የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በጋምቤላ ጽሕፈት ቤቱ ላይ ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ፣ ጽሕፈት ቤቱ በጊዜያዊነት በፌዴራል ፖሊስ ጥበቃ እንዲደረግለት ጥያቄ ማቅረቡን አስታወቀ፡፡ የፀጥታ ኃይሎች በጋምቤላ ከተማ ውስጥ በወሰዱት ዕርምጃ 50 ንፁኃን መገደላቸውንና 25 ሰዎች ላይ ቀላልና ከባድ የመቁልስ አደጋ ማድረሳቸውን የሚገልጽ የምርመራ ሪፖርት መስከረም 18 ቀን 2015 ዓ.ም. ይፋ ያደረገው ኢሰመኮ፣ ከሪፖርቱ በኋላ በጋምቤላ ጽሕፈት ቤቱ ላይ ጥቃት እንደደረሰበት ገልጿል፡፡

ጥቃቱ የደረሰው መስከረም 25 ቀን 2015 ዓ.ም. እኩለ ሌሊት ከስድስት እስከ ስምንት ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ መሆኑን ለሪፖርተር የተናገሩት የኮሚሽኑ የሰብዓዊ መብቶች ክትትልና ምርመራ ሥራ ክፍል ከፍተኛ ዳይሬክተር አቶ ይበቃል ግዛው፣ ጥቃት አድራሾቹ ‹‹በርከት›› ያለ ቁጥር ያላቸው ወጣቶች መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ እንደ ከፍተኛ ዳይሬክተሩ ገለጻ፣ ኮሚሽኑ የተቋማቱን ‹‹የሰብዓዊ መብት ተቋምነት›› ለማስጠበቅ በማለት በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ ጽሕፈት ቤቶቹን፣ በፌዴራልም ሆነ በሌሎች የፖሊስ አካላት አያስጠብቅም፡፡

ይህም ኢሰመኮ የሰብዓዊ መብት ተቋም ስለሆነ ማንም ሰው በቀላሉ መግባት መውጣት የሚችልበት እንዲሆን በማሰብ የተደረገ እንደሆነ ከፍተኛ ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡ ለዚህም ሲባል የተቋሙ ጽሕፈት ቤቶች በኮሚሽኑ የጥበቃ ሠራተኞች እንጂ በፖሊስ እንደማይጠበቁ አክለዋል፡፡ ‹‹በጋምቤላ ክልል ያለው የፀጥታ ሁኔታ ጉዳዩን በተለየ አካሄድ እንድናየው ያደርጋል፤›› ያሉት ከፍተኛ ዳይሬክተሩ፣ የፌዴራል ፖሊስ በጊዜያዊነት ለጽሕፈት ቤቱ ጥበቃ እንዲያደርግ ሥራ መጀመሩንና ለፌዴራል ፖሊስ ጥያቄ መቅረቡን አስታውቀዋል፡፡

በጽሕፈት ቤቱ ላይ ጥቃት ያደረሱበት ግለሰቦች ኢሰመኮ ጋምቤላ ክልል ውስጥ ያለውን ሥራ እንዲያቋርጥና ጥሎ እንዲወጣ ዛቻ ሲያደርሱ እንደነበር የገለጹት አቶ ይበቃል፣ ‹‹ነውረኛ ስድብ እየተሳደቡ፣ ኮሚሽኑ ጋምቤላ ውስጥ ያለውን ሥራ እንዲያቋርጥና ጥሎ እንዲወጣ እያሳሰቡ ነበር የቆዩት፤›› በማለት ሁኔታውን ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም በጽሕፈት ቤቱ መግቢያ ላይ የሚገኝንና በከተማዋ ውስጥ ያለን ሌላ ቢልቦርድ በቀለም እንዳበላሹት አስታውቀዋል፡፡

ኮሚሽኑ ይህንኑ ጥቃት አስመልክቶ ሐሙስ መስከረም 26 ቀን 2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ጥቃት አድራሾቹ ከኢሰመኮ ባሻገር፣ ‹‹በከተማዋ የተለያዩ የሰብዓዊ መብቶች ሥራዎችን በሚያከናውኑ ሌሎች ድርጅቶች ላይ ተመሳሳይ ጥፋት አድርሰው፣ ድርጅቶቹ ከከተማው ለቅቀው እንዲወጡ አስፈራርተዋል፤›› ብሏል፡፡ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) ጥቃቱን፣ ‹‹ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለውና በክልሉ የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ምልከታ የሚጥል›› በማለት የገለጹት ሲሆን፣ የፌዴራልና የክልሉ መንግሥት ተባብረው ጥቃቱን በአፋጣኝ እንዲያስቆሙ አሳስበዋል፡፡

አቶ ይበቃል ጥቃቱ በጽሕፈት ቤቱ የሚሠራው ሥራ ላይ፣ ‹‹ተፅዕኖ ለማሳደር ያለመ›› እንደሆነ የተናገሩ ሲሆን፣ ጥቃቱ የደረሰው ከሳምንት በፊት የወጣውን የምርመራ ሪፖርት ተከትሎ ነው የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡ ኮሚሽኑ መስከረም 18 ቀን 2015 ዓ.ም. ይፋ ያደረገው የምርመራ ሪፖርት የክልሉ የፀጥታ ኃይሎች፣ ከኦነግ ሸኔና ከጋምቤላ ነፃነት ግንባር (ጋነግ) ጋር ያደረጉትን ውጊያ ተከትሎ፣ ሰኔ 7 ቀን 2014 ዓ.ም. በጋምቤላ ከተማ ባደረጉት ውጊያና በተከታዮቹ ቀናት የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የሚዳስስ ነው፡፡

የኮሚሽኑ ባለ 13 ገጽ የምርመራ ሪፖርት በፀጥታ ኃይሎች ሴቶችና የአዕምሮ ሕመምተኞችን ጨምሮ ቢያንስ 50 ሲቪል ሰዎች በተናጠልና በጅምላ ከፍርድ ውጪ መገደላቸውን፣ የተገደሉት ሰዎችን አስከሬኖች ባልታወቀ ቦታ በጅምላ መቅበራቸውን ገልጿል፡፡ ሪፖርቱ፣ ‹‹ቢያንስ 25 በሚሆኑ ሰዎች ላይ ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱን፣ እንዲሁም በበርካታ ሰዎች ላይ የመደብደብና የማሰቃየት ተግባር መፈጸሙን ኮሚሽኑ አረጋግጧል›› ሲልም ተጨማሪ ግኝቶችን ያስረዳል፡፡ ‹‹የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎችና መሣሪያ በቤታችሁ እንዳለ ተጠቁመናል፣ የደበቃችሁትን መሣሪያ አውጡ›› በሚል ምክንያት እንደሆነ ሪፖርቱ ላይ ሰፍሯል፡፡

የኦነግ ሸኔና ጋነግ ታጣቂዎችም በአንፃሩ መንገድ ላይ ሲንቀሳቀሱ ያገኟቸውን ቢያንስ ሰባት ሰዎች ገድለው በሲቪል ሰዎች ላይ ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት ማድረሳቸውንም ሪፖርቱ አካቷል፡፡ የጋምቤላ ክልል ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት መስከረም 22 ቀን 2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ‹‹ሚዛናዊነት የጎደለው›› ሲል የተቸው ሲሆን፣ የምርመራ ሪፖርቱን እንደማይቀበለውና እንደሚያወግዘው አስታውቋል፡፡

‹‹የጋምቤላን ነባር ብሔረሰቦችና አብረዋቸው ለረዥም ዘመናት ከሚኖሩ ወንድምና እህት ኢትዮጵያውያን ጋር እርስ በርስ ለማጋጨት ሆን ተብሎ የተዘጋጀ ሪፖርት ሆኖ አግኝተነዋል፤›› ሲልም ኮሚሽኑን በወገኝነትነት ከሷል፡፡ የጋምቤላ ክልል ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኡገቱ አዲንግ የኢሰመኮ ሪፖርት ‹‹ማኅበረሰቡን አስቆጥቷል›› ብለው፣ በክልል በሚገኘው የኮሚሽኑ ጽሕፈት ቤት ላይ ጥቃት የደረሰው ‹‹በዚህ ምክንያት ሊሆን ይችላል›› ሲሉ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በጽሕፈት ቤቱ ላይ ጥቃት ስለመድረሱና የኮሚሽኑ ቢልቦርዶች መበላሸታቸውን እንደሚያውቁ የተናገሩት አቶ ኡገቱ፣ ‹‹ኮሚሽኑ ግን  ጉዳዩን ለፖሊስ ሪፖርት አላደረገም፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ፖሊስ ማስረጃ ባይኖረውም ጥቃት ያደረሱትን ለመያዝ ጥረት ያደርጋል፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡ የኮሚሽኑ የሰብዓዊ መብቶች ክትትልና ምርመራ ሥራ ክፍል ከፍተኛ ዳይሬክተር አቶ ይበቃል፣ ኢሰመኮ ከክልሉ መንግሥት ጋር እስካሁን ‹‹መደበኛ›› የሆነ ግንኙነት አለማድረጉን ገልጸው፣ በቀጣይ ንግግር እንደሚደረግ ጠቁመዋል፡፡

ምንጭ – ሪፖርተር 

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *