የኤርትራ ጦር በትግራይ ሕዝብ ላይ እያደረሰ ያለውን ግፍ እንዲያቆም እና ከትግራይ በአስቸኳይ እንዲወጣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጠንካራ እርምጃ እንዲወስድ ህወሓት ጠየቀ። ህወሓት ይህንን ጥሪ ያቀረበው ቅዳሜ ኅዳር 10/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ሲሆን፣ የኤርትራ ጦር በትግራይ ሕዝብ ላይ “ተቆጥሮ የማያልቅ ግፍ እየፈጸመም ነው” ብሏል። በዚህም መግለጫ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በተለይም ደግሞ የአፍሪካ ኅብረት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ አሜሪካ እና የአውሮፓ ኅብረት በኤርትራ አገዛዝ ላይ ጠንካራ  እርምጃ እንዲወስዱ ጥሪ አቅርቧል።

ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በተጨማሪ የኢትዮጵያ መንግሥትም የኤርትራ ጦር በትግራይ ሕዝብ ላይ እየፈጸመ ነው ያለውን ግፍ እና በደል በአስቸኳይ እንዲያስቆም ህወሓት ጠይቋል። በተጨማሪም ጦሩ ከትግራይ መሬት በአስቸኳይ እንዲወጣ እና እየፈጸማቸው ባሉ ወንጀሎች እንዲጠየቅ የኢትዮጵያ መንግሥት እና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ “ሁለንተናዊ ጥረት ሊያደርጉም እንደሚገባም” ይኸው መግለጫ አትቷል። በኢትዮጵያ መንግሥትና በህወሓት መካከል የተደረሰውን ግጭት በዘላቂነት የማቆም ስምምነትን ተከትሎ ኤርትራ ሠራዊቷን ከማስወጣት ይልቅ ተጨማሪ ሠራዊት ወደ ትግራይ እያስገባች ትገኛለች ብሏል።

የኤርትራ ጦር “የትግራይ ሕዝብ እና መንግሥት ሃብት እና ንብረት በተሽከርካሪ እየጫነ እየዘረፈ፣ መውሰድ ያልቻለውንም እያወደመው እና እየቃጠለው፣ የትግራይ ቅርሶች በስፋት እያወደመ እና እየዘረፈ ይገኛል” በማለት “ካሁን በፊት በትግራይ እና ሕዝቡ ላይ ሲያካሂድ የቆየው ሁለንተናዊ ማጥቃት ከደቡብ አፍሪካው ስምምነት በኋላም አጠናክሮ ቀጥሏል” ሲል ከሷል። ከጥቂት ሳምንታት በፊት በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት መካከል የተደረሰው ስምምነትን ተከትሎ፣ ናይሮቢ ላይ በተፈረመው የስምምነት ማስፈጸሚያ ዝርዝር መሠረት የትግራይ ኃይሎች ትጥቅ እንዲፈቱ እና የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ውጪ ያሉ ኃይሎች ከትግራይ እንዲወጡ ከስምምነት መደረሱ ይታወሳል።

ሁለት ዓመታት ባስቆጠረው ጦርነት ውስጥ የኤርትራ ኃይሎች በትግራይ ውስጥ ፌደራል መንግሥቱን ደግፈው መሰማራታቸውንና መጠነ ሰፊ የመብት ጥሰቶችን መፈጸማቸውን በሚመለከት ከመብት ተቋማት እና ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች የወጡ ሪፖርቶች አመልክተዋል። ጦርነቱ ባለፈው ዓመት ነሐሴ ላይ ዳግም ካገረሸ በኋላ የኤርትራ ሠራዊት ተሳታፊ መሆኑ በተደጋጋሚ ሲነገር የቆየ ቢሆንም፣ በደቡብ አፍሪካውም ሆነ በናይሮቢው ስምምነት ላይ በግልጽ አልተጠቀሰም። የኤርትራ መንግሥትም ሆነ የኢትዮጵያ መንግሥት ስለ ኤርትራ ሠራዊት በሚነሱ ጉዳዮች ላይ እስካሁን በይፋ የሰጡት ምላሽ የለም።

የኤርትራ ኃይሎች ሰላማዊ ሰዎችን እየገደሉና ንብረት እየዘረፉ መሆኑን የህወሓት ቃለ አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ ከሰሞኑ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር። በባለፈው ወር ጥቅምት 23/2015 ዓ.ም በፕሪቶሪያ የተደረሰውን ስምምነት የጠቀሰው ይህ መግለጫ ግጭት እንዲቆም እና ሕገ መንግሥቱ እንዲከበር እንዲሁም “በትግራይ መሬት ውስጥ” ያለው የኤርትራ ጦር እንዲወጣ ስምምነት ላይ ተደርሷል ብሏል። የትግራይ ኃይሎች ትጥቅ አፈታት ጋር ተያይዞ የናይሮቢው የትግበራ ስምምነት ሰነድ የውጭ ኃይሎች መውጣት እንዳለባቸው አስቀምጧል።

የትግራይ ኃይሎች የከባድ መሳሪያ ማውረድ የሚካሄደው የውጭ አገር እና የፌደራሉ መከላከያ ያልሆኑ የክልል ኃይላት ከክልሉ በተመሳሳይ ወቅት ሲወጡ ነው ብሏል። በዚህ የአፈጻጸም ሰነድ ላይ ከትግራይ ክልል ይወጣሉ የተባሉት የውጭ አገር እና የፌደራሉ መከላከያ ያልሆኑ የተባሉት የክልል ኃይሎች በስም አልተጠቀሱም። ከኢትዮጵያ መንግሥት አጋር በመሆን በጦርነቱ እየተሳተፈች ያለችው ጎረቤት አገር ኤርትራ የድርድሩ አካል አልነበረችም።

በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተደረሰው ግጭት የማቆም ስምምነት ኤርትራን በቀጥታ ያልጠቀሳት ሲሆን፣ ምዕራባውያን አገራትና ተቋማት ኤርትራ ጦሯን ከትግራይ በተደጋጋጋሚ እንድታስወጣም ሲጠይቁ ይሰማል። ከሰሞኑም ኤርትራ ሠራዊቷን ከትግራይ የማታስወጣ ከሆነ ማዕቀብ ሊጣልባት እንደሚችል የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ከፍተኛ ኃላፊ ተናግረዋል። ባለሥልጣኑ በአሁኑ ወቅት ከኤርትራ ጦር በተጨማሪ የአማራ ልዩ ኃይል እና የአፋር ሚሊሻ በትግራይ ይገኛሉ ያሉ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት እና ህወሓት የደረሱት የሰላም ስምምነት ኃይሎቹ እንዲወጡ የሚጠይቅ ነው ሲሉ አስታውሰዋል።

ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሃገራት በባይደን አስተዳደር ያለውን የአሜሪካ ስትራቴጂ በገመገመበት የምክር ቤት አባል ስብሰባም ኤርትራ የሰብዓዊ እርዳታን በማገድ፣ መድፈር፣ ህፃናትን መግደል ጨምሮ በርካታ ጥሰቶች እየፈጸሙ እንደሆነ ተገልጾ የኤርትራ ጦር መውጣት አለበት ተብሏል። የአሜሪካው የምክር ቤት አባል ብራድ ሸርማን “የኤርትራ ጦር በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል የሚሰማራበት ሕጋዊ ምክንያት የለም” ሲሉም ተደምጠዋል።

በዓለም ላይ ካሉ ደም አፋሳሽ ጦርነቶች አንዱ ሲሉ ገልጸው ኤርትራ ጦሯን እንደምታስወጣ ተስፋ ቢያደርጉም የስምምነቱ አካል አይደሉም ብለዋል። ሆኖም ኤርትራ ጦሯን ካላስወጣች በአገሪቷ እንዲሁም በፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ላይ የባይደን አስተዳደር ተጨማሪ ማዕቀብ እንዲጣል ጠይቀዋል። “ኤርትራ ጦሯን ካላስወጣች ተጨማሪ ማዕቀቦች መጣል አለበት፤ በፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ማዕቀብ መጣልን ጨምሮ የመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ኤርትራን የሚያወግዝ ውሳኔዎችን ማሳለፍ፣ የኤርትራን ዳያስፖራ ቀረጥ በአሜሪካ ውስጥ መሰብሰብን መመርመር እና አስፈላጊ ከሆነም በቅንጦት ዕቃዎች ላይ ‘የመርከብ ማጓጓዣ’ ላይ ገደቦችን መጣል ያስፈልጋል” ሲሉም ሸርማን ተናግረዋል።

ኤርትራ በኢትዮጵያ ላይ አሉታዊ ሚና አላት ሲሉ የተናገሩት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ረዳት ኃላፊ ሞ ሊፊ በበኩላቸው ኤርትራ ጦሯን ካላስወጣች በኤርትራ ላይ ማዕቀብ እንደሚጣል ተናግረዋል። ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች ካደረጉት ስምምነት ጋር ተያይዞ የውጭ ኃይሎችን ማስወጣት የስምምነቱ አካል ሆኖ መካተቱ አዎንታዊ ነው ብለዋል። በተጨማሪም ለሁለት ዓመታት ያህል የኢትዮጵያ መንግሥት ረሃብን እንደ ጦር መሳሪያ ተጠቅሞበታል ያሉት የምክር ቤት አባሉ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንን ስምምነት ተግባራዊ ካላደረገ እርምጃ ሊወሰድ ይገባል ብለዋል።

ኃላፊዋ በበኩላቸው ለኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት በፕሪቶሪያ የተደረሰውን ስምምነት እንዲሁም በናይሮቢ ላይ ያለውን የትግበራ ሰነድ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ማድረግ አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር የነበራትን የቀደመ አጋርነትና ግንኙነት ወደነበረው ለመመለስ እንደሚያስችል በግልፅ ነግረናቸዋል ብለዋል። ለትግራይ ያልተገደበ ዕርዳታ መግባት፣ ኢንተርኔትን ጨምሮ የተቋረጡ መሰረተ ልማቶች መመለስ፣ ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ የታሰሩ የትግራይ ተወላጆች ካልተፈቱ የባይደን አስተዳደር የኢትዮጵያን የአጎዋ ተጠቃሚነት እንዲሰርዝ፣ ዓለም አቀፍ ብድር እንዳይለቀቅም ጠይቀዋል።

ኃላፊዋ እነዚህን የስምምነቱ አካል የሆኑትን ሃሳቦች ተፈጻሚ መደረግ እንዳለባቸው ለኢትዮጵያ ባለሥልጣናት መናገራቸውን ጠቅሰዋል። በደቡብ አፍሪካ እና በኬንያ በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት ሲቪል እና ወታደራዊ አመራሮች የተፈረመው ስምምነት ግጭትን በዘላቂነት ማቆምን፣ ያልተገደበ እና ያልተቆራረጠ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦትን፣ ትጥቅ መፍታትን፣ እና የመሠረታዊ አገልሎቶች ወደነበሩበት መመለስን በዋናነት ይዟል።

ምንጭ – ቢቢሲ

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *