድበት ቦታ በጣም ራቅ ያለ መሆኑ ነው። “ደቡብ እና ምዕራብ ኦሮሚያ ጀምሮ ተስፋፍቶ አሁን ወደ ማዕከል የመቅረብም ነገር አለ። የኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት መቋረጡ የሚድያ ሽፋን እንዳይሰጠው አስተዋፅዖ አድርጓል።”

ከኦሮሚያ ክልል በግጭት ከተፈናቀሉት መካከል

የዜጎች ደኅንነት ጉዳይ

ቢቢሲ በተለያየ ጊዜያት ጥቃት ሲደርስ የሚያናግራቸው ሰላማዊ ዜጎች በማንነታቸው ምክንያት ሰለባ እንደሆኑ፣ ቤት ንብረታቸውን ጥለው እንደተፈናቀሉ ይናገራሉ። ከእነዚህም መካከል የ37 ዓመቱ የሆሮ ጉዱሩ ነዋሪ የመንግሥት ኃይሎችን ከደረሰበት ጥቃት ሊያስጥሉት እንዳልቻሉ ይናገራል። በተለይም በምዕራብ ወለጋ የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች በተደጋጋሚ ለሚደርስባቸው ጥቃት የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊትን ተወቃሽ በማድረግ፤ መንግሥት ተገቢውን ጥበቃ አላደረገልንም ይላሉ። የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት በበኩሉ “ጥቃቱን አልፈፀምንም፤ ተጠያቂው መንግሥት ነው” የሚል ምላሽ በመስጠት ክስተቱ በገለልተኛ አካል ይጣራ ይላል።

“አሁን ያለው ሁኔታ ግጭት ከማለት ጦርነት ተብሎ ቢጠራ ይሻላል” ይላሉ በጄምስ ማዲሰን ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ታሪክ መምህር እና ተመራማሪው ፕ/ር ኢታና ሃብቴ። ተመራማሪው በተለያዩ ቦታዎች ዜጎች በማንነታቸው ምክንያት ጥቃት ሲደርስባቸው መንግሥት ደኅንነታቸውን  የመጠበቅ ኃላፊነቱን አልተወጣም ብለው ያምናሉ። ምሑሩ፤ መንግሥት ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ሁኔታውን የመቆጣጠር አቅም አለው፤ ነገር ግን ፍላጎት ይኑረው አይኑረው እርግጠኛ አይደሉም። በኦሮሚያ ክልል ግጭት በሚከሰትባቸው ቦታዎች ያሉ ነዋሪዎች የሚያቀርቡትን ቅሬታ በተመለከተ ምላሽ እንዲሰጡን የክልሉ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ እንዲሁም የፈደራል ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎትን ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

ኮሚሽናቸው በቅርቡ የተዘገቡ ጥቃቶችን በተመለከተ ምርመራ እያደረገ እንደሆነ የጠይቅናቸው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) “መረጃ እየሰበሰብን ነው። ምርመራችን ስናጠናቅቅ ውጤቱን ይፋ እናደርጋለን” ሲሉ ለቢቢሲ ምላሽ ሰጥተዋል። በሌላ በኩል ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋማት ወደ አካባቢው አቅንተው ጉዳዩን እየመረመሩት እንደሆነ  ለማጣራት ያናገርናቸው አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂዩማን ራይትስ ዋች “ለጊዜው አስተያየት መስጠት አንችልም” የሚል ምላሽ ሰጥተውናል።

ፀዳለ፤ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከሌሎች በተሻለ መረጃ የማግኘት ዕድል አለው ብለው ቢያምኑም “ድርጅቱ የሚያወጣው ሪፖርት አከራካሪ መሆኑ ተነሳሽነቱን ጎድቶታል” ብለው ያስባሉ። “ገለልተኛ የሆነ ሪፖርት ቢያወጡ እንኳ አወዛጋቢ ስለሚሆን ይህ ጉዳይ መነሳሳታቸውን የጎዳው ይመስለኛል። ይሄ ሊሆን ባይገባማ አስተዋፅዖ ግን ይኖረዋል።” ተንታኟ፤ ሌሎች ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋማት የኦሮሚያን ግጭት ልክ እንደ ትግራይ ጦርነት ተከታትለው ባይመረምሩትም፣ ከዚህ ቀደም የተወሰኑ ምርምራ ማከናወናቸውን መዘንጋት አይፈልጉም። እርሳቸው እንደሚሉት ከላይ የተጠቀሱት ምክንያቶች ልክ እንደ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ሁሉ የሰብዓዊ መብት ተቋማትም ጉዳዩን ችላ እንዲሉት አስተዋፅዖ አድርጓል።

ግጭቱ የመቆም ተስፋ ይኖረው ይሆን?

ፕሮፌሰር ኢታና፤ “ይህን ጥያቄ ከ2018 በፊት ብጠየቅ ቀለል ያለ ምላሽ እሰጥ ነበር” በማለት፣ ጉዳዩ አሁን በጣም ከባድ እና የተወሳሰበ ደረጃ ላይ ስለደረሰ በቀላሉ ምላሽ የሚገኝበት አይመስልም። አዲስ ስታንዳርዷ ፀዳለ ለማ በበኩላቸው፣ ለችግሩ ፖለቲካዊ መፍትሔ እንዲበጅለት “መንግሥት ዝግጁ አይደለም” የሚል ስጋት አላቸው። ፀዳለ፤ መንግሥት የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊትን ሽብርተኛ ተብሎ፤ እውቅና መንፈጉ፣ ጉዳዩ ከቁም ነገር እንዳይወሰድ ትልቅ ሚና ተጫውቷል ይላሉ። “የኦሮሞ ፓርቲዎችን ጨምሮ አንዳንድ ፖለቲከኞች በመንግሥት ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል። ይህንን የተቃወሙ ሌሎች ፓርቲዎች ደግሞ ከፖለቲካ ምሕዳሩ ተገፍተዋል።”

መንግሥት፤ ለኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት እውቅና መስጠት በፍፁም አይሻም የሚሉት ፀዳለ፣ ይህ ካልሆነ ፖለቲካዊ መፍትሔ አይመጣም ብለው ያምናሉ። ፕ/ር ኢታና ደግሞ መጀመሪያ መቅደም ያለበት ጦርነቱ መቆሙ ነው ይላሉ። “ጦርነት ካልቆመ ንግግር ማድረግ አይቻልም።” “የሕዝብ ደኅንነት ተጠብቆ፤ የታጠቀው ኃይል እውቅና ተሰጥቶት፤ ጥያቄዎች ወደ ጠረጴዛ መጥተው ውይይት ሊደርግባቸው ይገባል።”

ከዚህ ጋር በተያያዘ የኦሮምያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አወሉ አብዲ መንግሥታቸው በክልሉ ለሚስተዋለው የፀጥታ ችግር መፍትሔ ለማበጀት እየሠራ ነው ሲሉ ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል። ነገር ግን አሁንም ሰላማዊ ዜጎች በስጋት ውስጥ መኖራቸውን ቀጥለዋል፤ በየትኛዋ ደቂቃ ቤት ንብረታቸውን ጥለው ሊሰደዱ እንደሚችሉ አያውቁም፤ ብዙዎች ለቅሷቸውን ለፈጣሪያቸው ከማሰማት ውጪ አማራጭ ያላቸው አይመስልም።

ምንጭ – ቢቢስ

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *