የምዕራብ ኢትዮጵያዋ ክልል ጋምቤላ በዋና ከተማዋ የሰዓት እላፊ ገደብ መጣሉን የክልሉ መንግሥት አስታወቀ። ክልሉ እንደገለጸው የሰዓት እላፊውን መጣል ያስፈለገው በጋምቤላ ከተማ ውስጥ ካለው ሁኔታ ጋር በተያያዘ “ሕገወጥ እንቅስቃሴዎችን ለመቆጣጠር” መሆኑን የጋምቤላ ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ያወጣው መግለጫ አመልክቷል። ከአንድ ወር በፊት ሰኔ 07/2014 ዓ.ም በሽብርተኝነት የተፈረጀው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትና የጋምቤላ ነጻነት ግንባር ታጣቂዎች በጋምቤላ ከተማ ላይ ጥቃት ሰንዝረው ለሰዓታት የከተማዋን የተወሰነ ክፍል ተቆጣጥረው እንደነበር ይታወሳል።

በወቅቱም የክልሉ የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት እርምጃ ታጣቂዎቹን ከከተማዋ ማስወጣት የቻሉ ሲሆን፣ ከጥቃቱ ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች መሞታቸው ተነግሮ ነበር። ይህንን ጥቃት ተከትሎም በዚያው ሰሞን በክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አማካይነት የተከሰተውን የሰላም መደፍረስ ለመቆጣጠር የምሽት የእንቅስቃሴ ገድብ ቢጣልም፣ ቁጥጥሩ የላላ እንደነበረ የኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊው አቶ ኡገቱ አዲንግ አመልክተዋል።

በክልሉ ዋና ከተማ ላይ ታጣቂዎች ከፈጸሙት ጥቃት ከአንድ ወር በኋላ ደግሞ ከትናንት ሐሙስ ሐምሌ 07/2014 ዓ.ም. ጀምሮ በጥብቅ ተግባራዊ የሚሆን ሰዓት እላፊ መጣሉ ተገልጿል። ይህንንም ተከትሎ በጋምቤላ ከተማ ውስጥ በተጣለው ሰዓት እላፊ ከአምቡላንሶች እና ከፀጥታ ኃይሎች ተሽከርካሪዎች በስተቀር፣ ማንኛውም የሰዎች እና የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ከምሽቱ 2 ሰዓት እስከ ንጋቱ 11፡30 ድረስ ገደብ ተጥሎባቸዋል። ይህ በጋምቤላ ከተማ የተጣለው የሰዓት እላፊ ገደብ አስከ መቼ እንደሚቆይ የተቀመጠ የጊዜ ገደብ የለም።

የኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊው እንደሚሉት በአሁኑ ወቅት በጋምቤላ ከተማ ያለው ሁኔታ ሰላማዊ መሆኑን ገልጸው፣ የክልሉ የፀጥታ ኃይሎችም የተጠናከረ ጥበቃ እያደረጉ መሆኑን አመልክተዋል። ባለፈው ሳምንት ከሐምሌ 01/2014 ዓ.ም. ጀምሮ የጋምቤላ ክልል አጎራባች የሆነው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልም በዋና ከተማው አሶሳ በተመሳሳይ የሰዓት እላፊ ገደብ መጣሉ ይታወሳል።

በአሶሳ ከተማ የተጣለው የሰዓት እላፊ ከጋምቤላው በተለየ ለተሽከርካሪዎችና ለእግረኞች የተለያየ ሰዓት ገደብ የጣለ ሲሆን፣ ተሸከርካሪዎች ከምሽቱ 2 ሰዓት እስከ ንጋት 12 ሰዓት እንዲሁም እግረኞች ከምሽት 3 ሰዓት እስከ ንጋት 12 ድረስ መንቀሳቀስ እንደማይችሉ ተገልጿል። ባለፈው ወር በጋምቤላ ከተማ በታታቂዎች ከተፈጸመው ጥቃት ጋር በተያያዘ በምዕራብ ኦሮሚያ ከሚንቀሳቀሰው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እና በክልሉ አለ ከሚባለው የጋምቤላ ነጻነት ግንባር በኩል የጋምቤላ ክልል የፀጥታ ስጋት እንዳለበት ይነገራል።   በተጨማሪም ከደቡብ ሱዳን ጋር የሚዋሰነው የጋምቤላ ክልል ከጎረቤት አገር በሚመጡ ታጣቂዎች በሚፈጸሙ ተደጋጋሚ ጥቃቶች ምክንያት ግድያና የከብቶች ዘረፋ ያጋጥመዋል።

ምንጭ – ቢቢሲ

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *