የኢትዮጵያ መንግሥት ሰላም ለማውረድ ከህወሓት ጋር በሚደረገው የድርድር ሂደት እንደሚገፋበት ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ። ዛሬ መስከረም 30 ቀን 2015 ዓ. ም. ስድስተኛው የሕዝብ ተወካዮች እና የፌደሬሽን ምክር ቤት 2ኛ ዓመት የጋራ መክፈቻ ስብሰባ ላይ ፕሬዝዳንቷ መንግሥት በዚህ ዓመት ትኩረት የሚያደርግባቸውን ጉዳዮች በተመለከተ ባደረጉት ንግግር ነው ይህንን ያሉት።

“የአገሪቱን ጥቅም ባስከበረ” እንዲሁም “ዘለቄታን ባማከለ” መልኩ ከህወሓት ጋር የሚደረገውን ድርድር የፌደራል መንግሥቱ እንደሚቀጥልበት ገልጸዋል። ፕሬዝዳንቷ እንዳሉት መንግሥት የድርድር ሂደቱን ቢገፋበትም “የሰላም አማራጭ ተትቶ ትንኮሳ ከተደረገ አስፈላጊው እርምጃ ይወሰዳል” ሲሉ ተናግረዋል። ጨምረውም መንግሥት “ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ለመደራደር” ያለውን ፍላጎት በንግግራቸው ጠቅሰው “የሰላም በር አይዘጋም” ሲሉ አስምረውበታል።

አያይዘውም ማንኛውንም ልዩነት ለመፍታት “ያለ ቅድመ ሁኔታ ለመወያየት አሁንም ጥሪ ያቀርባል” ሲሉ ፕሬዝዳንቷ ተናግረዋል። የባለፈው ሳምንት የአፍሪካ ኅብረትን የድርድር ጥሪ ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት ያለ ቅድመ ሁኔታ በየትኛውም ቦታና ጊዜ ንግግር ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን በመግለጽ ግብዣውን መቀበሉ ይታወሳል። በተመሳሳይም ህወሓት ደቡብ አፍሪካ ውስጥ በአፍሪካ ኅብረት አሸማጋይነት ይደረጋል በተባለው ንግግር ላይ ለመሳተፍ ፈቃደኛ መሆኑን ገልጿል።

ነገር ግን በአህጉራዊው ድርጅት አማካይነት ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ ይደረጋል ተብሎ የነበረው ንግግር የሎጂስቲክስ በተባለ ችግር ምክንያት ወደ ሌላ ጊዜ መዘዋወሩ ተነግሯል። ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ፣ በዚህ ዓመት መንግሥት አገሪቱ ከጦርነት የምትወጣበት እንዲሆን ያለውን ፍላጎት ጠቁመው፣ የአፍሪካ ኅብረትም ለሰላም የሚያደርገውን ጥረት እንደሚቀጥል ተስፋ እንዳለ ጠቅሰዋል። ከዚህ በተጨማሪም ፕሬዝዳንቷ በዓመቱ የምክር ቤቶቹ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ከህወሓት ጋር ከሚደረገው ድርድር ባሻገር አገር አቀፍ የምክክር ኮሚሽኑ የሐሳብ ልዩነቶችን በውይይት ለመፍታት የሚያደርገውን ጥረት መንግሥት እንደሚደግፍ ገልጸዋል።

“ደም አፋሳሽ ጦርነት ከሚፈጥረው ቂምና ቁርሾ እንዲሁም ከግጭት አዙሪት ለመውጣት” ከአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ጎን መቆም እንደሚያሻ ተናግረዋል። ከሰዓት በኋላ በተደረገው ስብሰባ የ2014 ዓ. ም. ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና የምጣኔ ሀብት ዳሰሳ አቅርበው፣ ለ2015 ዓ. ም. የተያዙ ዕቅዶችን ርዕሰ ፕሬዝዳንቷ በንግግራቸው ዳሰዋል። በጦርነቱ ሳቢያ የወደሙ ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ተቋማት እንዲሁም ሌሎች አገልግሎት መስጫዎችን መልሶ ለማቋቋም በ2014 ዓ. ም. ሥራዎች እንደተጀመሩና በያዝነው ዓመትም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

ጦርነት፣ የኮሮናቫይረስ፣ ጎርፍ እና ድርቅ በአገሪቱ ምጣኔ ሀብት ላይ ጫና ቢያሳድርም፣ ውጤቶች እንደተመዘገቡም ርዕሰ ብሔሯ ሳይጠቅሱ አላለፉም። ያለፈው ዓመት ከውጭ ንግድ ከፍተኛ የሚባለው ገቢ የተመዘገበበት እንደሆነ ጠቅሰው፣ የታክስ ገቢ 93.5% እንዳደገ እንዲሁም ለ2.38 ሚሊዮን ሕዝብ የሥራ ዕድል እንደተፈጠረ ተናግረዋል። ግብርናው 43% ድርሻውን እንደያዘና የአገልግሎት ዘርፍ ደግሞ 32% ድረሻ እንደያዘ በንግግራቸው ጠቅሰዋል።

መንግሥት በተያዘው በጀት ዓመት ትኩረት ከሚሰጣቸው ምጣኔ ሀብታዊ ማሻሻያዎች መካከል የታክስ ገቢ ማሻሻል፣ የሀብት ብክነት መቀነስ እንዲሁም የመንግሥትን በጀት ድህነትን የሚቀንስ ዘርፍ ላይ እንደሚያተኩር ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ጠቅሰዋል። አያይዘውም በግጭት ሳቢያ ለተፈናቀሉ ሰብአዊ እርዳታ ለማድረግ እንዲሁም ማኅበራዊ አገልግሎት መስጫዎችን መልሶ ለማቋቋም ፋይናንስ በማሰባሰቡ መንግሥት እንደሚቀጥል ጠቁመዋል። አዳዲስ ትምህርት ቤቶችን በመሥራ እና አሮጌ ትምህርት ቤቶች በማደስ እንዲሁም ደግሞ ለአቅመ ደካሞች ቤት በመሥራት ማኅበራዊ በጎ አገልግሎቶች 1 ሚሊዮን ዜጋ እንደተሳተፈ ገልጸዋል።

በምጣኔ ሀብት ረገድ ማኅበረሰቡን እየፈተነ ያለውን የዋጋ ንረት ለማርገብ የምግብ ምርትን በማሳደግ፣ የንግድ ሰንሰለትን አዘምኖ ምርትን ወደ ገበያ በማምጣት እና አነስተኛ ገቢ ላላቸው ድጎማ በማድረግ እንደሚሠራ አክለዋል። በ2014 ዓ. ም. ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኃይል ማመንጨት መጀመሩን እንደ ስኬት የጠቀሱት ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ፣ ግድቡን በተያዘለት ጊዜ አጠናቆ የሚመነጨውን ኃይል ከኢትዮጵያ ባሻገር ለጎረቤት አገራትም የመሸጥ ዕቅድን በንግግራቸው አንስተዋል። መንግሥት በተያዘው የበጀት ዓመት አገሪቱን አማራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ በማድረግ እንዲሁም የተቀዛቀዘውን የቱሪዝም ዘርፍ በማነቃቃት እንደሚሠራ ጠቁመዋል።

በሕዝቡ ዘንድ በፍትሕ እጦት እና መዘግየት የተፈጠረውን ቅሬታ ለመቅረፍ እንደሚሠራ እንዲሁም የአገር አቀፍ ተቋማትን አሠራር ግልጽና ቀልጣፋ ለማድረግ እንደሚሠራም ጠቅሰዋል።

ምንጭ – ቢቢሲ

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *