በኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ሲካሄድ የቆየው የሰላም ንግግር ለተጨማሪ ቀናት መራዘሙን ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ምንጭ ለቢቢሲ ገለጹ። በደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ውስጥ እየተካሄደ የሚገኘው ንግግር ለሦስት ተጨማሪ ቀናት መራዘሙን እና ረቡዕ ዕለት ሊጠናቀቅ እንደሚችል ቢቢሲ ያገኘው መረጃ አመልክቷል። ሁለት ዓመት የሆነውን የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነት ለማስቆም በአፍሪካ ኅብረት አማካይነት ደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ውስጥ ይፋዊ ድርድር እየተደረገ ይገኛል።ማክሰኞ ጥቅምት 15 የጀመረው የሰላም ንግግር ትናንት እሁድ ጥቅምት 20/2015 ዓ.ም. ይጠናቀቀል ተብሎ የተጠበቀ ቢሆንም፣ ውይይቱ በታቀደለት ጊዜ ባለመጠናቀቁ ንግግሩ ለተጨማሪ ቀናት እንደሚቀጥል ቢቢሲ አረጋግጧል።

ቢቢሲ ያናገራቸውና ንግግሩን በቅረብት የሚከታተሉት ምንጭ በሁለቱ ወገኖች መካከል አስካሁን በተደረገው ንግግር የተነሱ ጉዳዮችን ከመግለጽ ተቆጥበዋል። ነገር ግን በመካሄድ ላይ ያለው ድርድር ረቡዕ ዕለት የሚጠናቀቅ ከሆነ፣ ስለተካሄደው ንግግር ሂደት እና ውጤቱ የጋራ መግለጫ እንደሚወጣ ዲፕሎማቱ ለቢቢሲ ገልጸዋል። በደቡብ አፍሪካዋ ፕሪቶሪያ ከተማ በሚገኘው የአገሪቱ የዓለም አቀፍ ግንኙነት እና ትብብር መሥሪያ ቤት (የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት) ውስጥ እየተካሄደ ባለው ንግግር፣ ከሁለቱም ወገን ከፍተኛ ተወካዮች እየተሳተፉ ነው።

ሁለቱ ኃይሎች ልዩነቶቻቸውን በንግግር ለመፍታት በዝግ ስብሰባቸውን እያደረጉ ይገኛሉ። እስካሁን የድርድሩ አጀንዳዎችም ሆነ የሰላም ንግግሩ ሂደት የደረሰበት ደረጃ ምን እንደሆነ አይታወቅም። ይሁን እንጂ ምዕራባውያን እና የሰላም ንግግሩን በበላይነት የሚመራው የአፍሪካ ኅብረት ውይይቱ ደም አፋሳሽ ጦርነቱን ያስቆማል የሚል እምነት እንዳላቸው ከዚህ ቀደም ገልጸዋል። የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ መሐማት የድርድሩ መጀመርን ይፋ ባደረጉበት መግለጫ፤ የተኩስ ድምጽ እንዳይሰማ፣ የተባበረች፣ የተረጋጋች እና ሰላማዊ ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የአፍሪካ ኅብረት “በኢትዮጵያውን ባለቤትነት እና በአፍሪካ ኅብረት መሪነት” የሚካሄድ የሰላም ንግግር እንዲኖር ድጋፉን ለማድረግ ቁርጠኛ ነው ብለው ነበር።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን በበኩላቸው ይህ የሰላም ድርድር “ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ዘላቂ የሆነ ሰላም ለማምጣት ተስፋ ሰጪ መንገድ መሆኑን” ገልጸው ለግጭቱ የመጨረሻ እልባት ለማግኘት በዚህ ድርድር የተሳተፉ ተደራዳሪ ልዑካን በጉዳዩ ላይ ትኩረት ሰጥተው እንዲነጋገሩም አሳስበዋል። የፌደራል መንግሥቱ እና የትግራይ ኃይሎች የሚያደርጉትን ድርድር በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሊሴንጉን ኦባሳንጆ፣ የቀድሞ የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እና የቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ፑምዚሌ ማላምቦ-ናኩክ እንደሚያስተባብሩት ከዚህ ቀደም ተገልጿል። አሜሪካ፣ የተባበሩት መንግሥታት እና የምስራቅ አፍሪካ በየነ መንግሥታት (ኢጋድ) ደግሞ በድርድሩ ላይ የታዛቢነት ሚና ኖሯቸው ተሳታፊ እንደሚሆኑ የአፍሪካ ኅብረት አስታውቋል።

የንግግር አጀንዳዎች

የአፍሪካ ኅብረት ተፋላሚ ኃይሎች ግጭት አቁመው ልዩነቶቻቸው በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲፈቱ ተደጋጋሚ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል። ሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎች ሊደራደሩባቸው የሚችሏቸውን ጉዳዮች በይፋ ባይገልጹም፤ የአፍሪካ ኅብረት እና ምዕራባውያን ግን ለግጭቱ ፖለቲካዊ መፍትሄ ለመስጠት ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል። በትግራይ ኃይሎች በኩል ከፌደራል መንግሥቱ ጋር በሚደረገው ውይይት በዋናነት ግጭት በአስቸኳይ እንዲቆም፣ ያልተገደበ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት እንዲኖር እና የኤርትራ ኃይሎች ከትግራይ እንዲወጡ ማድረግ በቀዳሚነት ተጠቅሰዋል።

የፌደራል መንግሥት ግን ከዚህ ቀደም “ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ” ለንግግር ዝግጁ መሆኑን ሲገልጽ ቆይቷል።  የፌደራል መንግሥቱ እና የትግራይ ኃይሎች በደቡብ አፍሪካ ለንግግር የተቀመጡት በትግራይ የሚካሄደው ጦርነት ተጠናክሮ በቀጠለበት ወቅት ነው። ባለፉት ቀናት የፌደራሉ መንግሥት ጥምር ኃይሎች በርካታ ከተማዎችን እና የትግራይ አካባቢዎችን ከትግራይ ኃይሎች አስለቅቆ መቆጣጠሩ ተገልጿል።

ምንጭ – ቢቢሲ

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *