የአፍሪካ ኅብረት ብቻ!

አምባሳደር ሬደዋን ሁሴን ጨምረውም የኢትዮጵያ መንግሥት ከትግራይ ኃይሎች ጋር የሚያደርገውን ንግግር የሚመራ የአፍሪካ ኅብረት ብቻ ነው ሲሉ ቁርጥ ያለ የፌደራል መንግሥቱን አቋምም አንጸባርቀዋል። ከዚህ ቀደም የፌደራሉ መንግሥት ከትግራይ ኃይሎች ጋር የሚደረገውን ንግግር መምራት ያለበት የአፍሪካ ኅብረት እንዲሆን ፍላጎት እንዳለው ገልጾ ነበር። የትግራይ ኃይሎች በበኩላቸው ድርድሩን በበላይነት የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እንዲመሩት ጠይቀው ነበር።

የአፍሪካ ኅብረት የቀድሞውን የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆን ልዩ መልዕክተኛ አድርጎ ከአዲስ አበባ መቀለ ተደጋጋሚ ጉዞ አድርገው ጥረት ቢያደርጉም ውጤት ማምጣት አልቻሉም። እንዲያውም የህወሓት መሪዎች በአፍሪካ ኅብረት ላይ ጠንከር ያለ ወቀሳን በማቅረብ፣ የኬንያ መንግሥት የአሸማጋይነት ሚናውን እንዲይዝ ፍላጎታቸውን ገልጸዋል። ማክሰኞ ዕለት ወደ መቀለ የተጓዙት ምዕራባውያን ከፍተኛ ዲፕሎማቶች ግን በአህጉራዊው ድርጅት መሪነት የሚካሄድን ንግግር ለመደገፍ ዝግጁ መሆናቸውን በመግለጫቸው ላይ አመልክተዋል።

መቀለ ላይ የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ማይክ ሐመር፣ የአውሮፓ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አኔት ዌበር እንዲሁም በኢትዮጵያ የካናዳ እና የጣሊያን አምባሳደሮች ከህወሓት ከፍተኛ አመራሮች ጋር መወያየታቸው ይታወሳል። ልዩ መልዕክተኞቹ እና አምባሳደሮቹ ከመቀለ ጉዟቸው መልስ በትግራይ ክልል ተቋርጠው የሚገኙትን መሠረታዊ አገልግሎቶችን ለመጠገን በፌደራል መንግሥቱ ለሚላኩ ባለሙያዎች የደኅንነት ዋስትና የሚሰጥ ደብዳቤ ከህወሓት ሊቀ መንበር ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) መቀበላቸውን ገልጸዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የትግራይ ኃይሎች በተባበሩት መንግሥታት የተቋቋመውን የሰብዓዊ መብቶች ባለሙያዎች ኮሚሽንን ተችተዋል። የትግራይ ኃይሎች ባውጡት መግለጫ ኮሚሽኑ ከትግራይ አስተዳደር ጋር “ሆነ ብሎ ትርጉም ያለው ግንኙነት አልፈጠረም” ያሉ ሲሆን ይህም፤ መተማመን እንዳይኖር ሊያደርግ ይችላል ብለዋል። ይህ ኮሚሸን በተመድ የተቋቋመው ከሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ጋር በተያያዘ የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን እንዲመረምር ነው። ኮሚሽኑ ከሐምሌ 18/2014 ዓ. ም. እስከ ሐምሌ 24/2014 ዓ. ም. በአዲስ አበባ ቆይታ ያደረገ ሲሆን፤ ወደ ትግራይ ግን አልተጓዘም።

የድርድር ፍላጎት

ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ የተጀመረውን የእርስ በእርስ ጦርነት ለማብቃት በመንግሥትም ሆነ በህወሓት በኩል ድርድር ለማድረግ ፍላጎት ይኑር እንጂ እስካሁን ሁለቱ ወገኖች በይፋ ፊት ለፊት አልተገናኙም። የፌደራሉ መንግሥት ከትግራይ ኃይሎች ጋር የሚደረገውን ውይይት የሚመራ ሰባት አባላት ያሉት እና በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን የሚመራ ኮሚቴ አዋቅሮ ሥራ መጀመሩን ማስታወቁ ይታወሳል።

የትግራይ ኃይሎችም ከኢትዮጵያ መንግሥት አመራሮች ጋር በኬንያ መንግሥት አሸማጋይነት በሚካሄድ ድርድር ላይ ለመሳተፍ ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል። የህወሓት ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ የትግራይ ኃይሎችን የሚወክል በከፍተኛ ሥልጣን ደረጃ የሚገኙ አባላት ያሉት ልዑክ መዘጋጀቱንና ለድርድር ለመላክ ዝግጁ እንደሆኑ አሳውቀዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት ድርድሩ በአህጉራዊው ድርጅት እንዲመራ ጽኑ ፍላጎት እናዳለው በተደጋጋሚ ያሳወቀ ሲሆን፣ የህወሓት አመራሮች ግን ከአፍሪካ ኅብረት ይልቅ ተሰናባቹ የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ አሸማጋይ እንዲሆኑ እንደሚፈልግ መግለጹ ይታወሳል።

ባለፈው ሳምንት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ከፍተኛ ዲፕሎማት ሞሊ ፊ ለአሜሪካ ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ የሰሜን ኢትዮጵያውን ጦርነት ለማስቆም የታቀደው ድርድር በኬንያ ምርጫ መጓተቱን መናገራቸው ይታወሳል። ዲፕሎማቷ በቀጣይ ሳምንት በኬንያ የሚካሄደው ምርጫ ከተጠናቀቀ በኋላ ድርድሩ ይጀመራል የሚል ተስፋ እንዳላቸው መናገራቸውን ኤኤፍፒ ዘግቦ ነበር።

ምንጭ – ቢቢሲ