የትግራይ ኃይሎች በደቡባዊ ትግራይ አቅጣጫ በፌደራል መንግሥት እና በአማራ ኃይሎች ጥቃት ተከፍቶብናል አሉ። “ከትግራይ ሠራዊት ወታድራዊ ኮማንድ” ተሰጠ በተባለው መግለጫ ዛሬ ረቡዕ፣ ነሐሴ 18/2014 ዓ.ም. ንጋት 11 ሰዓት ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት ተከፍቶብናል ብሏል። በህወሓት ስለቀረበው ክስ ከኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ ከሌላ ገለልተኛ ወገን እስካሁን የተባለ ነገር የለም። ይሁን እንጂ ከቀናት በፊት የፌደራል መንግሥቱ “ህወሓት የጦርነት ነጋሪት እየጎሰመ ነው” ብሎ መክሰሱ ይታወሳል። የመንግሥት ኮምንኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ባለፈው ሳምንት በሰጡት መግለጫ “ህወሓት የጦርነት ነጋሪት ቢጎስምም መንግሥት ግን አሁንም ለሰላም ቅድሚያ ይሰጣል” ብለው ነበር።
በትግራይ ቴሌቪዥን በተነገረው የትግራይ ኃይሎች መግለጫ፤ የአማራ ሚሊሻ እና ፋኖ እና የአገር መከላከያ ሠራዊት ጥምር ኃይል በትግራይ ደቡብ አቅጣጫ መጠነ ሰፊ ጥቃት ጀምረዋል ብሏል። በመግለጫው የፌደራል እና የክልል ኃይሎች የጀመሩት ዘመቻ ዋነኛው ዓላማ “ከምዕራብ ትግራይ እና ምዕራብ ጎንደር ወደ አዲአቦ፣ አስገዲ እና ጸለምቲ እንደሆነ ገልጽ ነው” ብሏል። በመግለጫው ላይ የትግራይ ኃይሎች “ጥቃቱን ለመመከት” እና “ወደ ጸረ ማጥቃት ለመሸጋገር” ሙሉ አቋም ላይ እንገኛለን ብለዋል። ከጥቂት ቀናት በፊት የትግራይ ኃይሎች በሰሜን ምዕራብ በኩል የፌደራል መንሥት ኃይሎች የከባድ መሳርያ ድብደባ መፈፀማቸውን ጠቅሰው ነበር።
ይሁን እንጂ መንግሥት ይህንን ውንጀላ አስተባብሎ፣ “ከሰላም ድርድሩ ለመሸሽ የሚቀርብ ሰበብ ነው” ብሎ ነበር። ይህንን ተከትሎም የህወሓት ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ፣ እስካሁን የነበረው የተኩስ አቁም በመሰረተ ሃሳብ ደረጃ “ፈርሷል” ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረው ነበር።
የሰላም ስምምነት
ይህ የትግራይ ኃይሎች መግለጫ የተሰማው ላለፉት 21 ወራት ገደማ በጦርነት ውስጥ የቆዩት ተዋጋዊ ኃይሎች ልዩነቶቻቸውን በንግግር በውይይት እንዲፈቱ በርካታ ጥረቶች እየተደረጉ ባሉበት ወቅት ነው። ባለፉት ጥቂት ወራት የአፍሪካ ሕብረት ልዩ ልዑክ እና ምዕራባውያን ዲፕሎማቶች እና አምባሳደሮች በመቀለ እና አዲስ አበባ ባለስልጣናትን ማነጋገራቸውን ተከትሎ በበርካቶች ዘንድ የሰላም ተስፋ መኖሩን ገልጸው ነበር። ይሁን እንጂ ምዕራባውያኑ ዲፕሎማቶች እና አምባሳደሮች ወደ መቀለ ከተጓዙ ከሳምንታት በኋላ የህወሓት ኃይሎች በፌደራል መንግሥቱ በተለያዩ አቅጣጫ ጥቃት እንደተከፈተባቸው ተናግረው ነበር።
የህወሓት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳም በትዊተር ገጻቸው ለሰብዓዊነት ሲባል ተደርሶ የነበረው የተኩስ አቁም ስምምነት ፈርሷል ብለው ነበር። የፌደራል መንግሥቱ ቃል አባይ ግን “የሰላም ስምምነቱ ሳይዘገይ በትግራይ መሠረታዊ አገልግሎት እንዲጀመር ለማድረግ የደኅንት ሁኔታ መመቻቸት ስላለበት ቅድሚያ የፖለቲካ ውይይት ማድረግን የአፍሪካ ኅብረት እንዲያጠናክር እያደረገ” እንደሚገኝ ጠቅሰው ህወሓት ግን “የሰላም አማራጭን ለመከተል ስላልፈለገ” መንግሥት “ተኩስ አቁሙን አፍርሷል” ማለቱን ኮንነዋል።
በተመሳሳይ ሁኔታ የጠቅላይ ሚንስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢልለኔ ስዩም ያለፈው ሳምንት ሐሙስ ነሐሴ 12/2014 ዓ.ም. ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ የአገሪቱ መከላከያ ሠራዊት በትግራይ ኃይሎች ላይ ተኩስ ከፍቷል መባሉ “ሐሰት ነው” ብለዋል። የትግራይ ኃይሎች ረቡዕ ነሐሴ 11/2014 ዓ.ም. ባወጡት መግለጫ የፌደራል መንግሥቱ ጦር “በምዕራብ ትግራይ በኩል በከባድ መሣሪያ የታገዘ ጥቃት ፈጽሟል” ማለታቸው አይዘነጋም። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በሰሜን ምዕራብ ትግራይ ደደቢት አካባቢ ባሉ የትግራይ ኃይሎች ላይ በከባድ መሣሪያ ለአንድ ሰዓት የቆየ ድብደባ አድርሷል ሲልም ከትግራይ ወታደራዊ ዕዝ የወጣው መግለጫ ይጠቁማል።
በዚህም ለወራት ታውጆ የነበረው የሰብአዊ እርዳታ የተኩስ አቁም አዋጅ ተጥሷል ብሏል መግለጫው። ይህን መግለጫ ተከትሎ የጠቅላይ ሚንስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢልለኔ፣ በትግራይ ኃይሎች የተሰነዘረው ክስ “ከሰላም ንግግር ለመሸሽ እንደ ምክንያት የቀረበ ነው” ብለዋል። በተያየዥ ዜና የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ትላንት ነሐሴ 17/2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ የሠራዊቱን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ “የመዘገብ ወይም የማራገብ አሉታዊ ሙከራዎች በአስቸኳይ ይቁሙ” ሲል አሳስቧል። በመግለጫው “አንዳንድ የማኅበራዊ ሚዲያ ዘገባዎች እና መረጃዎች አፍራሽ ውንጀላን ባልተገባ መልኩ እየተቀባበሉት መሆኑን አስተውለናል” ብሏል። “ጠላት በዚህ ገባ፣ በዚህ ወጣ፤ የወገን ሠራዊት በዚህ ገባ፣ በዚህ ወጣ የሚለው ወሬ በፍፁም ዜና እና የዜና ትንታኔ ሊሆን አይችልም” ብሏል አገር መከላከያ በመግለጫው።
ምንጭ – ቢቢሲ