በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ውስጥ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች፡
በኦሮሚያ ክልል በሚንቀሳቀሰው የሸኔ ታጣቂ ቡድን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጥቃቶች እየደረሱ ይገኛሉ፡፡ በእነዚህም አሰቃቂ ጥቃቶች በርካታ ቁጥር ያላቸው ንጹሀን ሰዎች ላይ ሞት፣ የአካል ጉዳት፣ ንብረት ውድመት እና ሌሎችም የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች እየተፈጸሙ ይገኛሉ፡፡ መንግስት መሰል ድርጊቶች እንዳይፈጸሙ ቀድሞ የመከላከል እና የዜጎችን ደህንነት እና ሰብዓዊ መብቶች የማስከበር ተቀዳሚ ሀላፊነት ያለበት ቢሆንም ይህ ሳይሆን በመቅረቱ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ውስጥ በርካታ ቁጥር ያላቸው ንጹሀን ሰዎች ላይ አሰቃቂ ጥቃቶች እየደረሱ ይገኛሉ፡፡ ሰኔ 27 ቀን 2014 ዓ.ም በቄለም ወለጋ ለምለም ቀበሌ በሚገኙ መንደር 20 እና 21 ውስጥ በሸኔ ታጣቂ ቡድን በተፈጸመ ጥቃት በርካታ ሰዎች መሞታቸውን እና 72 ሰዎች በጅምላ እንደተቀበሩ፣ ይህ ጥቃት የብሔር ማንነትን መሰረት ያደረገ ሲሆን ጥቃቱ በተፈጸመባቸው አካባቢዎች ውስጥ ይኖሩ የነበሩት የአማራ ብሔር ተወላጆች እንደሆኑ፣ በደረሰው አሰቃቂ ጥቃት ከሞቱት ሰዎች መካከል በርካታውን ቁጥር የሚይዙት ሴቶች እና ህጻናት መሆናቸውን፣ የመንግስት የጸጥታ አካላት በአሁኑ ሰዓት በአካባቢው እንደሚገኙ እና ይህ ጥቃት የደረሰባቸው ሰዎች ብዙዎቹ ንጹሀን ገበሬዎች መሆናቸውን ኢሰመጉ ካሰባሳቸው መረጃዎች ለመረዳት ችሏል፡፡
ተያያዥ የህግ ግዴታዎች፡
ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች መግለጫ አንቀጽ 3 “እያንዳንዱ ሰው በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደህንነቱ የመጠበቅ መብት” እንዳለው ያረጋግጣል። ኢትዮጵያ ፈርማ የተቀበለችው የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃል–ኪዳንም በአንቀጽ 6 (1) እና 9 (1) ላይ ይህንኑ መብት በማረጋገጥ፣ መንግሥታት በቃል–ኪዳኑ የተረጋገጡትን መብቶች በግዛታቸው የማክበር፣ የማስከበርና የማሟላት ግዴታ እንዳለባቸውም በአንቀጽ 2 (1) እና 2(2) ይደነግጋል። የአፍሪካ የሰዎችና የሕዝቦች መብቶች ቻርተር አንቀጽ 4 ማንኛውም ግለሰብ በሕይወት የመኖር መብቱና የአካሉ ደህንነት ሊከበርለትና ሊጠበቅለት እንደሚገባና እነዚህን መብቶቹን በዘፈቀደ ሊነፈግ እንደማይችል ተመላክቷል። የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ–መንግሥት አንቀጽ 14 “ማንኛውም ሰው ሰብዓዊ በመሆኑ የማይደፈርና የማይገሰስ በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደህንነትና የነጻነት መብት አለው” ሲል ይደነግጋል። በተመሳሳይ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ–መንግስት አንቀፅ 15 ማንኛውም ሰው በሕይወት የመኖር መብት እንዳለውና በሕግ ከተደነገገው ውጪ ሕይወቱን ሊያጣ እንደማይችል በግልፅ ደንግጓል። ከዓለም አቀፍ፣ አህጉር አቀፍ እና ሀገር አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌዎች እንደምንረዳው መንግስት የሰዎችን ሰብዓዊ መብቶች ማክበር፣ ማስከበር እና የማሟላት ሀላፊነት አለበት፡፡ ይህ ሳይሆን ሲቀር እና በመንግስት ቸልተኝነት የዜጎች ሰብዓዊ መብቶች ሳይከበሩ ሲቀሩ ዋነኛ ተጠያቂ ሊሆን የሚገባው መንግስት ነው፡፡
የኢሰመጉ ጥሪ፡
ኢሰመጉ ሰኔ 27 ቀን 2014 ዓ.ም በቄለም ወለጋ ለምለም ቀበሌ በሚገኙ መንደሮች ውስጥ የተፈጸመውን ማንነትን መሰረት ያደረገ ጥቃት እያወገዘ:
- የፌደራል እና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስታት በኦሮሚያ ክልል የሚኖሩ ሰዎችን ሰብዓዊ መብቶች የማስከበር ሀላፊነት ስላለባቸው በሸኔ ታጣቂዎች በተደጋጋሚ እየደረሱ ላሉ ጥቃቶች ቀዳሚ ተጠያቂ እንደሆኑ በመረዳት በአስቸኳይ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት እነዚህን በኦሮሚያ ክልል በአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ እየተፈጸሙ ያሉ የብሔር ማንነትን መሰረት ያደረጉ አሰቃቂ ጥቃቶችን እንዲያስቆሙ፣
- ሰኔ 11 ቀን 2014 ዓ.ም ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ እና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሚዥንጋ ወረዳ ሴነ ቀበሌ ውስጥ እና ሰኔ 27 ቀን 2014 ዓ.ም በቄለም ወለጋ ለምለም ቀበሌ በሚገኙ መንደሮች ውስጥ የብሔር ማንነትን መሰረት ያደረገ አሰቃቂ ጥቃት የፈጸሙ አካላት ላይ ገለልተኛ የሆነ ምርመራን በማከናወን ለህግ እንዲያቀርብ፣
- መንግስት በተደጋጋሚ በአካባው የሚደርሱ የሰበዓዊ መብቶች ጥሰቶችን በመቆጣጠር የአካባቢውን ሰላም እንዲያረጋግጥ እና በአካባቢው በቂ የጸጥታ አካላትን በማሰማራት መሰል ጥቃቶች ዳግም እንዳይፈጸሙ እንዲከላከል፣
- የሀይማኖት አባቶች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የማህበረሰብ አንቂዎች፣ ጋዜጠኞች፣ ሲቪል ማህበራት እና ሰብዓዊነት የሚሰማው በሙሉ በተደጋጋሚ እየደረሱ ላሉ አሰቃቂ ጥቃቶች የፌደራል እና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ትኩረት ሰጥተው በመስራት የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶች የማስከበር ሀላፊነታቸውን እንዲወጡ በመወትወት የበኩላቸውን እንዲወጡ ኢሰመጉ ጥሪውን እያቀረበ በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ተጨማሪ የምርመራ ስራን በማከናወን ሰፋ ያለ ዘገባን እንደሚያዘጋጅ ከወዲሁ ይገልጻል፡፡