የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እና የግብፁ አቻቸው አብዱል ፋታህ አል ሲሲ ቅዳሜ ሐምሌ 9/2014 ሳዑዲ አረቢያ ውስጥ በተገናኙበት ወቅት በታላቁ ሕዳሴ ግድብና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ መወያየታቸው ተነገረ። በመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ጉብኝት እያደረጉ ያሉት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ባይደን ሳዑዲ አረቢያ ውስጥ እየተካሄደ ከሚገኘው የአረብ አገራት ጉባኤ በተጓዳኝ ከግብፁ ፕሬዝዳንት አል ሲሲ ጋር ተወያይተዋል። የሁለቱ መሪዎች ውይይትን በተመለከተ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ዋይት ሐውስ እና የግብፅ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ባወጡት መግለጫ ላይ፣ መሪዎቹ የአገሮቻቸው የጋራ በሆኑ ጉዳዮች ላይ መነጋገራቸውን ጠቁመዋል።

በመሪዎቹ ውይይት ከተደረጉባቸው ጉዳዮች መካከል ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ እየገነባችው ያለው ታላቁ የሕህዳሴ ግድብ አንዱ ነበር ተብሏል። ፕሬዝዳንት አል ሲሲ አገራቸው የግድቡን የውሃ ሙሌትና ቀጣይ ሥራ በተመለከተ የግብፅን የውሃ ዋስትና በሚያስከብር ሁኔታ “አሳሪ ሕጋዊ ስምምነት እንዲደረስ” ያላትን ጽኑ አቋም ለባይደን መግለጻቸውን ጽህፈት ቤታቸው አመልክቷል። ፕሬዝዳንት ባይደንም አሜሪካ የግብፅን የውሃ ዋስትና እንደምትደግፍ እንዲሁም ለአካባቢው ሰላምና ብልጽግና አስተዋጽኦ የሚያደርግ፣ የሁሉንም ወገኖች ጥቅም የሚያስከብር ዲፕሎማሲያዊ መፍትሔ ላይ እንዲደረስ እንደሚፈልጉ መናገራቸውን ከዋይት ሐውስ የወጣው መግለጫ ጠቅሷል።

ጨምሮም ሁለቱ መሪዎች ባለፈው ዓመት መስከረም ላይ “በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት መግለጫ ላይ እንደተጠቀሰው እና በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት” በግድቡ ሙሌትና ቀጣይ ሥራ ላይ ሳይዘገይ ከስምምነት የመደረሱን አስፈላጊነት መናገራቸውን ከአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት የወጣው መግለጫ አመልክቷል። አሜሪካ የሕዳሴው ግድብን በተመለከተ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን ጨምሮ በከፍተኛ ባለሥልጣናቷ አማካይነት በኢትዮጵያ፣ በግብፅና በሱዳን መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ለማሸማገል ጥረት ስታደርግ መቆየቷ ይታወሳል።

ኢትዮጵያ ዋሽንግተን ሲካሄድ የነበረውንም ድርድር ያቋረጠችበት ምክንያት በግብጽ ፍላጎት ታዛቢ እንዲሆኑ የገቡት አሜሪካና የዓለም ባንክ ለግብጽ ከመወገን አልፈው የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን ላይ ጫና ለማሳደር ሞክረዋል በማለት ኢትዮጵያ መውቀሷ የሚታወስ ነው። አሜሪካ፣ የዓለም ባንክ ከግብጽ ጎን ቆመው ነበር በተባለው በዚህ ድርድር ላይ ከመጀመሪያው ሙሌት በኋላ ኢትዮጵያ ለምትጠቀመው ውሃ ለግብጽ የተጠራቀመ የውሃ ጉድለት ማካካሻ እንድትሰጥ የሚያስገድድ እንደሆነም ተገልጾ ነበር። ይህንንም ተከትሎ ኢትዮጵያ የግብጽ ሃሳብ በአባይ ወንዝ ላይ ተፈጥሯዊ መብት እንዳይኖራት ወይም ምንም ዓይነት የውሃ ልማት ያልተገነባበት ፍሰት እንዲኖር የሚጠብቅ ነው በማለትም ትተቻለች።

ኢትዮጵያ አምስት ቢሊዮን የሚጠጋ ዶላር አውጥታ እየገነባችው ያለው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ወደ መጠናቀቁ እየተቃረበ ሲሆን፤ የግድቡ ግንባታ ሲጠናቀቅ በአፍሪካ ካሉ ግዙፍ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች ሁሉ ቀዳሚው ይሆናል ተብሏል። ግብፅና ሱዳን አሳሪ ስምምነት ሳይደረግ የግድቡ ውሃ ሙሌት እንዳይካሄድ በተደጋጋሚ ቢወተውቱም ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ዓመታት በሁለት ዙር ውሃውን በመሙላት፣ በዚህ ዓመትም ሦስተኛውን ዙር ሙሌት እንደምታከናውን አሳውቃለች። ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት እየገነባችው ያለው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ካሉት 13 ተርባይኖች መካከል አንዱ ባለፈው የካቲት ወር ኃይል ማመንጨት መጀመሩን ይፋ አድርጋለች።

ግድቡ ሙሉ ለሙሉ ተገንብቶ ሲጠናቀቅ ከ5 ሺህ ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም አለው። የመካከለኛ ምሥራቅ ጉዟቸውን ከእስራኤል ጀምረው ወደ ሳዑዲ አረቢያ ያመሩት ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ጅዳ ውስጥ ከፕሬዝዳንት አል ሲሲ ጋር በተገናኙበት ጊዜ፣ ከታላቁ የሕዳሴ ግድብ በተጨማሪ ስለአካባቢው እና ዓለም አቀፍ ወቅታዊ ጉዳዮች እንዲሁም በሁለቱ አገራት መካከል ስለሚደረጉ የትብብር መስኮች ተወያይተዋል። ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ በግብፅ ባለው የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ምክንያት ግንኙነታቸው ተቀዛቅዞ እንደነበር ይታወሳል።

ምንጭ – ቢቢሲ

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *