በደቡብ አፍሪካ ውስጥ በኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት እና በህወሓት መሪዎች መካከል ሲካሄድ በነበረው ድርድር ላይ የህወሓት ኃይሎች ትጥቅ እንዲፈቱ ከስምምነት ላይ ተደረሰ። ለአስር ቀናት ያህል ሲካሄድ በቆየው ድርድር ማብቂያ ላይ በተፈረመው ባለ 12 ነጥብ ስምምነት ላይ በአገሪቱ መኖር ያለበት የጦር ኃይል አንድ መሆን እንዳለበት ከስምምነት ላይ በመደረሱ ነው የህወሓት ኃይሎች ትጥቅ እንዲፈቱ የተስማሙት። በስምምነቱ መሠረት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ለማረጋገጥ እና የኢፌደሪ ሕገ-መንግሥቱን ለማስከበር ሁለቱ ወገኖች የተስማሙ ሲሆን፤ ይህም “ኢትዮጵያ አንድ ብሔራዊ መከላከያ ኃይል ብቻ አላት” በሚለው ተስማምተናል ብለዋል።

“በመሬት ላይ ያለውን የፀጥታ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት የህወሓት ተዋጊዎችን ትጥቅት ለማስፈታት፣ ተዋጊዎችን ከሠራዊቱ እንዲወጡ ለማድረግ እና መልሶ ወደ ማኅበረሰቡ ለመቀላቀል” ዝርዝር ፕሮግራሞች ላይ ተስማምተና ብለዋል የፌደራል መንግሥቱ እና ህወሓት። ሁለት ዓመት የዘለቀውን ደም አፋሻሽ ጦርነት ለማብቃት በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት መሪዎች መካከል በተደረሰው ስምምነት “የጥይት ድምጽ በዘላቂነት እንዳይሰማ” በመስማማት፣ ጦርነቱ እንዲያበቃ የሚያስችል ዘላቂ የግጭት ማስወገድ ስምምነት ተፈርሟል። ፖለቲካዊ ልዩነቶችን ለመፍታት በትግራይ ክልል ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት እንዲሰፍንና ከዚህ በተጨማሪም በግጭቱ የወደሙ መሠረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት ሁለቱ ወገኖች መስማማታቸው ተገልጿል።

ስምምነቱ ይፋ በተደረገበት ሥነ ሥርዓት ላይ የኢትዮጵያ መንግሥትን በመወከል የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፣ ከህወሓት በኩል ደግሞ የቡድኑ ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ ፊርማቸውን አኑረዋል። በአፍሪካ ኅብረት መሪነት ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ከአንድ ሳምንት በላይ ሲካሄድ የነበረው ድርድር ሲያበቃ ነው ሁለቱ ወገኖች እየተካሄደ ያለውን ግጭት በዘላቂነት ለማቆም ከስምምነት የደረሱት። ሁለት ዓመት የሞላው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ከተጀመረ በኋላ የኢትዮጵያ መንግሥትን እና የህወሓት መሪዎችን ወደ ድርድር ጠረጴዛው ለማምጣት አዳጋች ሆኖ ቆይቶ ነበር።

ከፍተኛ ውድመትና ደም መፋሰስን ለማስቆም በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ውስጥ ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች ለይፋዊ ንግግር የተቀመጡት ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሆን፣ በዚህም ሲጠበቅ ከነበረው ስምምነት ላይ መድረሳቸው ይፋ ሆኗል።

ድርድር

በሰሜን ኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነት ለሁለት ዓመታት ሲፋለሙ የቆዩት ሁለቱ ኃይሎች ግጭት ለማቆም ፣ የተስማሙ ሲሆን፤ የሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ እና የሰላማዊ ዜጎችን ደኅንነት ማረጋጋጥ በሚሉት ጉዳዮች ላይ ከስምምነት ደርሰዋል። ሁለቱ ኃይሎች ከዚህ ስምምነት መድረሳቸውን ያስታወቁት በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ሥር ድርድሩን ሲያስተባብሩ ከነበሩት መካከል አንዱ የሆኑት የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጎን ኦባሳንጆ ናቸው። በመግለጫው ላይ ድርድሩን ሲያስተባብሩ ከነበሩት ከቀድሞ የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንታ እና ከቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት በተጨማሪ የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር ተገኝተዋል።

ሁለቱ አካላት በአስቸኳይ ግጭት እንዲቆም መስማማታቸው በደም አፋሳሹ ጦርነት የሚጠፋውን ሕይወት ከመታደጉም በላይ በግጭት ምክንያት ከሰብዓዊ እርዳታ ርቀው ለረሃብ አደጋ ለተጋለጡት እርዳታ ማድረስ ያስችላል። ከማክሰኞ ጥቅምት 15/2015 ዓ.ም ጀምሮ በፌደራል መንግሥቱ እና በትግራይ ኃይሎች መከካከል ሲካሄድ የቆየውን የሰላም ንግግር በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሲጎን ኦባሳንጆ፣ የቀድሞ የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እና የቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ፑምዚሌ ማላምቦ-ናኩክ ሲያስተባብሩት ነበር።

አሜሪካ፣ የተባበሩት መንግሥታት እና የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግሥታት (ኢጋድ) ደግሞ በድርድሩ ላይ የታዛቢነት ሚና ኖሯቸው ተሳታፊ ሆነው ቆይተዋል። ነገ ሐሙስ ጥቅምት 24/2015 ዓ.ም. ሁለተኛ ዓመቱን የሚደፍነው ጦርነትን ለማብቃት ዘላቂ የግጭት ማስወገድ ስምምነት በዋናነት የተፈረመ ሲሆን ዝርዝር ሁኔታዎች በቀጣይ የሚታወቁ ይሆናል።

ምንጭ – ቢቢሲ