የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ለኢትዮጵያ ያቋቋመው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መርማሪ ኮሚሽን ወደ አዲስ አበባ ለመግባት ፈቃድ አገኘ። የፈረንሳዩ ዜና ወኪል (ኤኤፍፒ) እንደ ዘገበው ኮሚሽኑ ወደ አዲስ አበባ ለመግባት ከኢትዮጵያ መንግሥት ፈቃድ አግኝቷል። የኮሚሽኑ መርማሪዎች ወደ ክልሎች መንቀሳቀስ እንዲችሉ የኢትዮጵያ መንግሥት ፈቃድ እንዲሰጣቸው መጠየቃቸውን የዜና ወኪሉ ዘገባ ያመለክታል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነት የተፈጸሙ የጦር ወንጀሎችን እና የመብት ጥሰቶችን የሚመረምር ቡድን አባላትን የሰየመው በመጋቢት ወር ነበር።

በወቀቱም ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ መርማሪ እንዲቋቋም የተላለፈውን ውሳኔ እንደማትቀበለውና አንዳንዶች የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔን ለፖለቲካ ዓላማ ማራመጃነት ሲጠቀሙበት በድጋሚ ማየቷ እንዳሳዘናት ገልጻ ነበር። ይህ የመርማሪ ኮሚሽን የማዋቀር እርምጃም በውስጥ ጉዳይዋ ለመግባት የሚደረግ ሙከራ መሆኑን በመጥቀስ እንደማትቀበለውና እንደማትተባበርም ገልጻ ነበር። የተባበሩት መንግሥታት ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ላለፉት ጥቂት ወራት የደረሰበትን ምርመራ አስመልክቶ ረቡዕ ዕለት ለምክር ቤቱ ሪፖርት ማቅረቡ ተሰምቷል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በትግራይ ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ተቀስቅሶ በአጎራባቾቹ የአማራና የአፋር ክልሎች በተዛመተው የእርስ በርስ ጦርነት የተፈጸሙ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች፣ የስደተኛ ሕጎችና ሌሎች ጥሰቶችን ለማጣራት በሚል ነው ኮሚሽኑን ያቋቋመው። የኮሚሽኑ አባል የሆኑት ስቴቨን ራትነር ለፈረንሳዩ የዜና ወኪል አንደተናገሩት ሐምሌ ወር አጋማሽ ላይ ወደ አዲስ አበባ የመሄድ እቅድ አላቸው። የዚህ ጉዟቸው ዓላማም ወደ ሌሎች ክልሎች “ያልተገደበ” የእንቅስቃሴ ፈቃድ ማግኘት መሆኑን ገልፀዋል።

የኮሚሽኑ አባላት በግንቦት ወር ከኢትዮጵያ የፍትህ ሚኒስትር ጋር ተገናኝተው ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት ፈቃድ እንዲሰጣቸው ጥያቄ ማቅረባቸውን የኮሚሽኑ ሊቀመንበር ካሪ ቤሪ ሙሩንጊ ተናግረዋል። ሙሩንጊ አክለውም “ለኢትዮጵያ መንግሥት ያቀረብነው አዲስ አበባን የመጎብኘት ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ አግኝቷል” ብለዋል። “በአዲስ አበባ በሚኖረን ምከክር የሰብዓዊ መብት ጥሰት ወደ ተፈፀመባቸው አካባቢዎች መርማሪዎቻችን እንዲገቡ፣ ከጥቃት የተረፉትን እና የጥቃቱ ሰለባዎችን እንዲሁም ምስክሮችን እንዲያገኙ ፈቃድ ይሰጠናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን” ሲሉ አክለዋል።

 በጄኔቫ የኢትዮጵያ መንግሥት ተወካይ የሆኑት ዘነበ ከበደ ቆርቾ፣ ኢትዮጵያ ያላት ስጋት ከግምት ውስጥ ከገባ “የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ ተግባራዊ መንገዶች አሉ” ሲሉ ተናግረዋል። አክለውም ኢትዮጵያ “አዲስ ምዕራፍ እየከፈተች” እንዲሁም መንግሥት “ግጭቱ በሠላማዊ መንገድ የሚቋጭበትን” መንገድ እየፈለ መሆኑን ገልፀዋል። ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ ትግራይ ውስጥ ተከስቶ ወደ አማራና አፋር ክልሎች የተዛመተው ደም አፋሳሽ ጦርነት ሺዎችን በመቅጠፍና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን በማፈናቀል መጠነ ሰፊ ሰብዓዊ ቀውስ አድርሷል።

በኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ የተሳተፉ ሁሉም ወገኖች በተለያየ ደረጃ እንደ ጦር ወንጀል ሊቆጠሩ የሚችሉ ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች፣ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ሕግና የስደተኛ ሕግ ጥሰቶችን መፈፀማቸውን የመብት ተቆርቋሪዎች ያወጧቸው ሪፖርቶች ያመለክታሉ።

ጥቂት ስለ ኮሚሽነሮቹ

  • ካሪ ቤቲ ሙሩንጊ (ኬንያ)

በሽግግር የፍትህ ሂደቶች የካበተ ሥራ ልምድ ያላቸው ካሪ ቤቲ በተጨማሪም በሴቶች ሰብአዊ መብቶች፣ በሥርዓተ-ፆታ፣ በሕገመንግስት እና በአስተዳደር ሕጎች ላይ በርካታ ሥራዎችን አበርክተዋል። በአሁኑ ጊዜ የኬንያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጠበቃ እና ተሟጋች የሆኑት ግለሰቧ በአመፆችና በግጭቶች ውስጥ የሴቶችን ሰብአዊ መብት ከማስከበር ጋር በተያያዙ ሥራዎች ላይ አተኩረዋል። ከምክር ቤቱ ድረገፅ ባገኘነው መረጃ መሰረት ካሪ ቤቲ የኬንያ እውነት ፍትህ እና እርቅ ኮሚሽን ምክትል ሊቀመንበር እና ኮሚሽነር ሆነው በአውሮፓውያኑ 2009 እሰከ 2010 ባለው ጊዜ አገልግለዋል።

በተጨማሪም በዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት ለተጎጂዎች የትረስት ፈንድ የዳይሬክተሮች ቦርድ የአፍሪካ ተወካይ፣ በደቡብ ሱዳን የጋራ ክትትል እና ግምገማ ኮሚሽን ከፍተኛ የሽግግር የፍትህ አማካሪነት ሰርተዋል። እንዲሁም በሰብዓዊ ምክር ቤቶች ምክር ቤት በተመሰረተው በወረራ ለተያዘው የፍልስጥኤም ግዛት ገለልተኛ የምርመራ ኮሚሽን አባልም ነበሩ።

  • ስቲቨን ራትነር (አሜሪካ)

ስቲቨን ራትነር በአሁኑ ወቅት በሚቺጋን የሕግ ትምህርት ቤት የሕግ ፕሮፌሰር ናቸው። ፕሮፌሰር ራትነር ትምህርታቸውና ምርምራቸውና ዓለም አቀፍ ሕግ፣ በዓለም አቀፍ የሰብአዊ ሕግጋት፣ የፀረ-ሽብርተኝነት ስልቶች፣ በሰብአዊ መብት ረገጣ ተጠያቂነት እና የውጭ ኢንቨስትመንትን በሚመለከት የድርጅት እና የመንግሥት ተግባራት ላይ ያተኩራል።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጥላ ስር የካምቦዲያ ባለሙያዎች ቡድን እና በሲሪላንካ የተጠያቂነት የባለሙያዎች ቡድን አባል በመሆን አገልግለዋል። በተጨማሪም ከአውሮፓውያኑ 2008-2009 ባለው ጊዜ ወቅት በጄኔቫ የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ የሕግ ክፍል ውስጥ ሰርተዋል። በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በዓለም አቀፍ ሕግ አማካሪ ኮሚቴ ውስጥ እና በተለያዩ የግልግል ዳኝነት ላይ የዓለም አቀፍ ኢንቨስትመንት ባለሙያም ሆነው መስራታቸውን የምክር ቤቱ መረጃ ጠቁሟል።

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *