ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም. በትግራይ ውስጥ ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ የተለያዩ ወገኖች ሰላም እንዲወርድ ጥሪ ሲያቀርቡ እና ጥረት ሲያደርጉ እነሆ ሁለት ዓመት ሊሞላ ነው። በተለይ የኢትዮጵያ መንግሥት ለሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት መቀላጠፍ በሚል መጋቢት 15/2014 ዓ.ም. ላልተወሰነ ጊዜ የሚጸና የተኩስ አቁም ሲያውጅና የትግራይ ኃይሎችም በዚሁ ውሳኔ ሲስማሙ ለድርድር በር ይከፍታል የሚል ተስፋን ፈጥሮ ነበር።

ይህንን አጋጣሚ በመጠቀምም የአፍሪካ ኅብረት፣ አሜሪካ፣ የአውሮፓ ኅብረት እና የቀድሞው የኬንያ መሪ ድርድር እንዲጀመርና ጦርነቱ ማብቂያ እንዲያገኝ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል። በተለይ የአፍሪካ ኅብረት እና አሜሪካ በተደጋጋሚ ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት እንዲሁም ከትግራይ ኃይሎች መሪዎች ጋር በአዲስ አበባ እና በመቀለ ንግግር ቢያደርጉም ይህ ነው የተባለ ጦርነቱን የሚያስቆም ውጤት ሳያገኙ ቆይተዋል።

የአፍሪካ ኅብረት ከፍተኛ ተወካይ እና የአሜሪካ መንግሥት ልዩ ልዑክ ያደረጓቸው ጥረቶች፣ ወደ ትግራይ የሚደርሰውን የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት እንዲሻሻል ያደረገው የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲጸና በማድረግ በዘላቂነት ጦርነቱን ለማስቆም ሳያስችል ቆይቷል።

የቀደሙ ሙከራዎች

በተባበሩት መንግሥታት፣ በተለያዩ አገራት ያጋጠሙ ግጭቶችን ለማስቆም በተደረጉ ጥረቶች ውስጥ የሰሩት የሕግ ባለሙያና ዲፕሎማቱ አቶ ባይሳ ዋቅወያ፣ በሰሜን ኢትዮጵያ የሚካሄደውን ጦርነት ለማብቃት ፈታኝ እና ውስብስብ ሁኔታዎች እንዳሉ ይናገራሉ። ነገር ግን የትኛውም ዓይነት ጦርነት በተለይም የእርስ በርስ ጦርነቶች የሚያበቁት በተፋላሚ ወገኖች መካከል በሚደረጉ ድርድሮች በመሆኑ “የቱንም ያህል ፈታኝ ሁኔታዎች ቢኖሩም ብቸኛው መፍትሔ ድርድር ነው” ይላሉ።

ሁለቱም ወገኖች ጦርነቱ በድርድር እንዲያበቃ ፍላጎት እንዳላቸው በተደጋጋሚ የገለጹ ሲሆን፣ ንግግሩን ማን ይምራው በሚለው ላይ ግን ልዩነት ነበራቸው። የኢትዮጵያ መንግሥት የአፍሪካ ኅብረትን ብቸኛ ምርጫው ሲያደርግ፣ የትግራይ ኃይሎች ደግሞ የቀድሞውን የኬንያ ፕሬዝዳንት በአደራዳሪነት መርጠው ነበር። ይህም ከመነሻው ለንግግር የነበረውን ዕድል እንዲጓተት በማድረግ፣ ለመነጋገር የነበረውን ተስፋ እንዲደናቀፍ እና ጊዜ እንዲባክን አድርጎ ነበር።

ነገር ግን የትግራይ ኃይሎች ሐሳባቸውን ቀይረው ንግግሩ በአፍሪካ ኅብረት በኩል እንዲካሄድ በመስማማታቸው የሰላም ተስፋው መልሶ አንሰራራ። ከዚህ በፊት ግን ሁለቱ ወገኖች ይፋዊ ባልሆነ መንገድ በአሸማጋዮች አማካኝነት መገናኘታቸው ሲነገር ነበረ። የትግራይ ኃይሎች በአንድ ደብዳቤያቸው ላይ ይህንኑ የገለጹ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ግን ይህንን በሚመለከት ያለው ነገር የለም።

የአውሮፓ ኅብረት ልዩ ተወካይ የሆኑት አኔት ቬበር በመስከረም ወር መጀመሪያ ላይ ለኅብረቱ አባል አገራት ባሰራጩት አንድ ሰነድ ላይ፣ ሁለቱ ወገኖች በአሜሪካ አመቻችነት በተለያዩ ጊዜያት ይፋዊ ባልሆነ ሁኔታ በጂቡቲ እና በሲሸልስ መገናኘታቸውን ጠቅሰዋል። ይህም ቢሆን ግን ለጦርነቱ ማብቃት የሚያግዝ መደበኛ ድርድር ለማድረግ የሚያስችል ውጤትን ለማምጣት ሳይችል ቀርቷል።

ለንግግሩ ገፊ ምክንያቶች

ማንኛውም ጦርነት በተለይም የእርስ በርስ ጦርነት መቋጫው ድርድር ነው የሚሉት በድርድር እና በዲፕሎማሲ ዓለም አቀፍ ልምድ ያላቸው አቶ ባይሳ ዋቅወያ፣ ሁለቱም ወገኖች ንግግር ለመጀመር ፍላጎታቸውን ማሳየታቸው፣ የተለያዩ ወገኖች ጫና እንዳለ ሆኖ አምነውበት የሚገቡበት ነው የሚል አዎንታዊ አመለካከት አላቸው። ቢሆንም ግን በጦርነቱ ጅማሬ ወቅት በዓለም ላይ የነበረው ተጨባጭ ሁኔታ በአሁኑ ወቅት የለም። በተለይ ምዕራባውያን ትኩረታቸው በዩክሬንና ሩሲያ ጦርነት መያዙ፣ እንዲሁም በዓለም ዙሪያ የተከሰተው ምጣኔ ሀብታዊ ጫና ነገሮችን ለውጧል።

አቶ ባይሳም ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች እና በአገር ውስጥ ያሉ ክስተቶች ተፋላሚ ወገኖች ፊታቸውን ወደ ድርድር እንዲያዞሩ አድርጓቸዋል ይላሉ። “በጦርነቱ ጅማሬ ወቅት የነበረው የምዕራባውያን ወደ አንድ ወገን ያዘነበለ ድጋፍ መመናመን፣ በትግራይ ላይ የቆየው ከበባ፣ በአገሪቱ እየተባባሰ የመጣው የምጣኔ ሀብት ቀውስና የኑሮ ውድነት በሁለቱም ወገን ንግግርን እንዲመርጡ አስገድዷቸዋል።” ባለፉት ሁለት ዓመታት ጦርነቱ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ነገር ግን በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለሞት መዳረጉ ይታመናል።

የተከሰተው ሰብአዊ ቀውስ ከትግራይ ባሻገር በአማራና በአፋር ክልሎች ውስጥ በመቶሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለእርዳታ ጠባቂነት ዳርጓል። አቶ ባይሳ ሁለቱም ወገኖች የጦርነቱን ከባድ ዋጋ ከማንም በላይ ይገነዘቡታል የሚሉት አቶ ባይሳ፤ ከተጠቀሱት ገፊ ምክንያቶች በተጨማሪ ይህ ደም አፋሳሽ የእርስ በርስ ጦርነት “ማንም አሸናፊ ሆኖ የሚወጣበት ባለመሆኑ ሁለቱም ወገኖች በንግግር ችግራቸውን ይፈታሉ” የሚል ተስፋ አላቸው።

የአፍሪካ ኅብረት ጥሪ

ሁለቱም ወገኖች ንግግሩን እንዲመራ የተስማሙበት አህጉራዊው ድርጀት የሰላም ሂደቱን ለመጀመር ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ለመገናኘት ማቀዱን በመግለጽ የግብዣ ጥሪውን መስከረም 21/2015 ዓ.ም. ማቅረቡ ሲነገር ለበርካቶች ድንገተኛ ነበር። በኅብረቱ የተጻፈ የጥሪ ደብዳቤ እንደሚለው በሁለቱ ወገኖች መካከል ይደረጋል ተብሎ በሚጠበቀው ንግግር ለቀጣይ ድርድር አስፈላጊ የሆኑ ዝርዝር ጉዳዮች ትኩረት እንደሚደረግባቸው አመልክቷል።

ንግግሩንም ለአንድ ዓመት የኅብረቱ የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ ሆነው ጥረት ሲያደርጉ የነበሩት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ እንደሚመሩትና የቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት እንዲሁም የቀድሞዋ የደቡብ አፍሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት እንደሚሳተፉ ገልጿል። የኢትዮጵያ መንግሥትም የአፍሪካ ኅብረት ግብዣ የኢትዮጵያ መንግሥት ከዚህ በፊት ካንጸባረቃቸው አቋሞቹ ጋር የሚጣጣሙ በመሆናቸው በንግግሩ ውስጥ እንዲሳተፍ የቀረበለትን ግብዣ እንደሚቀበለው አሳወቀ።

ከትግራይ ኃይሎች በኩልም የቀረበላቸውን የሰላም ንግግር ግብዣን እንደተቀበሉት ገልጸው፣ ነገር ግን ይህ ጥሪ ከመቅረቡ በፊት ከኅብረቱ ጋር ምክክር ባለመደረጉ የሰላም ውይይቱ ተሳታፊዎች፣ ታዛቢዎች እና ዋስትና ሰጪዎች፣ የጉዞ  እና የደኅንነት ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ጠይቀው ነበር። ለሁለቱም ወገኖች የቀረበው የንግግር ጥሪው ከቀረበ ከሳምንት በኋላ ደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ውስጥ ይካሄዳል የተባለው ንግግር፣ ሁለት ዓመት ሊሞላው በተቃረበው ጦርነት ውስጥ ከታዩት ሁሉ ጉልህ እመርታ ሊሆን እንደሚችልና ለቀጣይ ሰላም መሠረት ይጥላል የሚል ተስፋን በብዙዎች ዘንድ ፈጥሮ ነበር።

የአፍሪካ ኅብረትም “በሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች መካከል የሚካሄደው ይህ የሰላም ውይይት ጦርነቱን በሰላም ለመቋጨት መሠረት የሚሆኑ መርሆች፣ የአጀንዳ ጉዳዮች፣ አሰራሮች እና የጊዜ ሰሌዳዎች ላይ ይመክራል ተብሎ ይጠበቃል” ብሏል። የኢትዮጵያ መንግሥት እና የትግራይ ኃይሎች በንግግሩ ለመሳተፍ ፈቃደኛ መሆናቸውን መግለጻቸውን ተከትሎ፣ አፍሪካ ኅብረት ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ሁለቱም ወገኖች ለግብዣው አዎንታዊ ምላሽ መስጠታቸውን አድንቀው፣ ለሰላም ዕድል እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል።

ጨምረውም ንግግሩ በአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ እና የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ፣ በቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እና በቀድሞዋ የደቡብ አፍሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፉምዚሌ ምላምቦ-ናግኩካ የሚመራ መሆኑን ይፋ አድርጓል።

ያልታሰቡ እክሎች

ውይይቱ የሚጀመርበት ዕለት አንድ ቀን ሲቀረው አርብ ከሰዓት በኋላ ሮይተርስ የዜና ወኪል ዲፕሎማቲክ ምንጮችን ጠቅሶ፣ ባጋጠመ የሎጂስቲክስ እክል ምክንያት ንግግሩ ወደ ሌላ ጊዜ መተላላፉን ዘገበ።  ነገር ግን ምክንያት ሆነው የሎጂስቲክስ ችግር ምን እንደሆነ ዲፕሎማቶቹ በግልጽ ያሉት ነገር አልነበረም። ይህንን ተከትሎ ደግሞ ከአሸማጋዮቹ አንዱ የሆኑት የቀድሞው የኬንያው ፕሬዝዳንት ድርድሩ የሚጀመርበት ጊዜ ካላቸው ከሌላ ዕቅድ ጋር የሚደራረብ መሆኑን ጠቅሰው መገኘት እንደማይችሉ የሚገልጽ ደብዳቤ ለአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መጻፋቸው ይፋ ሆነ።

ነገር ግን የኡሁሩ ጥያቄ የጊዜ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም ያነሷቸው ጉዳዮች እንዳሉ ደብዳቤያቸው ላይ ጠቅሰዋል። ኡሁሩ በሌላ ጊዜ በሂደቱ ለመሳተፍ እንደሚችሉ፣ ነገር ግን ንግግሩ ስለሚካሄድበት ሂደት አወቃቀር እና አፈጻጸም፣ የተጋበዙ አሸማጋዮች መመሪያ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል። እንዲሁም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ የተኩስ አቁም ማድረግ ከንግግሩ ከአጀንዳዎች ሁሉ ቀዳሚው መሆን እንዳለበት እና ይህም ለንግግሩ ትክክለኛውን ሁኔታ ይፈጥራል በማለት ጥያቄ አቅርበዋል።

ዲፕሎማቱ አቶ ባይሳ እንደሚሉት፣ በዚህ ንግግር ጦርነቱን የሚቋጭ ስምምነት ላይ አይደርሱም። ሁለቱ ወገኖች ንግግር መጀመራቸው ዋነኛው ጉዳይ ነው። በዚህም ለቀጣይ ድርድር የሚያስፈልገውን ተኩስ አቁም ላይ መስማማት እንዲሁም ለጦርነቱ መቋጫ ለሚያስፈልጉ ጉዳዮች ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀት እና መስማማት ቀዳሚ እንደሚሆን ያምናሉ። ነገር ግን ይህንን ጦርነት ለማብቃት የሚደረገው ድርድር ቀላል እንደማይሆን የሚጠቅሱት አቶ ባይሳ “እንዲህ አይነት ውስብስብ ፖለቲካዊ ሁኔታ ያለበት ግጭት አይቼ አላውቅም” በማለት ጦርነቱ በቶሎ እንዲያበቃ ይመኛሉ።

ባለፈው ነሐሴ የተቀሰቀሰው ጦርነት እየተካሄደ ባለበት፣ ከዚህ በፊት ከታየው በተለየ ሁለቱም ወገኖች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ንግግር ለመጀመር ፍላጎታቸውን ባሳዩበት ሁኔታ በአደራዳሪዎች በኩል ገጠሙ በተባሉ እንቅፋቶች ተስተጓጉሏል። የአፍሪካ ኅብረትም በመጨረሻው ሰዓት ላይ ገጠሙት የተባሉት የሎጂስቲክስ ችግሮችን በተመለከ እንዲሁም በኡሁሩ ኬንያታ በኩል የቀረቡ ጥያቄዎችን በተመለከተ እስካሁን በይፋ ያለው ነገር የለም። እንዲሁም የገጠሙ ችግሮች ተቀርፈው በቀጣይ ንግግሩ መቼ ሊደረግ እንደሚችል የሚለው እየተጠበቀ ነው።

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *