የአፍሪካ ኅብረት የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በአስቸኳይ ቆሞ የሰብዓዊ እርዳታ እንዲቀርብ ያቀረበው ጥሪ ተፈጻሚ እንደሆን የትግራይ ኃይሎች ጠየቁ። ትግራይን እያስተዳደሩ የሚገኙት የትግራይ ኃይሎች ትናንት ጥቅምት 5/2015 ዓ.ም. ባወጡት መግለጫ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሙሳ ፋኪ መሐመት ያወጡትን መግለጫ በበጎ ጎኑ እንቀበለዋለን ብለዋል። ኮሚሽነር ሙሳ ፋኪ ከትናንት በስቲያ ቅዳሜ ጥቅምት 4/2015 ዓ.ም. ባወጡት መግለጫ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ጦርነት ተባብሶ መቀጠሉን የሚገልጹ ሪፖርቶች እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል።
ኮሚሽነር ሙሳ ፋኪ መሐመት በአስቸኳይ ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ ተኩስ ቆሞ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት እንዲጀመር በአጽንኦት ጠይቀዋል። ይህ የኮሚሽነሩ ጥሪ የተሰማው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና አሜሪካን ጨምሮ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ድርጅት ተቋማት የግጭት መባባስ እንዳሳሰባቸው በመግለጽ ጦርነት እንዲቆም ጥሪ ባስተላለፉበት ወቅት ነው። የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ተሳታፊ የሆኑ ኃይሎች ግጭቱን ከሚያባብሱ ድርጊቶችን እንዲቆጠቡ ጥሪ አቅርበው ነበር።
አንቶኒ ብሊንከን በትዊተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መንግሥታት በትግራይ ውስጥ የሚያካሂዱትን “የጋራ ወታደራዊ ጥቃት” እንዲያቆሙ ጠይቀዋል። በተጨማሪም በትግራይ ኃይሎች በኩልም “የጠብ አጫሪነት ተግባራትን” የክልሉ ባለሥልጣናት ከመፈጸም እንዲቆጠቡ የውጭ ጉዳይ ኃላፊው አሳስበዋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ጦርነቱ መባባሱን በማስመልከት የተፈጠረባቸው “ከባድ ስጋት” ከገለጹ በኋላ ጦርነቱ እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።
የአሜሪካ መንግሥት ተራድኦ ድርጅት ኃላፊ ሳማንታ ፓዎር በበኩላቸው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት መስፋፋት እጅጉን አሳሳቢ ነው ብለዋል። ሳማንታ በትዊተር ገጻቸው ባለፉት ቀናት በትግራይዋ ሽረ ከተማ ተፈጽመዋል የተባሉት የአየር ጥቃቶች እጅጉን አሳሳቢ ናቸው ብለዋል። የዩኤስኤይድ ዋና አስተዳዳሪ የኤርትራ ጦር በቅርብ ቀናት አካባቢዎቹን ሊቆጣጠር ይችላል የሚለው ሪፖርት እጅጉን አሳሳቢ ነው ብለዋል። ባለፉት ቀናት በሽረ ከተማ ላይ በተፈጸመ የአየር ጥቃት አንድ የረድዔት ሰራተኛው መገደሉን ዓለም አቀፉ የነፍስ አድን ቡድን (ኢንተርናሽናል ሬስኪው ኮሚቴ) መግለጹ ይታወሳል።
ተቋሙ በአየር ጥቃት የረድዔት ሰራተኛውን ጨምሮ ሶስት ሰዎች መገደላቸውንም ቅዳሜ ጥቅምት 5/2015 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። የጤናና የስነ ምግብ ቡድን አባል የሆኑት የረድዔት ሰራተኛው ለሴቶች እና ህጻናት እርዳታ እያቀረቡ ባለበት ወቅት በተፈጸመ ጥቃት ከቆሰሉ በኋላ ህይወታቸው አርብ ጥቅምት 4፣ 2015 ዓ.ም እለት ማለፉን መግለጫው አትቷል።

“በትግራይ ሰላም ሳይኖር፤ በኢትዮጵያ ሰላም ሊኖር አይችልም”
ህወሓት ትናንት ባወጣው መግለጫ መስከረም 1/2015 ላይ ግጭት ለማቆም ያወጣነውን መግለጫ የአፍሪካ ኅብረት፣ የተባበሩት መንግሥታት፣ የአውሮፓ ኅብረት ጨምሮ ሌሎች አካላት በበጎ ቢቀበሉትም ግጭቱን ለማቆም ግን አንዳችም ተግባራዊ እርምጃ አልተወሰደም ብሏል። ዓለም አቀፉ ማሕብረሰብ ግጭቱ በአስቸኳይ እንዲቆም ማረጋገጥ አልያም የትግራይ ሕዝብ እራሱን እንዲከላከል የመርዳት አማራጮች አሉት ያለው የህወሓት መግለጫ፤ ሁለቱም አማራጮች የማይወሰዱ ከሆነ፤ “የትግራይ ሕዝብ ሕልውናውን ለማረጋገጥ ትግሉን ይቀጥላል . . . በትግራይ ሰላም ሳይኖር፤ በኢትዮጵያ ሰላም ሊኖር አይችልም” ሲል ገልጿል። በመግለጫው ማጠቃለያ ላይ ዓለም አቀፉ ማሕብረሰብ የኤርትራ ጦር ከትግራይ እንዲወጣ ጫና እንዲያሳድር፣ ግጭት እንዲቆም ተግባራዊ እርምጃዎችን እንዲወስድ እና የኢትዮጵያ መንግሥት ወደ ድርድር ጠረጴዛ እንዲመጣ ጫና እንዲያሳድር ጠይቀዋል።
የደቡብ አፍሪካው የሰላም ንግግር
ከሁለት ሳምንታት በፊት የአፍሪካ ኅብረት ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ሊያካሂደው አስቦት በነበረው የሰላም ንግግር ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት እና የትግራይ ኃይሎች እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርቦ፣ ሁለቱም ወገኖች ተሳታፊ ለመሆን ፈቃደኛ መሆናቸውን ገልጸው እንደነበር ይታወሳል። ነገር ግን ምክንያቱ በግልጽ ባልተገለጸ ሁኔታ ንግግር ሊደረግበት የታሰበው ቀን ወደ ሌላ ጊዜ መተላለፉ ከመነገሩ ባሻገር፣ አሸማጋይ ይሆናሉ ከተባሉት ሦስት የቀድሞ አፍሪካውያን መሪዎች መካከል አንዱ የሆኑት የኬንያው የቀድሞ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ መሳተፍ እንደማይችሉ ገልጸዋል። በመጪው ጥቅምት 24/2015 ዓ. ም. ሁለት ዓመት የሚሞላው ጦርነት በአሥር ሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ሞት፣ ለመቶ ሺዎች መፈናቀል፣ ሚሊዮኖችን ደግሞ ሰብአዊ እርዳታ ጠባቂ ከማድረግ ባሻገር ከባድ ቁሳዊ ውድመትን ማስከተሉ ሲዘገብ ቆይቷል።
ምንጭ – ቢቢሲ