በኢትዮጵያ የአፋር እና የአማራ ክልሎች የተፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች እና ዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ሕግ ጥሰቶች ላይ የተደረገ ምርመራ ሪፖርት – የቀጠለ

116. ጦርነቱ በተካሄደባቸው አንዳንድ አካባቢዎች በተለይ የትግራይ ኃይሎች የአካባቢው ነዋሪ የሆኑ ሲቪል ሰዎችን ኢ-ሰብአዊ በሆነ እና ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ ማሰቃየታቸውን፤ መደብደባቸውን እና ማንገላታታቸውን የኮሚሽኑ ምርመራ ያሳያል። የትግራይ ኃይሎች ታጣቂዎች ሲቪል ሰዎችን መረጃ፣ ገንዘብ እና የደበቃችሁትን የግል የጦር መሳሪያ ስጡን በሚሉ እና ሌሎች ምክንያቶች ደብድበዋል፤ አሰቃይተዋል፤ በተወሰኑ አጋጣሚዎችም ከደበደቡ እና ካሰቃዩ በኃላ ተጎጂዎቹ ላይ ግድያን ፈጽመዋል።

የሕግ ማዕቀፍ
117. ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት እና የሰብአዊነት/ጦርነት ሕጎች የጭካኔ እና ማሰቃየት ተግባራትን በየትኛውም ሁኔታ በጥብቅ ይከለክላሉ።
 በመሆኑም በሰላም ጊዜም ሆነ በጦርነት ወቅት ተዋጊ ኃይሎች ጥበቃ በተደረገላቸው ሲቪል ሰዎች ላይም ሆነ በሌሎች በጦርነቱ ተሳታፊ የሆኑ የተያዙ ወይም በሌላ ሁኔታ በቁጥጥራቸው ስር የገቡ ተዋጊዎችም ላይ ምንም ዓይነት የጭካኔ ተግባር መፈጸም አይችሉም። በተ.መ.ድ የጭካኔ፣ ኢሰብአዊና አዋራጅ አያያዝና ቅጣት ክልከላ ስምምነት በተመለከተው ትርጓሜ መሰረት የጭካኔ እና የማሰቃየት ተግባር (torture) በሰዎች ላይ ሆን ተብሎ መረጃን ወይም የእምነት ቃልን ለማግኘት፣ በቅጣት መልክ፣ ለማስፈራራት ወይም ለማስገደድ ወይም በሌላ መድሎ ላይ በተመሰረተ ማንኛውም ምክንያት የሚፈጸም በአካል ወይም በሥነ ልቦና ላይ ከፍ ያለ የስቃይ ስሜትን የሚያደርስ ድርጊት እንደሆነ ይገልጻል።

118. በትግራይ ኃይሎች እና በመንግሥት መካከል በተካሄደው ዓለም አቀፋዊ ያልሆነ ጦርነትን በሚመለከቱት የሕግ ማዕቀፎችም የትኛውም ታጣቂ ኃይሎች ሰፊ እና ስልታዊ በሆነ መልኩ ድርጊቱን የፈጸሙ እንደሆነ ድርጊቱ የጦር ወንጀል (War Crimes) እና/ወይም በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል (Crimes against Humanity) ሊሆን እንደሚችል ያመላክታል።

የምርመራው ግኝቶች
119. ሐምሌ 3 ቀን 2013 ዓ.ም. የትግራይ ኃይሎች በአፋር ክልል ፈንቲ ረሱ ዞን የከለዋን ከተማ ነዋሪ የሆነችን የ30 ዓመት ሴት “የመንግሥት ሰላይ ነሽ” በሚል ምክንያት በመንገድ ስትጓዝ ከያዟት በኃላ ለሁለት ተከታታይ ቀናት ከባድ ድብደባ ፈጽመዋባታል። ተጎጂዋ የደረሰባትን ለኮሚሽኑ
በሚከተለው መንገድ አስረድታለች፦

“ከፈተሹኝ በኋላ አሳድረውኝ በጠዋት እንደሚለቁኝ ነግረውኝ ተራራው ላይ ወሰዱኝ። ሲነጋ እንዲለቁኝ ስጠይቃቸው አንደኛው በደረቅ እንጨት ዱላው ተሰባብሮ እስኪያልቅ ድረስ ደጋግሞ በላዬ ላይ አወረደብኝ። የአብይ መረጃ ነሽ፣ እያሉ እየተቀባበሉ በመሳሪያ ሰደፍ፣ በእርግጫ፣ በጥፊ እና በእንጨት እየደበደቡ እና እንደሚገሉኝ እየዛቱ ሁለት ቀን አቆዩኝ። ከዛም በመኪና ጭነው ወደ ከለዋን መልሰውኝ ለ5 ቀናት በቆርቆሮ ቤት ውስጥ አስረው አቆዩኝ” ብላለች። በተጎጂዋ ትከሻ ላይ የድብደባ ጠባሳዎችን ኮሚሽኑ ተመልክቷል።

120. በደቡብ ወሎ ዞን የተሁለደሬ ወረዳ በቀበሌ 017፣ 14 ነዋሪዎች ከነሐሴ 27 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ነሐሴ 29 ቀን 2013 ዓ.ም. በትግራይ ኃይሎች በደረሰባቸው ድብደባ እና ማሰቃየት ለጉዳት እንደተዳረጉ ተጎጂዎች፣ የቀበሌው አስተዳዳሪዎች እንዲሁም በአካባቢው የነበሩ ምስክሮች ለኢሰመኮ አስረድተዋል። ድብደባው እና ማሰቃየቱ ሲፈጸም የነበረው በዋነኝነት በክላሽ መሳሪያ ሰደፍ፤ በብረት እና ከብረት በተሰሩ መግረፊያዎችና በእንጨት ዱላዎች ሲሆን ድብደባው በአብዛኛው የሚደረገው ሰዎቹን በማሰር ነው። በተጨማሪም በዚሁ ቀበሌ በነሐሴ 28 ቀን 2013 ዓ.ም. የአካባቢው ነዋሪዎችን ሚሊሺያ ወይም ፖሊስ ናችሁ በማለት የትግራይ ኃይሎች በቁጥጥር ስር እንዳዋሏቸው እና ድብደባ ካደረሱባቸው በኋላ ከመካከላቸው 1 ነዋሪን በጥይት ተኩሰው እንደገደሉ የዓይን እማኞች እና ከሟች ጋር በቁጥጥር ስር ውሎ የነበሩና ከጥቃቱ ያመለጡ ነዋሪዎች አስረድተዋል። 

121. ሐምሌ 29 ቀን 2013 ዓ.ም. በአማራ ክልል ወረባቡ ወረዳ ቀበሌ 020 የትግራይ ኃይሎች የ20 ዓመት ወጣት እንስሳትን በመጠበቅ ላይ እያለ “የሶዶማ አካባቢ ተዋጊዎችን ትመስላለህ” በሚል ድብደባ እና ማሰቃየት ካደረሱበት በኋላ በጥይት ተኩሰው ገድለውታል። የትግራይ ኃይሎች በወረዳው 6 ቀበሌዎች ውስጥ በ10 ሰዎች (8 ወንድ እና 2 ሴቶች) ላይ ድብደባ እና የአካል ጉዳት አድርሰዋልየአካል ጉዳት ከደረሰባቸው መሀከል በቀበሌ 018 ነዋሪ የሆነ የ30 ዓመት ወጣት ሐምሌ 25 ቀን 2013 ዓ.ም የትግራይ ኃይሎች ከቤቱ በመውሰድ እግሩን እና እጁን ገልብጠው በማሰር እስከ ነሐሴ 30 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ ድብደባ የፈጸሙበት ሲሆን በድብደባውም ጉዳት እንደደረሰበት ለማረጋገጥ ተችሏል። በተመሳሳይ ቀበሌ ነዋሪ የሆነ የ40 ዓመት ጎልማሳ በትግራይ ኃይሎች በሰደፍ እና በዱላ ድብደባ እደተፈጸመበት እንዲሁም ሊገሉት በጥይት ተኩሰው እንደሳቱት አስረድቷል።

122. የትግራይ ኃይሎች በጋሸና ከተማ በቆዩበት ወቅት የአማራ ልዩ ኃይልና መከላከያን አብልታችኋል፣ አጠጥታችኋል፣ መሳሪያ አላችሁ አስረክቡ፣ ብር አላችሁ አምጡ፣ የሚሊሺያ ቤት አሳዩን በሚል ምክንያት ሲቪል ሰዎችን አሰቃይተዋል። ለአብነት በከተማው ቀበሌ 013 ነዋሪ ከሆኑት አንድ ግለሰብ ቤት ኅዳር 3 ቀን 2014 ዓ.ም ከምሽቱ 4፡00 ሰዓት “ብር እንዳላችሁ ሰምተናል ስጡን” ሲሉ ነዋሪዎቹ ብር እንደሌላቸውና መስጠት እንደማይችሉ በመመለሳቸው ከባድ ድብደባ ከፈጸሙባቸው በኋላ የቤቱን አባወራ ለብቻ በአቅራቢያ ወደሚገኝ ወንዝ በመውሰድ ልብሱን አስወልቀው በውኃ እየደፈቁ ከደበደቡት እና በሚስማር እግሩን ሁለት ቦታ ከወጉት በኋላ ብልቱን በካራ ተልትለውታል። ተጎጂው በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ለኮሚሽኑ ሲገልጽ፦

“ልብሴን አስወልቀው ዘቅዝቀው በውሃ ሲደፍቁኝ ራሴን ሳትሁ፤ ሲደበደቡኝ ህመሙ አይሰማኝም ነበር። በሚስማር ሁለቱን እግሬን ሲበሱኝም ምንም አልመለስሁላቸውም። በኋላ ግን ብልቴን በካራ ሲተለትሉኝ ህመሙ አቃተኝና ብሩ አለ፤ ውሰዱት ብዬ ከቤት ያስቀመጥኩትን 20,000 ብር ሰጠኋቸው” ብለዋል። ታጣቂዎቹ ገንዘቡን ከወሰዱ በኋላ ባለቤታቸውን ቤት ውስጥ ብር እንደነበረ ባልሽ ሲያምን አንቺ ግን የለም ብለሽ ዋሸሽን በማለት ከፍተኛ ድብደባ ፈጽመውባቸዋል።

123. በተመሳሳይ በጋሸና ከተማ 02 ቀበሌ አንድ የ65 ዓመት አረጋዊን የትግራይ ኃይሎች ታጣቂዎች ከፍተኛ ድብደባ፣ ማሰቃየትና እንግልት አድርሰውባቸዋል። ተበዳዩ የሚኖሩበት ቤት እና ለአልጋ ኪራይ በሚል በግቢያቸው ውስጥ በሰሯቸው ክፍሎች ውስጥ የትግራይ ኃይሎች ከተማዋን በተቆጣጠሩ ቁጥር እርሳቸውን ወደ አንድ ትንሽ ክፍል እንዲገቡ በማድረግ የቀረውን ቤት ሁሉ ይጠቀሙበት እንደነበር፤ በመጀመሪያ ቤታቸውን የቁስለኛ ማከሚያ ቤት እንዳደረጉት ይገልጻሉ። ሆኖም ታኅሣሥ 3 ቀን 2014 ዓ.ም. የመጡት የትግራይ ኃይሎች ታጣቂዎች ለዝርፊያ የመጡ መሆኑን እና ገንዘብ አምጣ በሚል የደረሰባቸውን እንደሚከተለው ለኮሚሽኑ አስረድተዋል፦

“ቤት መጡና ብር አምጣ አሉኝ። የለኝም ስላቸው ደበደቡኝ በሽተኛዋን ባለቤቴን ሳይቀር ክፉኛ ደበደቧት። ከዚያ ቤት ውስጥ ያለውን ነገር ሁሉ መፈተሽ ጀመሩና በሙዳይ የቆጠብነው 8500 ብር ነበር እሱን ሲያገኙት ወሰዱት። በኋላ ለኃላፊዎቻቸው ሂጄ እንዴት እንደዚህ ይደረጋል ብዬ ሳመለክት እናንተማ ከዚህ በላይም ይገባችኋል፤ ጋሸና ላይ 80 ሰው ተደፈረ 400 ሰው ተገደለ ብላችሁ ለሚዲያ ቃል ሰጥታችኋል ብሎ አስፈራራኝ” ብለዋል።

ተፅዕኖ
124. የትግራይ ኃይሎች በቁጥጥራቸው ስር በነበሩ አካባቢዎች በነዋሪዎች ላይ በተለያዩ ምክንያቶች የፈጸሟቸው የጭካኔ እና የማሰቃየት ተግባራት በተጎጂዎች ላይ ከፍ ያለ የአካል እና የሥነ ልቦና ጉዳት ያደረሱ ሲሆን ይህ በተለይ ተጎጂዎች በሕክምና እንዲረዱ የሚያስችል ነባራዊ ሁኔታ ያልነበረ ከመሆኑ አንጻር የተጎጂዎችን ስቃይ እንዲበረታ ያደረገ ነው።

መደምደሚያ
125. የትግራይ ኃይሎች በቁጥጥራቸው ስር በገቡ የአፋር እና አማራ ክልል አካባቢዎች ሲቪል ሰዎችን ላይ የጭካኔ እና የማሰቃየት ተግባር ፈጽመዋል። ለመንግሥት ኃይሎች መረጃ ታቀብላላችሁ፤ መሳሪያ አምጡ፣ ንብረት እንዳይወሰድ ተከላክላችኋል፤ በአካባቢያችሁ የመከላከያ፣ ልዩ ኃይል ወይም ፋኖ ታጣቂዊዎች የት እንዳሉ ታውቃላችሁ ወይም የነዚሁ አባላት የሆኑ ሰዎች ቤተሰብ ናችሁ በሚል እንዲሁም አካባቢዎቹን በሚቆጣጣሩበት ወቅት በትግራይ ኃይሎች ላይ ለደረሰባቸው ጥቃት ወይም የትግራይ ታጣቂዎች እና ትግራይ ላይ ለደረሰ ሞት እና ጉዳት የበቀል/አጸፋ እርምጃ መሆኑን ጭምር በግልጽ እየተናገሩ ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆኑ ሲቪል ሰዎችን ደብድበዋል፤ አሰቃይተዋል፤ ለአካል እና የሥነ ልቦና ጉዳትም ዳርገዋል።

126. ይህ በጦርነት ወቅት ሲቪል ሰዎችን ተጠቂ ወይም ዒላማ እንዳይሆኑ በዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ሕግም ሆነ በሰብአዊ መብቶች ሕግ እንዲሁም በኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ የተቀመጡ ክልከላዎችን በግልጽ የሚጥስ እና የጦር ወንጀል እንዲሁም በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል ሊሆን የሚችል ነው። 

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *