በአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል እየተካሄደ ካለው ጦርነት ጋር በተያያዘ አየርላንድ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚጻረሩ ድርጊቶችን እየፈጸመች ነው ስትል የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ለአገሪቱ መንግሥት መጻፏ ተገለጸ። የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ለአየርላንዱ አቻቸው በጻፉት ደብዳቤ፣ አውሮፓዊቷ አገር በኢትዮጵያ ላይ “ያልተጠበቀ ደባ እየፈጸመች ነው” ሲሉ ከሰዋል። ከሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ጋር በተያያዘም አየርላንድ “ህወሓትን በመደገፍ በፀጥታው ምክር ቤት ያላትን መቀመጫ በመጠቀም በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲፈጠር ግፊት እያደረገች ነው” በማለት፣ አገሪቱ ከዚህ “ኢትዮጵያን ከማጥቃት ድርጊቷ እንድትታቀብ” ደብዳቤው ጠይቋል።
አየርላንድ የሰሜን ኢትዮጵያን የእርስ በእርስ ጦርነት በተመለከተ በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ውይይት እንዲደረግ በተደጋጋሚ ለምክር ቤቱ ጥያቄ ከሚያቀርቡ አገራት መካከል ግንባር ቀደም ናት። ኢትዮጵያ ላለፉት ሁለት ዓመታት በአየርላንድ ላይ ቅሬታዋን ማቅረቧን የገለጹት ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ሬድዋን ሁሴን፣ ሰሚ በማጣቷ ኢትዮጵያ “በዚህ ሳምንት ለአየርላንድ መንግሥት ይፋዊ ማስጠንቀቂያ ጽፋለች” ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
ኢትዮጵያ ደብዳቤውን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን አማካይነት የጻፈች ሲሆን፣ የተላከውም ለአየርላንድ የውጭ ጉዳይ እና የመከላከያ ሚኒስትር ሳይመን ኮቪኒ መሆኑም ተገልጿል። አሁን የተጻፈው ደብዳቤ አየርላንድ በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ላይ እየፈፀመች ካለችው ጥቃት እንድትታቀብ ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ ያቀረበችውን ጥሪ ችላ እንዳለችው ገልጿል።
ከዚህ በተጨማሪም አየርላንድ በኢትዮጵያ እና በአውሮፓ ኅብረት መካከል ያለው ግንኙነት መሻሻል ላይ እክል ፈጥራለች በማለት በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የተጻፈው ደብዳቤ ከሷል። የኢትዮጵያ መንግሥት እንዳለው አየርላንድ የፀጥታው ምክር ቤትን እና የአውሮፓ ኅብረትን በመጠቀም “እየፈፀመች ከምትገኘው የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ከሚነካ ድርጊቷ እንድትታቀብ” ጠይቋል።
በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ስለተጻፈው የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ እና የቀረቡባትን ክሶች በተመለከተ አየርላንድ አስካሁን ያለችው ነገር የለም።

አየርላንድ የተባባሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት አባል ስትሆን፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ ጉዳዩን በሚመለከት በምክር ቤቱ ስብሰባ እንዲካሄድ ከሚጠይቁ አገራት መካከል አንዷ ናት። ከአየርላንድ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ መንግሥት ጠንካራ ይፋዊ እርምጃ ሲወስድ ይህ የመጀመሪያው አይደለም። ባለፈው ዓመት ኅዳር ወር ላይ አዲስ አበባ በሚገኙ የአገሪቱ ዲፕሎማቶች ላይ መንግሥት እርምጃ መውሰዱ ይታወሳል። በወቅቱም የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ አዲስ አበባ የነበሩ አራት የአየርላንድ ዲፕሎማቶች በኢትዮጵያ ተቀባይነት እንደሌላቸው እና በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ ውሳኔ ማስተላለፉን ይፋ አድርጎ ነበር።
በወቅቱ ውሳኔውን በተመለከተ የአየርላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለኢትዮጵያ እርምጃ ምክንያት “በአገሪቱ እየተካሄደ ካለው ጦርነትና ከሰብአዊ ቀውስ አንጻር በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት እና በዓለም አቀፍ መድረኮች አየርላንድ በያዘችው አቋም ነው” ብሏል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሳይመን ኮቬኒ በኢትዮጵያ እርምጃ ማዘናቸውን አመልክተው “የፀጥታው ምክር ቤትን ጨምሮ አየርላንድ የምታራምደው አቋም ከአውሮፓ ኅብረት ጋር የተጣጣመ ነው” ብለው ነበር። ኢትዮጵያ በሰሜን የአገሪቱ ክፍል እየተካሄደ ካለው ጦርነት ጋር በተያያዘ አንዳንድ የአውሮፓ አገራት ተገቢ ያልሆነ ጫና እና ጣልቃ ገብነትን እያንጸባረቁ ነው ስትል በተደጋጋሚ ስትወቅስ ቆይታለች።
ምንጭ – ቢቢሲ