የኢትዮጵያ መንግሥት እና የህወሓት ከፍተኛ የጦር አመራሮች በኬንያ መዲና ናይሮቢ ተገናኙ። የጦር አመራሮቹ የተገናኙት ከቀናት በፊት በሁለቱ ኃይሎች መካከል በፕሪቶርያ የተደረሰውን የሰላም ስምምነት የማስፈጸም አንዱ አካል በሆነው የትጥቅ ማስፈታት ሂደት ላይ ለመነጋገር ነው። የፌደራል መንግሥቱ መከላከያ ኃይል ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እና የትግራይ ኃይሎች ዋና አዛዥ ጄኔራል ታደሰ ወረደ ዛሬ ሰኞ ጥቅምት 28/2015 ዓ.ም. ረፋድ በናይሮቢ ንግግር መጀመራቸው ይፋ ተደርጓል።

ይህ ውይይት በቀጣይ ቀናት ቀጥሎ እንደሚካሄድ ተገልጿል። የንግግሩን መጀመር ይፋ በተደረገበት መድረክ በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር ድርድሩን ሲያስተባብሩ ከነበሩት መካከል የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሊሱንጉን ኦባሳንጆ እና የቀድሞ የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ተገኝተዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት እና ህወሓት ረቡዕ ጥቅምት 23/2015 ዓ.ም. በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በፈረሙት የሰላም ስምምነት መሠረት ህወሓት መሬት ላይ ያለው የደኅንነት ሁኔታ መሰረት ባደረገ መልኩ ትጥቁን ለመፍታት መስማማቱ ይታወሳል።

ሁለቱ አካላት በደረሱት የሰላም ስምምነት መሠረት ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ ባሉት አምስት ቀናት የሁለቱ አካላት ከፍተኛ የጦር አመራሮች በአካል ተገናኝተው ትጥቅ የማስፈታት ሂደትን በተመለከተ ይነጋገራሉ ይላል። ይህን ተከትሎም ስምምነቱ በተፈጸመ ዛሬ በአምስተኛ ቀኑ የፌደራል መንግሥቱን ጦር ወክለው ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እንዲሁም ህወሓትን ወክለው ጄኔራል ታደሰ ወረደ ለንግግር ናይሮቢ ኬንያ ተገናኝተዋል።

ሁለቱ የጦር መኮንኖች በተገኙበት መድረክ የንግግሩ መጀመር ይፋ ሲደረግ፤ የአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ኦሊሴንጉን ኦባሳንጆ በፕሪቶሪያ በነበረን የ10 ቀናት ቆይታ ተደራዳሪ አካላት ደከመን ሰለቸን ሳይሉ ከአምስት ቀናት በፊት የተፈረመው የሰላም ስምምነት ላይ ተደርሷል ብለዋል። የሁለቱ አካለት ከፍተኛ የጦር መኮንኖች በስምምነቱ መሠረት ለንግግር እዚህ መገኘታቸው የስምምነቱ ተፈጻሚነት አዎንታዊ አቅጣጫ ላይ እንዳለ የሚያሳያ ነው ብለዋል ኦባሳንጆ።

ኡሁሩ ኬንያታ በበኩላቸው በጉዳዩ ለመነጋገር እዚህ የተገኙት ሁለቱ ግለሰቦች ከዚህ ቀደም አብረው የሰሩ ትውውቅ ያላቸው የሥራ ባልደረቦች ናቸው ካሉ በኋላ፤ በሂደቱ መጨረሻም ለተሻለች ኢትዮጵያ እና ለቀጠናው ጥቅም አዎንታዊ ውጤት ያስመዘግባሉ የሚል እምነት አለኝ ብለዋል።

“በፕሪቶሪያ ጀምርን (የሰላም ንግግሩን) አሁን አንድ ስንዝር ተቃርበን ናይሮቢ ላይ እንገኛለን፤ በቀጣይ ደግሞ በመቀለ እንደሚሆን ብዙ ተስፋ አለን። ከዚያም በመጨረሻ በአዲስ አበባ ላይ እናከብረዋለን። ይህ ጸሎታችን እና ተስፋችን ነው” ብለዋል የቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ።

ትጥቅ ማስፈታት ስምምነት

በስምምነቱ ላይ ዋነኛ ጉዳይ የሆነውን ትጥቅ ማስፈታትን በተመለከተ ሁለቱም ወገኖች በኢትዮጵያ ውስጥ አንድ የመከላከያ ኃይል ብቻ እንዳለ ከስምምነት ደርሰዋል። በስምምነቱ መሰረት የሰላም ስምምነቱ በተፈረም በ24 ሰዓታት ውስጥ የሁለቱ ወገኖች ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ግንኙነት ይፈጥራሉ። መንግሥት እና ህወሓት የፈረሙት የፕሪቶሪያው ስምምነት የሁለቱ አካላት ከፍተኛ የጦር መኮንኖች በአካል ተገናኝተው ትጥቅ የማስፈታቱን ሂደት ዝርዝር ካወጡ በኋላ ባሉት አስር ቀናት ውስጥ ከባድ መሳሪያ ትጥቅ የመፍታቱ ሂደት ይጠናቀቃል ይላል።

 ይሁን እንጂ የተቀመጠው አስር ቀናት ጊዜ ገደብ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች በሚሰጡት ሀሳብ እና በሁለቱ ወገኖች አጽዳቂነት ሊራዘም ይችላል።  ከዚህ ስምምነት በኋላ ባሉት 30 ቀናት ቀላል የጦር መሳርያዎችን ጨምሮ ትጥቅ የመፍታት ሂደቱ ሙሉ ሙሉ ይጠናቀቃል።

ምንጭ – ቢቢሲ

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *