ለሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት ሰላማዊ መፍትሔ ለማምጣት በአፍሪካ ኅብረት አማካይነት በደቡብ አፍሪካ በተጀመረው የሰላም ንግግር የአሜሪካ መንግሥት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) እና የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) በታዛቢነት እየተሳተፉ መሆኑ ተገለጸ።ቭድርድሩ ማክሰኞ ጥቅምት 15 ቀን 2015 ዓ.ም. በኢትዮጵያ የፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት ተወካዮች መካከል የተጀመረ ሲሆን፣ ሁለቱ ወገኖች ለመጀመሪያ ጊዜ ቀጥተኛ በደቡብ አፍሪካ መጀመራቸው እንዳስደሰታቸው የወቅቱ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ ማሃመት መጀመሩን አስመልክቶ ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

በኢትዮጵያ በትግራይ ክልል ለተፈጠረው ግጭት ሁለቱ ወገኖች ፖለቲካዊ መፍትሔ እንዲያመጡም ጠይቀዋል፡፡ የሰላም ንግግሩን የአፍሪካ ቀንድ የአፍሪካ ኅብረት ከፍተኛ ተወካይና የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ፣ ከቀድሞው የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታና ከደቡብ አፍሪካ የቀድሞ ምክትል ፕሬዚዳንት ፉምዚል ምላምቦ ንግኩካ (ዶ/ር) ጋር እንደሚመሩትም አስታውቀዋል። የሰላም ንግግሩ በኢትዮጵያውያን ባለቤትነት የጥይት ድምፅን በማስቆም የተረጋጋች የአፍሪካ አኅጉርን ዕውን ማድረግ በሚለው የአፍሪካ ኅብረት መርህ መሠረት እንደሚካሄድ የጠቆሙት ሊቀመንበሩ፣ በዚህም መሠረት የአፍሪካ ኅብረት የተባበረች፣ የተረጋጋች፣ ሰላማዊና የማትበገር ኢትዮጵያን የመፍጠር ሒደትን በቁርጠኝነት እንደሚደግፍ ገልጸዋል።

በተጀመረው ንግግርም ሁለቱም ወገኖች በትግራይ ክልል ለተፈጠረው ግጭት ፖለቲካዊ መፍትሔ እንዲያመጡ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። በተያየዘ ዜና በመከላከያ ሠራዊት በቁጥጥር ሥር በዋሉ የትግራይ አካባቢዎች የሕዝብ አስተዳደር ለመመሥረት፣ ከአካቢቢው ነዋሪዎች ጋር ምክክር መጀመሩን የኢትዮጵያ መንግሥት አስታውቋል። በእንግሊዝ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ይፋ ባደረገው መረጃ እንዳስታወቀው፣ የአገር መከላከያ ሠራዊት ቁጥጥር ሥር በገቡ የትግራይ አካባቢዎች የሕዝብ አስተዳደር መመሥረትን ጨምሮ የተቋረጡ ማኅበራዊ አገልግሎቶችን ለመጀመር የሚያስችሉ መንገዶችን ለመፈለግ ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር ምክክር እየተካሄደ ነው።

ኤምባሲው አክሎ የኢትዮጵያ መንግሥት ከሰብዓዊ ዕርዳታ ድርጅቶች ጋር በመተባበር መከላከያ ሠራዊቱ በተቆጣጠራቸው አካባቢዎች ለሚኖሩ ዜጎች ሰብዓዊ ዕርዳታ ማድረስ እንደጀመረ፣ ይህንንም ተግባር አጠናክሮ ቀጥሏል ብሏል፡፡ መንግሥት ባለፈው ሳምንት በመከላከያ ሠራዊቱ ቁጥጥር ሥር ውለዋል ብሎ ያሳወቃቸው ከተሞች፣ ሽሬ፣ አላማጣና ኮረም ሲሆኑ፣ በዚህም ሳምንት ደግሞ አክሱም፣ አድዋና አዲግራት ከተሞች በመከላከያ ሠራዊት ቁጥጥር ሥር እንደዋሉ እየተነገረ ነው።

ኒውዮርክ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ ታዬ አጽቀ ሥላሴ (አምባሳደር) ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ፣ ባለፈው ዓርብ በሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት ዙሪያ በዝግ በተካሄደው የተመድ የፀጥታ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥትን አቋም ማስረዳታቸውን ተናግረዋል። ስብሰባው በተካሄደበት ወቅትም የፀጥታ ምክር ቤቱ አባላትም ሆኑ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ በአጠቃላይ የሰሜን ኢትዮጵያን ጉዳይ በመርህ ላይ ተመሠረተው እንዲመለከቱ ማሳሰባቸውን ገለጸዋል። በዚህም አግባብ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በየትኛውም የአገሪቱ አካባቢ የመግባትና የመንቀሳቀስ ሕገ መንግሥታዊ መብት እንዳለው ለምክር ቤቱ ማስገንዘባቸውን ጠቁመዋል።

ምንጭ – ሪፖርተር
selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *