..አ ነሐሴ 12 ቀን 1949 የወጡት የጄኔቫ ስምምነቶች፣ ሁለቱ ተጨማሪ ፕሮቶኮሎች አና በልማድ እና በትግበራ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያገኙ እና በሁሉም ሀገራት እንዲሁም የትጥቅ ግጭት ተሳታፊ ቡድኖች ላይ ገዢ የሚሆኑት የልማድ ዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ህጎች (customary IHL rules) በሁለቱም አይነት የትጥቅ ግጭቶች ወቅት ማለትም ዓለም አቀፋዊ በሆኑ እና ዓለም አቀፋዊ ባልሆኑ የትጥቅ ግጭቶች ወቅት ሊደርሱ የሚችሉ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለመቆጣጠር ጥቅም ላይ የሚውሉ ህጎች ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የሰብዓዊ መብቶች ህግጋቶች (ማለትም ዓለም አቀፍ፣ አህጉር አቀፍ እና ሀገር አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ህግጋቶች) እና ሌሎች ህጎችም እንደ አግባብነታቸው ጥቅም ላይ ይውላሉ፡፡ በዚህም መሰረት ሰብዓዊ መብቶች በሰላም ወቅት ብቻ ሳይሆን በትጥቅ ግጭትም ወቅት ጥበቃ የሚደረግላቸው መብቶች ናቸው፡፡

ጥቅምት 24/2013 /ም የተጀመረውን የትጥቅ ግጭት ተከትሎ በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ያስከተሉ ድርጊቶች ሲፈጸሙ ቆይተዋል። ኢሰመጉ ይህንን የትጥቅ ግጭት በቅርበት ሲከታተል የቆየ ሲሆን የግጭት ቀጠና በነበሩ አካባቢዎች ከግጭት ነጻ በሚሆኑበት ሰዓት በሁለት ዙር የሰብዓዊ መብቶች የምርመራ ቡድኖቹን በማሰማራት የምርመራ ስራዎችን አከናውኗል፡፡ ኢሰመጉ የምርመራ ስራ ባካሄደባቸው ጦርነቱ ሸፍኗቸው በነበሩ የሰሜን ኢትዮጵያ ክፍሎች ውስጥ በርካታ የሆኑ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች መፈጸማቸውን ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ ከነዚህም ጥሰቶች መካከል ግድያ(ሞት)፣ የአካል ጉዳት፣ ጾታዊ ጥቃት(አስገድዶ መድፈር)፣ ንብረት ማውደምና መዝረፍ፣ ኢሰብዓዊ አያያዝ፣ እና እገታ ይገኙበታል፡፡

ግድያ እና የአካል ጉዳት
ኢሰመጉ የምርመራ ስራዎችን ባከናወነባቸው እና የትጥቅ ግጭቱ ሸፍኗቸው በነበሩ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ውስጥ በሚገኙ በርካታ ስፍራዎች ከፍርድ ውጪ የተፈጸሙ ግድያዎች (Extrajudicial killings) እና በሰቪል ሰዎች ህይወት እና አካል ላይ የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን በምርመራው አግኝቷል፡፡ ሁሉም ሰው በሕይወት የመኖር ሰብዓዊ መብት አለው፡፡ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች መግለጫ አንቀጽ 3 “እያንዳንዱ ሰው በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደህንነቱ የመጠበቅ መብትእንዳለው ያረጋግጣል። ኢትዮጵያ ፈርማ የተቀበለችው የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃልኪዳንም በአንቀጽ 6 (1) እና 9 (1) ላይ ይህንኑ መብት በማረጋገጥ፣ መንግሥታት በቃልኪዳኑ የተረጋገጡትን መብቶች በግዛታቸው የማክበር፣ የማስከበርና የማሟላት ግዴታ እንዳለባቸውም በአንቀጽ 2 (1) እና 2 (2) ይደነግጋል። የአፍሪካ የሰዎችና የሕዝቦች መብቶች ቻርተር አንቀጽ 4 ማንኛውም ግለሰብ በሕይወት የመኖር መብቱና የአካሉ ደህንነት ሊከበርለትና ሊጠበቅለት እንደሚገባና እነዚህን መብቶቹን በዘፈቀደ ሊነፈግ እንደማይችል ተመላክቷል።

የኢ...ሪ ሕገመንግሥት አንቀጽ 14 “ማንኛውም ሰው ሰብዓዊ በመሆኑ የማይደፈርና የማይገሰስ በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደህንነትና የነጻነት መብት አለውሲል ይደነግጋል። በተመሳሳይ የኢ...ሪ ሕገመንግስት አንቀፅ 15 ማንኛውም ሰው በሕይወት የመኖር መብት እንዳለውና በሕግ ከተደነገገው ውጪ ሕይወቱን ሊያጣ እንደማይችል በግልፅ ደንግጓል፡፡ ኢትዮጵያም በኢ...ሪ ሕገመንግስት አንቀጽ 9 ንዑስ አንቀጽ 4 መሠረት እነዚህን ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ የሰብዓዊ መብቶች ሰነዶች አጽድቃ እና የሐገሪቱ ሕግ አካል እንዲሆኑ አድርጋለች፡፡ በሕገመንግሥቱ አንቀጽ 13 ንዑስ አንቀጽ 2 መሠረት ደግሞ በሕገ መንግስቱ ምዕራፍ ሦስት ስር የተዘረዘሩት መብቶችና ነጻነቶች ከዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ሕግጋት፣ ስምምነቶች እና ሰነዶች መርሆዎች ጋር በተጣጣመ መንገድ ሊተረጎሙ እንደሚገባ እውቅና የሰጠች ሐገር እንደመሆኗ፤ ሰብዓዊ መብቶችን የማክበር፣ የማስከበር እና የማሟላት ግዴታ ተጥሎባታል።

ይህ ልዩ ዘገባ በትጥቅ ግጭት ወቅት የተፈጸሙ ግድያዎችን እና የደረሱ የአካል ጉዳቶችን የሚሸፍን በመሆኑ ከሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌዎች በተጨማሪ (human rights laws) የሰብዓዊነት ህጎችን (humanitarian laws) የሚጠቀም ይሆናል፡፡ ስለሆነም በሰሜን ኢትዮጵያ እይተካሄደ የሚገኘው የትጥቅ ግጭት አለም ዓቀፋዊ ያልሆነ የትጥቅ ግጭት በመሆኑ ለዚህ የትጥቅ ግጭት አይነት ጥቅም ላይ የሚውሉ ህጎች በዚህ የትጥቅ ግጭት ወቅት ይተገበራሉ፡፡ ዓለም አቀፋዊ ይዘት የሌለውን የትጥቅ ግጭት የሚገዛው የአራቱ የጄነቫ ስምምነቶ የጋራ የሆነው አንቀጽ 3 በተዋዋይ ወገኖች (በተዋጊ ወገኖች) ላይ አስገዳጅ የሆነ ድንጋጌን አስቀምጧል፡፡ ይህ አንቀጽ የጦር መሳሪያቸውን ያስቀመጡ የጦር ሀይል አባላትንና በህመም ፣ በመቁሰል፣ በመታሰር ወይም በማንኛውም ሌላ ምክንያት ከውጊያ ውጪ የሆኑትን ሰዎች ጨምሮ በግጭቱ ተግባር ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ የሌላቸው ሰዎች ህይወትና አካል ላይ የሀይል እርምጃ መፈጸም፣ በተለይም በማንኛውም መልኩ የሚፈጸም ግድያ፣ አካልን መቆራረጥ፣ ጭካኔ የተሞላበት ተግባር መፈጸምና ማሰቃየት በማንኛውም ጊዜና ቦታ የተከለከሉ ናቸው ሲል ይደነግጋል፡፡

ሁለተኛው የጄኔቫ ስምምነቶች ተጨማሪ ፕሮቶኮል በአንቀጽ 4 ንዑስ አንቀጽ 2(ሀ) ላይ በሰዎች የህይወት፣ የጤንነትና የአካል ወይም የአእምሮ ደሕንነት ላይ የሀይል ድርጊት፣ በተለይም ግድያ እንዲሁም እንደማሰቃየት አካልን ማጉደል ወይም እንደማናቸውም የአካል ቅጣት ያለ የጭካኔ አያያዝ በማናቸውም ጊዜና በየትኛውም ቦታ የተከለከለና ተከልክሎም የሚቆይ ነው ሲል ይደነግጋል፡፡ አለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤትን ለማቋቋም የወጣው ሰነድ (rome statute) በአንቀጽ 8 ንዑስ አንቀጽ (ሐ) ላይ አለማቀፋዊ ይዘት በሌለው የትጥቅ ግጭት ወቅት በትጥቅ ግጭቱ ላይ ተሳትፎ በሌላቸው ሰዎች ላይ የሚፈጸም ግድያ ወይም አካል ጉዳት የጦር ወንጀል መሆኑን ይደነግጋል፡፡ በተጨማሪም የልማድ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ህግ በደንብ ቁጥር 89 ላይ በትጥቅ ግጭት ላይ ተሳትፎ በሌላቸው ሰዎች ላይ ግድያ መፈጸም የተከለከለ ተግባር መሆኑን ይደነግጋል፡፡ ከዓለም አቀፍ ልማዳዊ የትጥቅ ግጭት ህጎች (customary IHL)፣ ከ አራቱ የጄነቫ ስምምነቶች እና ከሁለቱ ተጨማሪ የጄኔቫ ስምምነት ፕሮቶኮሎች በመነሳት በትጥቅ ግጭት ወቅት ተፈጻሚ የሚሆኑ አምስት መርሆችን ማግኘት እንችላለን፡፡ 

እነዚህ አምስት መርሆች የመለየት መርህ (principle of distiniction)፣ በትጥቅ ግጭት ውስጥ ቀጥተኛ ተሳትፎ ማድረግ ያቆሙ ሰዎችን ያለማጥቃት መርህ (The principle on the prohibition to attack those hors de combat) ፣ ተገቢ ያልሆነ ስቃይን ከማድረስ የመቆጠብ መርህ (The principle on the prohibition to inflict unnecessary suffering)፣ የተመጣጣኝነት መርህ (The principle of proportionality) እና የአስፈላጊነት መርህ (The principle of necessity) ናቸው፡፡ እነዚህ መርሆች ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያገኙ እና ጥቅም ላይ የሚውሉ መርሆች በመሆናቸው ከነዚህ መርሆች በተቃርኖ በሲቪል ሰዎች እና ጥበቃ በሚደረግላቸው ሰዎች ላይ የሚፈጸሙ ግድያዎች የአካል ጉዳቶች ልማዳዊ በሆኑ ዓለም አቀፋዊ የሰብዓዊነት ህጎች (customary IHL) መሰረት የጦር ወንጀለኝነትን ሊያቋቀሙ ይችላሉ፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *