በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተደረሰው ግጭትን በዘላቂነት የማቆም ስምምነትን ተከትሎ በናይሮቢ ለቀናት የተካሄደው ውይይት ህዳር 3፣ 2015 ዓ.ም በፌደራሉ መከላከያ እና በትግራይ ኃይሎች መካከል የስምምነቱ የትግበራ ሰነድ በመፈረም ተጠናቋል። የፌደራል መንግሥቱ መከላከያ ሠራዊት ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እና የትግራይ ኃይሎች ዋና አዛዥ ጄኔራል ታደሰ ወረደ ጥቅምት 23 ላይ የተደረሰውን ጦርነት በዘላቂነት የማቆም ስምምነት ላይ ተወያይተው የተስማሙበትም ሰነድ ይፋ ሆኗል።

ውይይቱ በናይሮቢ፣ ካረን ሞራን ማዕከል ከሰኞ ጥቅምት 28፣ 2015 ዓ.ም ጀምሮ በዝግ የተካሄደ ሲሆን ውይይታቸው ለሶስት ቀናት ይይቆያል ተብሎ የነበረ ቢሆንም ለተጨማሪ ቀናት ተራዝሞ ህዳር 3፣ 2015 ዓ.ም ተጠናቋል። ይህ የትግበራ ሰነድ ስድስት ጉዳዮችን የጠቀሰ ሲሆን እነዚህም ግጭቶችን በዘላቂነት ማቆም፣ ትጥቅ ማስፈታት፣ ሰብዓዊ ረድዔት፣ ሰላማዊ ነዋሪዎችን መጠበቅ፣ ሚዲያን በኃላፊነት መጠቀም እና ክትትል እና ማረጋገጥ የሚሉ ይገኙበታል።

ይህንንም ስምምነት አስመልክቶ ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖችም ከናይሮቢ በሰጡት የጋራ መግለጫ ላይ “ሁለቱም አካላት በትግራይ እና በአጎራባች ክልሎች እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሁሉ ሰብአዊ እርዳታን ለማመቻቸት ተስማምተዋል” ብሏል። የኢትዮጵያ መንግሥትና ህወሃትን እያሸማገሉ ያሉት የኬንያ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በበኩላቸው መሰል አሰቃቂ ድርጊቶችን በሚፈጽሙ አካላት ላይ “ከባድ ማዕቀብ” እንደሚጣልባቸው በዚህ ወቅት አስጠንቅቀዋል።

 ነገር ግን ኡሁሩ እንዳሉት ቅድሚያ የሚሰጠው ጠመንጃን ጸጥ ማሰኘት፣ ለነዋሪዎች እርዳታ ማስገባት እና መስረታዊ አገልግሎቶችን ወደነበረበት መመለስ ነው ብለዋል። የትግራይ ኃይሎች ዋና አዛዥ ጄራል ታደሰ ወረደም “ባለፉት ሁለት አመታት ያልተነገረ ሰቆቃ ደርሶብናል አሁንም እየተሰቃየን ነው” “ስለዚህ ዛሬ እየገባን ያለነው ቁርጠኝነት የህዝባችን ስቃይ በቅርቡ እንደሚቆም ተስፋ በማድረግ ነው።” ብለዋል። ለመሆኑ የትግበራው ዝርዝር ሰነድ ምንን ይዟል?

ግጭቶችን በዘላቂነት ማቆም

 • ከማንኛውም ወታደራዊ ግጭቶች መታቀብና ማቆም
 • የዚህን ስምምነት አፈጻጸም አጠቃላይ ዓላማ ለማሳካት አስፈላጊ እርምጃዎች መወሰዱን ማረጋገጥ

የትግራይ ኃይሎችን ትጥቅ ማስፈታት

በፕሪቶሪያ ስምምነት አንቀጽ 6 መሰረት መሰረት ትጥቅ ማስፈታት ተፈጻሚ እንደሚሆን በሰነዱ ላይ ተጠቅሷል።

 • ከፍተኛ የሰራዊቶቹ አዛዦች ህዳር 6፣ 2015 ዓ.ም ወደ መደበኛ ቦታቸው ከደረሱ በኋላ ባሉት ሰባት ቀናት ለሰራዊት አባላቶቻቸው ገለጻ ያደርጋሉ።
 • ገለጻ በተደረገ በአራት ቀናት ውስጥ ወታደሮች ከጦርነት ቀጠና እንዲርቁ ያደርጋሉ።
 • ወታደሮች ከጦርነት ከራቁ በኋላ የፌደራል ባለስልጣናት በህገ መንግሥቱ መሰረት መሰረታዊ አገልግሎቶችን ጨምሮ የፌደራል ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ።
 • የትግራይ ኃይሎች የከባድ መሳሪያ ማውረድ የሚካሄደው የውጭ ሃገር እና የፌደራሉ መከላከያ ያልሆኑ የክልል ኃይላት ከክልሉ በተመሳሳይ ወቅት ሲወጡ ነው።
 • በዚህ ሰነድ በተፈረመበት ዕለትም የቀላል መሳሪያ ትጥቅ መፍታትን በተመለከተ ዝርዝር የአፈጻጸም ዕቅድ አውጥቶ በአስራ አራት ቀናት ውስጥ ሪፖርት የሚያቀርብ የጋራ ኮሚቴ እንደሚቋቋም ተጠቅሷል።
 • ኮሚቴው ከእያንዳንዱ ተፋላሚ ወገኖች ሁለት አባላትን፣ እንዲሁም ከአፍሪካ ህብረት የክትትልና ማረጋገጫ ቡድን አንድ ተወካይንም ያቀፈ ይሆናል።

በዚህ የአፈጻጸም ሰነድ ላይ ከትግራይ ክልል ይወጣሉ የተባሉት የውጭ ሃገርና የፌደራሉ መከላከያ ያልሆኑ የተባሉት የክልል ኃይሎች በስም አልተጠቀሱም። ከኢትዮጵያ መንግሥት አጋር በመሆን በጦርነቱ እየተዋጋች ያለችው ጎረቤት አገር ኤርትራ የድርድሩ አካል አልነበረችም። ያለፈው ሳምንቱ የግጭት ማቆም ስምምነት በቀጥታ ያልጠቀሳት ሲሆን ምዕራባውያን አገራትና ተቋማት ኤርትራ ጦሯን ከትግራይ በተደጋጋጋሚ እንድታስወጣም ሲጠይቁ ይሰማል።

የሰላማዊ ነዋሪዎች ጥበቃ

በስምምነቱ አንቀጽ 4 መሰረት በህገ መንግሥቱ መሰረት የፌደራል የጸጥታ አካላት እና የክልል የጸጥታ አካላት ሰላማዊ ዜጎችን የመጠበቅ ኃላፊነት እንዳላቸው ጠቅሶ በዚህ ረገድ ሁለቱ አካላት

 • በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት መከላከል
 • የዜጎችን ሰላማዊ እንቅስቃሴ ማረጋገጥ
 • የሲቪል ተቋማትን እና የመሰረተ ልማትን ደህንነት ማረጋገጥ
 • ሴቶችን እና ህጻናትን ጨምሮ የተጋላጭ ቡድኖችን ደህንነት ማረጋገጥ።
 • ሰላማዊ ዜጎችን ከፀጥታ ኃይሎች ከሚደርስ ጥቃት መከላከል
 • ተፋላሚ ወገኖች ይህንን የስምምነቱን አንቀጽ አራት ከጣሱ ጠንካራ ውግዘት እና የቅጣት እርምጃም እንደሚጠብቃቸውም ያትታል።

ሰብዓዊ ረድዔትን በተመለከተ

በፕሪቶሪያ አንቀጽ 5 መሰረት ተፋላሚ ወገኖች የተስማሙባቸው

 • ያልተገደበ ሰብዓዊ እርዳታ እንዲቀርብ ማመቻቸት
 • ሁሉም የሰብዓዊ እርዳታዎች በፌደራል መንግሥት ቁጥጥር እና እንዲሁም በማሳወቅ እንዲያልፉ
 • ለሰብዓዊ ረድዔት ሰራተኞች እና ድርጅቶች በጥያቄያቸው መሰረት መከላከያ የደህንነት ዋስትና እንዲሰጡ።
 • ሁለቱም ወገኖች የሰብዓዊ እርዳታ ሰራተኞች ያለምንም እንቅፋት እንዲንቀሳቀሱ ማመቻቸት ይጠበቅባቸዋል።
 • ሁለት የፍተሻ ጣቢያዎች ብቻ የሚኖሩ ሲሆን አንደኛው ከመነሻው ወይም ረድዔቱ ከሚጫንበት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በመድረሻ አካባቢዎች ላይ ይቋቋማል።

ክትትል እና ማረጋገጥ

ተፋላሚ ወገኖች በፕሪቶሪያ ስምምነት አንቀጽ 11 መሰረት በአፍሪካ ህብረት በከፍተኛ ደረጃ ፓነል ከሚቋቋመው የክትትልና ማረጋገጫ ቡድን ጋር ለመተባበር እንደተስማሙ ይጠቅሳል። የዚህ ቡድን መግለጫ እና  የማመሳከሪያ ውል ከተፋላሚ ወገኖች ጋር በመመካከር መዘጋጀት እንዳለበትም ይጠቁማል።

 • ቡድኑ ይህ መግለጫ ከተፈረመ በአስር ቀናት ውስጥ ሥራውን ይጀምራል።
 • ስምምነቱ ከተፈረመም በኋላ በአስር ቀናት ውስጥ በመከላከያ የደህንነት ዋስትና ሊሰጠው እንደሚገባም በሰነዱ ላይ ተቀምጧል።

ሚዲያን በኃላፊነት መጠቀም

ሌላቸው በዚህ ሰነድ ላይ የተቀመጠው የተፋላሚ ወገኖች በምን መልኩ ሚዲያን መጠቀም እንዳለባቸው የሚጠቅሰው ነው። ተፋላሚ ወገኖች በፕሮቶሪያ ስምምነት አንቀጽ 3 እና አንቀጽ 12 መሰረት የሚቆጣጠሯቸው ሚዲያዎች ገንቢ ሚና እንዲጫወቱና ይህን ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ የሚያግዝ መሆኑን ሊያረጋግጡ እንደሚገባም በግልጽ ያትታል። ይህ ውይይት በአፍሪካ ኅብረት ከፍተኛ ቡድን የናይጄሪያ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኦሉሴጎን አቦሳንጆ፣ የኬንያ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ፣ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን እና የኬንያ እና ደቡብ አፍሪካ ጄኔራሎች መርተውታል።

የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) በዚህ ውይይት ላይ የታዛቢነት ስፍራ እንዳለውም ተገልጿል። በስምምነቱ ላይ የታዛቢነት ድርሻ እንደነበራት የተገለጸው አሜሪካ በአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር የተወከለች ሲሆን፣ የፕሪቶሪያው ስምምነት እስኪተገበር ድረስ በቀጠናው እንደሚቆዩ እና ድጋፉም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃለ አቀባይ ኔድ ፕራይስ ከሰሞኑ ገልጸዋል።

ኔድ ፕራይስ ከሰሞኑ በስምምነቱ መሠረት የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦትን ማፋጠን እንዲሁም በትግራይና በአጎራባቾቹ የአፋር እና የአማራ ክልሎች ተቋርጠው የነበሩ መሠረታዊ አገልግሎቶችን መመለስ አንደኛው የናይሮቢ አጀንዳ እንደሆነ መጥቀሳቸው ይታወሳል። የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ህዳር 2፣ 2015 ዓ.ም  ባወጣው መግለጫ የሰላም ስምምነቱ በታቀደለት መንገድ እንዲፈጸም መንግሥት እየሠራ መሆኑን ገልጾ፤ ለዚህም በአገሪቱ መከላከያ ሠራዊት ስር ባሉ አብዛኞቹ የትግራይ አካባቢዎች እርዳታ እንዲደርስ እየተደረገ መሆኑንና መሠረታዊ አገልግሎቶች ቀስ በቀስ ሥራ እየጀመሩ ነው ብሏል።

የእርዳታ ድርጅቶች በበኩላቸው የእርዳታ ጭነቶች ወደ ጦርነት ቀጠና ለመግባት ፈቃድ እየተጠባበቁ እንዳሉ ተናግረዋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል ረሃብን እንደ ጦር መሳሪያ ይጠቀማል ሲል የሚወቅስ ሲሆን፣ በተጣለው እገዳ ምክንያት 90 በመቶ የሚሆነው የትግራል ክልል ሕዝብ አደጋ ላይ ወድቋል። የግጭት ማቆም ስምምነቱ ከተደረሰ በኋላ ምግብም ሆነ መድኃኒት እየገባ እንዳልሆነ የዓለም ጤና ድርጅት ገልጿል።

ዶክተር ቴድሮስ በክልሉ የተቋረጡት የቴሌኮም፣ የባንክና ሌሎች መሠረታዊ አገልግሎቶች እንዲመለሱም ጠይቀዋል። “ስድስት ሚሊዮን ሕዝቦች በሕይወት የሌሉ ይመስል ለሁለት ዓመታት ያህል ከዓለም ጋር እንዲቆራረጡ ተደርገዋል”  ብለዋል።  የኢትዮጵያ መንግሥት ዋና ተደራዳሪ አምባሳደር ሬድዋን ሑሴን የቴሌኮም፣ የመብራት እና የባንክ አገልግሎቶች በአፋጣኝ መጀመር አለብን ለዚህም ጥረት እየተደረገ ነው ማለታቸው ይታወሳል።

ከዚህ በፊት ግን “ሕዝባችን መጀመሪያ ምግብ እና መድኃኒት ያስፈልገዋል፣ እሱንም ለማድረግ እየሞከርን ነው” ብለዋል። “ምናልባት በዚህ ሳምንት መጨረሻ ወይም በሚቀጥለው ሳምንት አጋማሽ ላይ” ሰብዓዊ ዕርዳታ እንዲገባ ይፈቀዳል ሲሉ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ለጋዜጠኞች መናገራቸውን አሶሺየትድ ፕሬስ (ኤፒ) ዘግቧል።

ምንጭ – ቢቢሲ