በአሜሪካ ልዩ ልዑክ የተመራው ጉብኝት መጠናቀቁን ተከትሎ በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ባወጣው መግለጫ መንግሥት እና ህወሓት ገንቢ ካልሆነ የቃላት ልውውጥ ተቆጥበው ድርድር እንዲጀምሩ አሜሪካ እንደምታበረታታ አመለከተ። የአሜሪካ መንግሥት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ማይክ ሐመር የተመራው ልዑክ በኢትዮጵያ ባደረገው ጉብኝት ከኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ ከአፍሪካ ኅብረት ተወካዮችና ከህወሓት መሪዎች ጋር መወያየቱ ይታወሳል። በልዩ መልዕክተኛው ጉዞ በተለይ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የሚካሄደው ጦርነትን በሰላም ለማብቃት በሚደረገው ጥረት ዙሪያ ውይይት ማድረጋቸው የተገለጸ ሲሆን፣ መልዕክተኛው ሁለቱም ወገኖች የሰላም ንግግር እንዲጀምሩ ማበረታታቸው ተገልጿል።

ልዑካኑ “የኢትዮጵያ መንግሥት እና ህወሓት በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር ውይይት እንዲጀምሩ ያበረታቱ ሲሆን፣ ሁሉም ወገኖች ገንቢ ካልሆኑ ጠብ አጫሪ እና የጥላቻ ንግግሮች እንዲቆጠቡ” ጠይዋል። አምባሳደር ሐመር ከአውሮፓ ኅብረት እና ከሌሎች ምዕራባውያን ዲፕሎማቶች ጋር ባለፈው ሳምንት ወደ መቀለ ሄደው ከህወሓት ከፍተኛ አመራሮች ጋር ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል።

ቡድኑ በመቀለ ውይይቱ ወቅት በመንግሥትና በህወሓት መካከል ሊደረግ ስለታሰበው ድርድር ከመወያየታቸው በተጨማሪ፣ ከአንድ ዓመት በላይ በትግራይ የተቋረጡ መሠረታዊ አገልግሎቶችን ሥራ ለማስጀመር እንዲቻል ህወሓት የደኅንነት ዋስትና እንደሚሰጥ የገለጸበትን ደብዳቤ ለፌደራል መንግሥቱ አምጥተዋል።  ይህ የአሜሪካው ልዩ መልዕክተኛ እና ሌሎች ዲፕሎማቶች አባል የሆኑበት ቡድን የመቀለ ቆይታ፣ ከመንግሥት በኩል ትችት ገጥሞታል። በዚህም የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንት አማካሪ ሆኑት አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ቡድኑ “ለሰላም ውይይት ግፊት ከማድረግ ይልቅ የህወሓትን ቅድመ ሁኔታዎች በማሟላት እና ህወሓትን ማባበል ላይ አትኩሯል” በማለት ዲፕሎማቶቹ ምላሽ ያገኙ ጉዳዮችን ማንሳታቸውን ተችተዋል።

አምባሳደር ሐመር፣ ደብረ ጽዮን (ዶ/ር)፣ አምባሳደር ጃኮብሰን እና አቶ ጌታቸው

የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛው አምባሳደር ማይክ ሐመር ኃላፊነቱን ከተረከቡ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ባደረጉት በዚህ የመጀመሪያ ጉዟቸው ማጠናቀቂያ ላይ “አሜሪካ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነትን ባከበረ ሁኔታ አሜሪካ ኢትዮጵያን ለመደገፍ ያላትን ፍላጎት መግለጽ እፈልጋለሁ” ማለታቸውን በአዲስ አበባ የአሜሪካ ኤምባሲ ባወጣው መግለጫ ላይ ጠቅሷል። ሐመር ጨምረውም የሁለቱን አገራት የጋራ ጥቅም በሚያስጠብቅ ሁኔታ ሰላም ለማምጣት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ለመነጋገር ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ጋር የመወያየት ዕድል ማግኘታቸውን አመለክተዋል።

እንዲሁም “ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን እና ኢትዮጵያ ስላላት የምጣኔ ሀብታዊ ልማት ዕቅድን በተመለከተ የበለጠ ተረድቻለሁ” በማለት በአፍሪካ ኅብረት አማካይነት በሚደረግ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ሁሉንም የአባይ ተፋሰስ አገራትን ከሚጠቅም ስምምነት ላይ መደረስ እንሚቻል ገልጸዋል። በኢትዮጵያ፣ በሱዳንና በግብፅ መካከል ያለመግባባት ምንጭ የሆነው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ጉዳይ የልዩ መልዕክተኛው ጉዞ አንድ አጀንዳ ሲሆን፣ አምባሳደር ሐመር ወደ አዲስ አበባ ከማቅናታቸው በፊት በግብፅ ቆይታ ማድረጋቸው ይታወቃል። የልዑካን ቡድኑ በመጪው ዓመት ታኅሣሥ ወር ላይ በአሜሪካ አዘጋጅነት በሚካሄደው የአሜሪካ እና የአፍሪካ አገራት ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ እንድትሳተፍ ግብዣ ማቅረቡም ተገልጿል።

ከልዩ መልዕክተኛው ጋር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ያናገሩት በአዲስ አበባ የአሜሪካ ጉዳይ ፈጻሚ አምባሳደር ትሬሲ ጃኮብሰን፣ ለአሜሪካ-አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ የዋይት ሐውስ ግብዣን ለኢትዮጵያ ማቅረባቸው ተጠቅሷል። የኢትዮጵያ በዚህ ጉባኤ ላይ መሳተፍ ለዓለም አቀፋዊ ተግዳሮቶች በጋራ መፍትሔ ለመሻት በሚደረገው ጥረት ውስጥ የኢትዮጵያን እና የአሜሪካ እንዲሁም የአሜሪካ እና የአፍሪካን ግንኙነት የበለጠ ያጠናክራል ተብለዋል። ከአንድ ሳምንት በላይ በኢትዮጵያ ውስጥ ቆይታ ያደረጉት የአሜሪካ መንግሥት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተና አምባሳደር ማይክ ሐመር በአገሪቱ ከሚገኙ ፖለቲከኞች፣ የሰብአዊ መብት ቡድኖች፣ የሴቶች ማኅበራት መሪዎችና ከምሁራን ጋር ተገናኝተው ውይይት አድረገዋል።

ማይክ ሐመር ሁለት ዓመት ሊሞላው የተቃረበውና ከፍተኛ ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳትን ያስከተለው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ከተጀመረ በኋላ በአሜሪካ መንግሥት ከተሾሙት የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኞች ሦስተኛው ናቸው። ከሐመር በፊት በቦታው የነበሩት የአሜሪካ ከፍተኛ ዲፕሎማቶች ጦርነቱ በተባባሰበት ጊዜ በተደጋጋሚ ወደ ኢትዮጵያ እና ወደ አካባቢው አገራት ጉዞ ያደረጉ ቢሆንም አስካሁን ይህ ነው የሚባል በይፋ የሚታወቅ ውጤት ሳያገኙ ነው ቦታቸውን የለቀቁት።

ምንጭ – ቢቢሲ

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *