በሰሜን ኢትዮጵያ የሚካሄደውን ጦርነት ለማብቃት በፌደራል መንግሥቱ እና በትግራይ ኃይሎች መካከል በቀጠለው ንግግር ውስጥ “ከባድ የውጪ ጣልቃ ገብነት” እንዳለ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ተናገሩ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሲጂቲኤን ለተባለው የቻይና ዓለም አቀፍ ቴሌቪዥን እንደተናገሩት፣ በቀጠለው ንግግር ውስጥ የውጪ ጣልቃ ገብነት ቢኖርም የሰላም ስምምነት እንደሚደረስ ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል። በዚህ ሳምንት ውስጥ ከተጀመረ ሁለተኛ ዓመቱን የሚደፍነው የሰሜን ኢትዮጵያውን ጦርነት ለማብቃት በፌደራል መንግሥቱ እና በትግራይ ኃይሎች መካከል ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ንግግር እየተካሄደ ይገኛል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለቻይናው ቴሌቪዥን እንደተናገሩት ምንም እንኳን የተኩስ አቁም እንዲደረግ ዓለም አቀፍ ግፊት እየተደረገ ቢሆንም ኢትዮጵያውያን ለችግሮቻቸው እራሳቸው መፍትሔ መስጠት ይችላሉ ብለዋል። “በእርግጥ ከግራም ሆነ ከቀኝም በርካታ ጣልቃ ገብነቶች የሚኖሩ ከሆነ፣ በጣም አስቸጋሪ ይሆናል” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ። ጨምረውም “ኢትዮጵያውያን ችግሮቻችንን በእራሳችን መፍታት እንደምንችል ሊገነዘቡ ይገባል” ብለዋል።

በጦርነቱ ከባድ ሰብአዊ እና ቁሳዊ ውድመት እንደደረሰ ከሁሉም ወገን የተነገረ ሲሆን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ደግሞ ሰብአዊ እርዳታ ጠባቂ ሆነዋል።  ባለፈው ዓመት ለአምስት ወራት የቆየው የተኩስ አቁም ስምምነት ከተጣሰ በኋላ በትግራይ ክልል ውስጥ ውጊያዎች ሲካሄዱ እንደቆዩ ተዘግቧል። ይህንንም ተከትሎ በአፍሪካ ኅብረት አማካይነት ሁለቱም ወገኖች ለሰላም ድርድር እንዲቀመጡ እና ደም አፋሳሹን ጦርነት በውይይት እንዲያበቁት ጥረት እየተደረገ ነው። ለዚህም ሁለቱም ወገኖች በአህጉራዊው ድርጅት አሸማጋይነት ለመነጋገር ተስማምተው ከአንድ ሳምንት በፊት በከፍተኛ ተወካዮቻቸው አማካይነት ፕሪቶሪያ ውስጥ እየተነጋገሩ ይገኛሉ።

የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት ከሳምንታት በፊት ሽረ፣ አክሱም እና አድዋን ከትግራይ ኃይሎች ቁጥጥር ስር ማስለቀቁን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል። “ህወሓቶች የአገሪቱን ሕግ እንዲያከብሩ፣ ሕገ መንግሥቱንም እንዲያከብሩ እና እንደ ኢትዮጵያ አንድ ክልል እንዲንቀሳቀሱ ለማሳመን እየሞከርን ነው” ብለዋል። ባለፈው ሳምንት ማከሰኞ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ተጀምሮ እሁድ እለት ያበቃል የተባለው ንግግር ለተጨማሪ ቀናት ቀጥሎ ዛሬም እየተካሄደ ይገኛል። በዝግ እየተካሄደ የሚገኘው በመንግሥትና በትግራይ አመራሮች መካከል የሚካሄደው ንግግር በቀዳሚነት ጦርነቱን የሚያስቆም የተኩስ አቁም እንዲደረግ ያስችላል ተብሎ ይጠበቃል።

በሁለቱም በኩል በተወከሉ ከፍተኛ አመራሮች መካከል የሚደረገውን ንግግር የአፍሪካ ኅብረት ከፍተኛ ተወካይ ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ፣ የቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እና የደቡብ አፍሪካ የቀድሞ ምክትል ፕሬዝዳንት  ፑምዚሌ ማላምቦ-ናኩክ በአሸማጋይነት እየመሩት ነው። በተጨማሪም የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ)፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የአሜሪካ መንግሥት በታዛቢነት ተሳታፊ ናቸው።    አስከ እሁድ ይጠናቀቃል የተባለው ንግግር አስከ ነገ ረቡዕ ድረስ እንደሚቆይ የተነገረ ሲሆን፣ አስካሁን ስላለው ሂደት ከየትኛውም ወገን የወጣ መረጃ የለም።

የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር የሆኑት የሙሳ ፋኪ ማሐማት ቃል አቀባይ ትናንት ሰኞ ዕለት ለፈረንሳይ ዜና ወኪል – ኤኤፍፒ እንደተናገሩት በንግግሩ ሂደት “የተቀመጠ ቀነ ገደብ የለም” ብለዋል። በመንግሥት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል በሚደረገው ንግግር ላይ አንደኛው ወገን ከሌላኛው እንዲደረግ የጠየቀው ምን እንደሆነ አስካሁን በይፋ የታወቀ ነገር የለም። በሁለቱ ወገኖች መካከል እየተደረገ ያለው ንግግር ካበቃ በኋላ ስለሂደቱ እና ስለተገኘው ውጤት የጋራ መግለጫ እንደሚወጣ ይጠበቃል።

ሐሙስ ጥቅምት 24/2015 ዓ.ም. ሁለት ዓመት የሚሆነው ጦርነት ትግራይ ውስጥ ተቀስቅሶ ወደ አጎራባቾቹ የአፋርና የአማራ ክልሎች ተዛምቶ ነበር። ጦርነቱ በትግራይ፣ በአማራ እና በአፋር ክልሎች ውስጥ ከፍተኛ ውድመትን ከማስከተሉ ባሻገር በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለመፈናቀል እና ለእርዳታ ጠባቂነት ዳርጓል።

ምንጭ – ቢቢሲ

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *