ትናንት፣ ረቡዕ ጥቅምት 23 2015 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ፣ በኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት እና በህወሓት መሪዎች መካከል ሲካሄድ የነበረው ድርድር ተጠናቅቆ ከስምምነት ላይ ተደርሷል። የፌደራሉ መንግሥት እና ህወሓት የደረሱት ስምምነት በደም አፋሳሹ ጦርነት የሚጠፋውን ሕይወት መታደግ የሚያስችል ከመሆኑም በተጨማሪ በግጭት ምክንያት ከሰብዓዊ እርዳታ ርቀው ለረሃብ አደጋ ለተጋለጡት እርዳታ ማድረስ ያስችላል።

ለአስር ቀናት ያህል ሲካሄድ በቆየው ድርድር ማብቂያ ላይ በተፈረመው ባለ 12 ነጥብ ስምምነት ጠቅለል ተደርጎ ሲታይ ሦስት መሠረታዊ ጉዳዮችን ይዟል። እነዚህም በዘላቂነት ግጭት ማቆም፣ የህወሃት ታጣቂዎችን ትጥቅ ማስፈታት እና የሰብዓዊ እርዳታ ማድረስ ናቸው።

ግጭት ማስቆም

ሁለቱ አካላት በደቡብ አፍሪካ ለ10 ቀናት ከመከሩ በኋላ በዘላቂ ግጭት ለማቆም መስማማታችንን የኢትዮጵያ ሕዝብ እና ዓለም ይወቅልን ብለዋል። “በዘላቂነት የጦር መሳሪያ ድምጽ እንዳይሰማ ለማድረግ እና በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመት የዘለቀው ግጭት እንዲቆም ተስማምተናል” ብለዋል ሁለቱ አካላት። ህወሓት እና መንግሥት በአንድ ድምጽ ግጭቱ ከፍተኛ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ኪሰራዎችን አስከትሏል ካሉ በኋላ፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ ጥቅም ከግምት በማስገባት ግጭቱን ምዕራፍ ከኋላችን ትተን “በሰላም እና በመቻቻል ለመኖር” ተስማምተናል ብለዋል።

ትጥቅ ማስፈታት

የኢትዮጵን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ማረጋገጥ እና መጠበቅ መሠረታዊ ጉዳይ ነው ያሉት ህወሓት እና ኢትዮጵያ መንግሥት፤ የኢፌድሪ ሕገ-መንግሥትን ለማስከበር ተስማምተዋል። በስምምነታቸው መሠረት ‘ኢትዮጵያ አንድ የአገር መከላከያ ሠራዊት ብቻ ነው ያላት’ በሚለው ጉዳይ ተስማምተዋል። “መሬት ላይ ያለውን የጸጥታ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት የህወሓት ተዋጊዎች ትጥቅ የሚፈቱበት፣ የሚበተኑበት እና ወደ ማሕበረሰቡ ተመልሰው የሚቀላቀሉበት ዝርዝር ፕሮግራም ላይ ተስማምተናል” ብለዋል።

የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት

የኢትዮጵያ መንግሥት ከሰብዓዊ ድርጅቶች ጋር በመሆን የሰብዓዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው የተፋጠነ እርዳታ እንዲያደርስ ከመግባባት ላይ ተደርሷል።   የኢትዮጵያ መንግሥት መሠረታዊ አገልግሎቶችን ለመጀመር ጥረቱን ለመቀጠል እና በግጭቱ የወደሙ መሠረተ ልማቶችን መልሶ ለመጠገን ከስምምነት ደርሰዋል። የዚህ ስምምነት ተፈጻሚነት የሕዝብ ድጋፍን የሚፈልግ መሆኑ ተወስቷል።

በትግራይ ክልል ሕገ-መንግሥታዊ ሰርዓት የሚሰፍነበት እርምጃዎች፣ ፖለቲካዊ ልዩነትን የሚፈታ ማዕቀፍ እና ተጠያቂነትን፣ እውነትን፣ እርቅ የሚያመጣ የፍትሕ የሽግግር ስርዓት ፖሊስ ማዕቀፍ ለማረጋገጥ ተስማምተዋል። ከላይ የተጠቀሱትን ተግባራዊ ለማድረግ ሁለቱ አካላት የትኛውንም አይነት ግጭት ለማቆም፣ ግጭት ቀስቃሽ ከሆኑ ፕሮፖጋንዳዎች ለመታቀብ ተስማምተዋል።

ሁለቱ አካላት የሚያወጧቸው መግለጫዎች ይህን ስምምነት የሚደግፉ ብቻ እንዲሆኑ ተስማምተዋል። በኢትዮጵያ እና ከኢትዮጵያ ውጭ ያሉ ዜጎች ይህን ስምምነት እንዲደግፉ፤ ከፋፋይ እና ጥላቻ ከሚነዙ አስተያየቶች እንዲቆጠቡ እና ለመልሶ ግንባታ የሚውሉ ሃብት እንዲያሰባስቡ ተጠይቀዋል። “ይህ በአገሪቱ ታሪክ አዲስ እና ተስፋ የተጣለበት ምዕራፍ ነው” ብለዋል ሁለቱ አካላት።

 

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *