ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ውስጥ ሸኔ በዜጎች ላይ ጭፍጨፋ መፈጸሙን በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ ገለጹ።  ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትዊተር ገጻቸው ላይ ዛሬ ሰኞ ሰኔ 27/2014 ዓ.ም. አመሻሽ ላይ እንዳሰፈሩት መንግሥት ሸኔ የሚለው እና ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ በሚጠራው ቡድን “በኦሮሚያ ክልል፣ ቄለም ወለጋ ውስጥ የሚገኙ ዜጎች ጭፍጨፋ ተፈጽሞባቸዋል” ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተፈጸመ ስላሉት ጭፍጨፋ ምንም አይነት ዝርዝር መረጃ አላሰፈሩም።

ተቃዋሚው ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክረሲ ፓርቲ “ጭፍጨፋው በኦሮሚያ ክልል፣ ቄለም ወለጋ ዞን፤ ሮቢት ገበያ ወረዳ መቻራ ለምለም ቀበሌ” ውስጥ መፈጸሙንና በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸውን ገልጿል። ቢቢሲ ስለጥቃቱ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር የሆኑትን ዶክተር ዳንኤል በቀለን ጠይቆ እንደተረዳው ተቋሙ ጥቃት ስለመፈጸሙ እንደሚያውቅ ተናግረዋል። ነገር ግን ስለተከሰተው አጠቃላይ ሁኔታ ዝርዝር ለማግኘት ከጥቃቱ ከሸሹ ሰዎች መረጃ እያሰባሰቡ እንደሆነ እና የተፈጸመውን ጥቃት ኮሚሽኑ እየተከታተለው እንደሆነ አመልክተዋል።

ከሁለት ሳምንት በፊት በምዕራብ ወለጋ ጊምቢ፣ ቶሌ ቀበሌ ውስጥ ነዋሪ በሆኑ የአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ ጭፍጭፋ ተፈጽሞ በመቶዎች የሚቆጠሩ መገደላቸው ይታወሳል። በዚህ ጥቃት መንግሥት ከ330 በላይ መገደላቸውን የገለጸ ሲሆን ሌሎች ወገኖች ደግሞ አሃዙን ስድስት መቶ ያደርሱታል። ለተፈጸመው የጅምላ ግድያ ከጥቃቱ የተረፉና መንግሥት የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትን ተጠያቂ ሲያደርጉ፣ ቡድኑ ግን ክሱን ማስተባበሉ ይታወሳል።    ቀደም ካለው ጭፍጨፋ ከሁለት ሳምንት በኋላ ሌላ ጥቃት በምዕራብ ኦሮሚያ ውስጥ መፈጸሙን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አመልክተው፣ ታጣቂውን ቡድን ለጥቃቱ ተጠያቂ አድርገዋል።

“የፀጥታ አካላት ከሚያደርሱበት ዱላ የፈረጠጠው የሸኔ ቡድን በምዕራብ ወለጋ በዜጎች ላይ አደጋ እያደረሰ በመሸሽ ላይ ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ “በኦሮሚያ ክልል፣ ቄለም ወለጋ ውስጥ የሚገኙ ዜጎች ጭፍጨፋ ተፈጽሞባቸዋል” ብለዋል። ጨምረውም በተፈጸመው ጭፍጨፋ ምክንያት “በዜጎቻችን ላይ በደረሰው መከራ እያዘንን፤ ይሄንን አሸባሪ ቡድን እስከመጨረሻው ተከታትለን ከሕዝባችን ጋር እናስወግደዋለን” ብለዋል።

የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ባለፈው ዓመት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከህወሓት ጋር በሽብርተኛ ቡድንነት የተፈረጀ ሲሆን፣ በምዕራብ እና ደቡብ ኦሮሚያ ውስጥ ከተፈጸሙ ጥቃቶችና ግድያዎች ጋር ስሙ በተደጋጋሚ ሲነሳ ቆይቷል። ይህ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያለተጨማሪ መረጃ ተፈጸመ ባሉት “ጭፍጨፋ” የደረሰው ጉዳት ዝርዝር ባይታወቅም፣ በሰው ላይ ከፍ ያለ ጉዳት ሳይርስ እንዳልቀረ ይታመናል። ጥቃቱ በምዕራብ ኦሮሚያ ውስጥ በሁለት ሳምንት ውስጥ የተከሰተ ሁለተኛው መሆኑ ነው።

ምንጭ – ቢቢሲ

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *