በኢትዮጵያ የአፋር እና የአማራ ክልሎች የተፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች እና ዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ሕግ ጥሰቶች ላይ የተደረገ ምርመራ ሪፖርት – የቀጠለ

127. በዚህ ክፍል ኢሰመኮ ምርመራ ባደረገባቸው በአማራ እና አፋር ክልሎች አካባቢዎች የተፈጸሙ የዘፈቀደ እስር፣ ጠለፋ እና አስገድዶ መሰወር ክስተቶችን ይዳሰሳል። ኮሚሽኑ በተለያዩ አካባቢዎች ሲቪል ሰዎች ከጦርነቱ ተሳታፊ ኃይሎች ጋር ባላቸው ወይም አላቸው ተብሎ በተገመተ ግንኙነት ምክንያት መያዛቸውን፣ መታገታቸውን እና አንዳንዶቹ እስካሁንም ድረስ አለመገኘታቸውን የሚያሳዩ መረጃዎች ደርሰውታል። አንዳንዶቹ የታገቱ ሰዎች በያዛቸው ወይም ባገታቸው ኃይል ተገድለዋል፤ አካል ጉዳት ደርሶባቸዋል። ስለሆነም ይህ ክፍል በዚህ ሪፖርት ውስጥ በጦርነቱ ሂደት በሲቪል ሰዎች ላይ የደረሱ ጉዳቶችን ከሚዳስሰው ክፍል ጋር አብሮ የሚታይ ነው። 

የሕግ ማዕቀፍ
128. የዘፈቀደ እስር በዓለም አቀፍ ሰብአዊ መብቶች እና የሰብአዊነት ሕግ ድንጋጌዎች የተከለከለ ተግባር ነው። ሰዎች ነፃነታቸውን የሚገፈፉበት ሂደት የሕግ የበላይነትን ባከበረ መልኩ መከናወን አለበት። የዘፈቀደ እስር የሕግ መሰረት የሌለው እስር ሲሆን ተገቢነት የሌለው፣ ፍትሀዊ ያልሆነ እና ሕጋዊ ሥነ ሥርአቶችን ያልተከተለ እስርን ይጨምራል።
44 ብሔርን፣ ፆታን፣ ዕድሜን እና ሌሎች መድሏዊ ምክንያቶችን መሰረት ያደረገ እስር ደግሞ በመሰረታዊነት የዘፈቀደ እስር እንደሆነ ይቆጠራል።
129. በጦርነት ወቅት ከሰላም ጊዜ በተለየ ሁኔታ በጦርነቱ ተሳታፊ የሆኑ ሰዎች ሊያዙ እንደሚችሉ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች እና የሰብአዊነት ሕግ ድንጋጌዎች ቢያስቀምጡም፣ በዚህ ወቅትም ቢሆን የሕጋዊነት፣ የጥብቅ አስፈላጊነትና ተመጣጣኝነት እና ከመድልዎ ነፃ መሆን የሚሉትን የሰብአዊ መብት መርሆዎችን ባከበረ መልኩ መሆን ይኖርበታል።

130. ጠለፋ እና አስገድዶ መሰወር በሕይወት ከመኖር፣ ከጭካኔ እና ኢሰብአዊ አያያዝ የመጠበቅ፣ ፍትሕ የማግኘት እና ሌሎች መሰረታዊ የሰብአዊ መብቶች እና የሰብአዊነት ሕግ ጥበቃዎችን የሚጥሱ ተግባራት ናቸው። ዓለም አቀፋዊ ባልሆነ ጦርነት ጊዜ የጦርነቱ ተሳታፊ የሆኑ ኃይሎች ጠለፋ እና አስገድዶ መሰወርን ለመከላከል የተያዙ ሰዎችን የመመዝገብ እና ደኅንነታቸውን የማስጠበቅ ግዴታ አለባቸው።መንግሥታት በማንኛውም ጊዜ ሰዎችን በታጠቁ ኃይሎች እና ቡድኖች ከአስገድዶ መሰወር እና ከመታገት የመጠበቅ ኃላፊነትም አለባቸው።

የምርመራ ግኝቶች
131. የትግራይ ኃይሎች ቁጥጥራቸው ስር በነበሩ እና ኮሚሽኑ ምርመራ ባደረገባቸው አካባቢዎች እገታ እና አስገድዶ መሰወር ፈጽመዋል። በተለይም የመንግሥት አመራር፣ ሚሊሺያ ወይም ፋኖ አባል ነበራችሁ፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትንና የአማራ ልዩ ኃይልን አግዛችኋል ምግብና ውሃ ሰጥታችኋል፤ እንዲሁም የአካባቢውን አመራርና ታጣቂ ስምና ቤት አሳዩን በሚል ምክንያቶች፤ ግለሰቦችን የማገት እና የአስገድዶ መሰወር ተግባራት ተፈጽመዋል። በአማራ ክልል ወልድያ ከተማ 04 ቀበሌ የትግራይ ኃይሎች ነሐሴ 24 ቀን 2013 ዓ.ም. አንድ የ25 ዓመት ወጣትን የፋኖ ደጋፊነህ በሚል በሚኒባስ መኪና ከለቅሶ ቤት የተወሰደ ሲሆን ምርመራው እስከሚከናወንበት ቀን ድረስ ያለበት አልታወቀም።

132. በአንዳንድ አካባቢዎች መረጃ እንዲሰጡ በሚል በትግራይ ኃይሎች የተያዙ ሰዎች በግዳጅ ጦር መሳሪያና ጥይት እንዲሸከሙ እና ሌሎች አገልግሎቶች እንዲሰጡ ተደርገዋል። በአማራ ክልል ዳቦ ከተማ ኅዳር 4 ቀን 2013 ዓ.ም. የአካባቢውን አመራርና የሚሊሺያ ስምና ቤት ጠቁም በማለት የተያዘ አንድ ሰው ቀኑን ሙሉ በገመድ ከዛፍ ጋር እንደታሰረ፣ ከለሊቱ ስድስት ሰዓት ተፈቶ ባዶ ቤት ያለምግብ ማደሩን እና በነጋታው ሌላ ከተያዘ የከተማው ነዋሪ ጋር ተወስደው ወታደሮቹ በሚሄዱበት ሁሉ የጦር መሳሪያና ጥይት እንዳሸከሟቸው እና ለብዙ ቀናት ውሃ ካስቀዷቸው በኋላ በተያዙ በሶስተኛ ሳምንታቸው እንደተለቀቁ ለኮሚሽኑ አስረድተዋል።

133. በኃይል ታግተው ከተወሰዱ በኋላ የተለቀቁ የተወሰኑ ሲቪል ሰዎች ሲኖሩ በሌላ በኩል ከታገቱ በኋላ ኢሰብአዊ ድርጊት የተፈጸመባቸው እና የተገደሉም ይገኙበታል። ለአብነትም የትግራይ ኃይሎች አጣዬ ከተማን ኅዳር 6 ቀን 2014 ዓ.ም ሲቆጣጠሩ 01 ቀበሌ ነዋሪ የነበሩ አንድ ነጋዴ ቤት በመግባት እና ግለሰቡን በማገት ለ5 ቀናት ከቆዩ በኋላ ኅዳር 10 ቀን 2014 ዓ.ም. አጣዬ ከተማ ቀበሌ 01 ልዩ ስሙ ኤፌሶን ቁጥር 2 ትምህርት ቤት ውስጥ ‹‹ፋኖ ትቀልባለህ፣ ወታደር ታበላለህ፣ ቤትህ የወታደር ካምፕ ነው›› በሚል ምክንያት አስረው ካቆዩአቸው በኋላ ለኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች አሳልፈው ሰጥተዋቸው ኅዳር 13 ቀን 2014 ዓ.ም. ጃራ ዎታ በሚባል ቦታ ላይ ተገድለዋል።
134. በሌላ በኩል ነሐሴ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. በአፋር ክልል በርሀሌ ወረዳ አላ እና አስጉቢ ቀበሌዎች ከሚገኙት ሦስት መንደሮች (ኩሱርቱ፣ አሰዳ እና አድአርዋ) አካባቢ ከትግራይ ክልል ጋር አዋሳኝ በሆነ ቦታ በሚገኝ ኩሬ ውሃ ለመቅዳት 27 አህያ ጭነው የሄዱ 10 ልጃገረዶች በድንበሩ አቅራቢያ የነበሩ የትግራይ ታጣቂዎች ታግተው ከሰዓታት ቆይታ በኋላ ተለቀዋል።
135. የትግራይ ኃይሎች ተቆጣጥረዋቸው በነበሩ አካባቢዎች የተያዙበት ምክንያት እና አሁን የሚገኙበት ሁኔታ የማይታወቅ ሲቪል ሰዎችም ይገኛሉ። ለምሳሌ ጥቅምት 23 ቀን 2014 ዓ.ም. በአፋር ክልል ቡርቃ ቀበሌ ሙዴና የተባለ ቦታ ለገበያ የመጡ 6 ግለሰቦች እና ሌላ 2 የቡርቃ ቀበሌ ነዋሪ ነጋዴዎች ከነፍየሎቻቸው መኪና ላይ ተጭነው የተወሰዱ ሲሆን ይህ ምርመራ እስከተደረገበት ጊዜ ድረስ ቤተሰቦቻቸው ያሉበትን እንደማያውቁ ገልጸዋል። ከአፋር ክልል ካሳጊታ ከተማ በትግራይ ኃይሎች ተይዘው ከተወሰዱ ሰዎች ውስጥ የአንዱ እህት የሆነች ሴት እንደገለጸችው፦

“ጥቅምት 23 ቀን 2014 ዓ.ም. ካሳጊታ ከተማ ላይ በነበረው ጦርነት ምክንያት ሸሽተን አራ ቀበሌ ከገባን በኋላ ወንድሜ ሲፊ ከሚባል ቦታ አፋሮች ወደ ካሳጊታ ከተማ ገብተዋል የሚል ወሬ ሰምቶ ሄዶ በመጥፋቱ እሱን ፍለጋ ወጣን። የትግራይ ኃይሎች በሰፈሩበት ወራኢሉ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አጠገብ የወንድሜን ጫማ አግኝቼ ወንድሜ የት አለ? ብዬ ስጠይቃቸው የምናቀው ነገር የለም፣ ወንድምሽን እኛ አልገደልንም፣ ከዚህ ሂዱ ካልሆነ እንገድላችኋለን ብለው ሲያስፈራሩኝ የወንድሜን ጫማ ይዤ ተመለስኩ ። አሁን ወንድሜ እንደሞተ ነው የሚሰማኝ” በማለት አስረድታለች።

136. በሌላ በኩል ከትግራይ ኃይሎች ቁጥጥር ነፃ በወጡ አካባቢዎች ‹‹የፀጥታ ስጋት ናቸው፣ ከትግራይ ኃይሎች ወይም ከኦነግ ሸኔ ጋር ተባብረዋል፣ ወይም መረጃ አቀብለዋል›› በሚል ምክንያት በፌደራል የፀጥታ አካላትና በአማራ እና አፋር የፀጥታ ኃይሎች ቁጥራቸው የበዛ ሰዎች ታስረዋል። በተለይም የኢፌዴሪ መንግሥት ጥቅምት 23 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በመላው አገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ማወጁን ተከትሎ ለፀጥታ አካላት ከሽብር ቡድኖች ጋር ይተባበራሉ ተብለው ምክንያታዊ በሆነ መልኩ የተጠረጠሩ ሰዎችን ይዞ የማቆየት ስልጣን በመሰጠቱ ጦርነቱ ከነበረባቸው ስፍራዎች ውጪ በሚገኙ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው በተለይ የትግራይ ተወላጅ የሆኑ ሲቪል ሰዎች ከምክንያታዊነት በራቀ እና በመድሎ ላይ በተመረኮዘ መልኩ ተይዘው ታስረዋል።

137. ከእነዚህ እስሮች ውስጥ ጥቂቶቹ በሚመለከታቸው የፀጥታ አካላት መረጃ መሰረት የተፈጸሙ ሲሆን አብዛኛዎቹ ግን ከህብረተሰቡ ተገኘ በተባለ ጥቆማ መሰረት በአብዛኛው የትግራይ ብሔር ተወላጅ የሆኑ ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል። እድሜያቸው ከ60 ዓመት በላይ የሆኑ ወንዶች እና ሴቶች አረጋውያን፣ ሕጻናት ልጆች በማጥባት ላይ የነበሩ ሴቶች፣ የአዕምሮ ህመም ያለባቸው እና ተከታታይ ሕክምና የሚያስፈልጋቸው ሰዎችም ጭምር ተይዘው ታስረዋል። ፖሊስ ጣቢያዎች እና የተያዙ ሰዎችን የማቆያ ስፍራዎች የተጣበቡ፣ በቂ መጸዳጃ፣ አየር እና ብርሃን በማያገኙ የነበሩ ሲሆን በቂ የምግብ እና የጤና አገልግሎት አልነበራቸውም። በአብዛኛው አካባቢዎች የታሰሩ ሰዎችን
ጉዳይ የማጣራት ሂደት እጅግ የዘገየ ወይም ያልተጀመረ ነበር።

138. ከታሰሩት ሰዎች ውስጥ ጋዜጠኞች የሚገኙበት ሲሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከመታወጁ ጥቂት ቀናት በፊት ጀምሮ ቢያንስ 16 ጋዜጠኞች በኦሮሚያ፣ በፌደራል እና በአዲስ አበባ ፖሊስ በቁጥጥር ስር ውለዋል። ከነዚህ ውስጥ የታሰሩበት ስፍራ ለቀናት ያልታወቀ፣ ለረጅም ጊዜ በቤተሰብ መጎብኘት ያልቻሉ ሰዎች ይገኙበታል። ይህ ሪፖርት በሚፃፍበት ወቅት ታስረው የነበሩት አብዛኛዎቹ ጋዜጠኞች የተለቀቁ ቢሆንም የተወሰኑት በእስር ላይ ነበሩ።
139. በአጠቃላይ ከአስቸኳይ ጊዜ ከአዋጁ ጋር በተያያዘ ሰዎችን የመያዝ ሁኔታ በተወሰነ መጠን በሂደት እየተሻሻለ መጥቶ የነበረ ቢሆንም፤ ጦርነቱ በነበረባቸው አካባቢዎችም ሆነ በሌሎች ስፍራዎች በፌደራል እና በክልል መንግሥታት ሰዎችን በቁጥጥር ስር በማዋል ረገድ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መተግበር ባለበት መንገድ በተለይም “የጥብቅ አስፈላጊነት፣ ተመጣጣኝነት እና ከመድልዎ ነፃ መሆን” የሚሉትን የሰብአዊ መብት መርሆዎችን ባከበረ መልኩ አልተተገበረም።

ተፅዕኖ
140. ኮሚሽኑ ምርመራ ባደረገባቸው አካባቢዎች የሚገኙ የዘፈቀደ እስር፣ ጠለፋ እና አስገድዶ መሰወር የደረሰባቸው ተጎጂዎች እና የተጎጂ ቤተሰቦች ለከፍተኛ አካላዊ፣ ስነልቦናዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ቀውስ ተዳርገዋል፤ እንዲሁም በህብረተሰቡ መካከል ያለውን ማኅበራዊ መስተጋብር ላይም አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል። በተለያዩ አካባቢዎች በጦርነቱ ተሳታፊ ኃይሎች አሁንም የተያዙ ሰዎች የሚገኙ ሲሆን፣ የተሰወሩ ሰዎች ቤተሰቦቻቸው የደረሱበትን አሁንም ድረስ ማወቅ ባለመቻላቸው በጭንቀት ውስጥ ይገኛሉ።

ማጠቃለያ
141. ጦርነቱ በተካሔደባቸው የአማራ እና የአፋር ክልል አካባቢዎች የትግራይ ኃይሎች ዓለም አቀፍ የጦር ወንጀልን እና በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀልን ሊያቋቁም በሚችል መልኩ የእገታ እና አስገድዶ መሰወር ተግባራትን ፈጽመዋል። በሌላ በኩል የፌዴራል፣ የአማራ እና የአፋር ክልል የፀጥታ ኃይሎች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውድ ውስጥም ቢሆን መጠነ ሰፊ የዘፈቀደ እስር ፈፅመዋል።

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *