በሰሜን ኢትዮጵያ ላለው ችግር በአፍሪካ ኅብረት በኩል የሰላማዊ መፍትሔ አማራጮች እንዲታዩ ገዢው የብልጽግና ፓርቲ ውሳኔ ማሳለፉን የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ተናገሩ። ብልጽግና ፓርቲ ባለፈው ሳምንት ማብቂያ፣ የሥራ አስፈጻሚና የማዕከላዊ ኮሚቴዎቹን ስብሰባ ማድረጉን ተከትሎ በተሰጠው መግለጫ በሰሜን ኢትዮጵያ ስላለው ጦርነት እና በሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መክሮ ውሳኔ ማሳለፉ ተገልጿል። የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ እና የፍትሕ ሚኒስትርና የፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ በሰጡት መግለጫ ላይ እንደተጠቀሰው፣ በትግራይ ክልል ተቀስቅሶ ወደ ሌሎች ክልሎች ተስፋፍቶ የነበረውና መቋጫ ያላገኘው ጦርነት ሰላማዊ መፍትሔ እንዲፈለግለት ወስኗል።
በዚህም መሠረት የሰላም ንግግሩ “ሕገ መንግሥታዊነትን ባከበረ፣ የአገርን መሠረታዊ ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ” መሆን እንዳለበት ፓርቲው መወሰኑንና ሂደቱም በአፍሪካ ኅብረት መሪነት መካሄድ እንዳለበት ብልጽግና ፓርቲ ውሳኔ ማሳለፉን የፍትህ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ዐሕመድ ከጥቂት ሳምንታት በፊት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው መንግሥታቸው ጦርነቱን በሰላም ለማብቃት ፍላጎት እንዳለው ማሳወቃቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ለዚህም በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ ኮሚቴ ዝርዝር ጉዳዮችን እያጠና መሆኑን ገልጸው ነበር። ይህንንም ተከትሎ ከመንግሥት ጋር ሁለት ዓመት ሊሞላው አራት ወራት በቀረው ጦርነት ውስጥ የገባው ህወሓትም ለድርድር ዝግጁ መሆኑን ባወጣው መግለጫ አመለክቶ ነበር።
ነገርግን ህወሓት በኬንያ መንግሥት አሸማጋይነት በሚካሄድ ድርድር ላይ ለመሳተፍ ዝግጁ መሆኑን በመግለጽ፣ የአፍሪካ ኅብረት የሚጠበቅበትን ያህል አለማከናወኑን ገልጾ ተችቷኀዕ። የኅብረቱ ልዩ ተወካይ በሆኑት የቐድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ላይም ጥያቄ አንስቷል። አሁን የኢትዮጵያ ገዢ ፓርቲ ለሰላማዊ መፍትሔ በሩ ክፍት መሆኑን በገለጸበት መግለጫው ላይ ግን ድርድሩ በአህጉራዊው ድርጅት መሪነት የሚካሄድ መሆኑን ተገልጿል። ይህ የሁለቱ ወገኖች የአሸማጋይ ፍላጎት መለያየት በሰላም ጥረቱ ላይ እንቅፋት ሊያስከትል ይችላል የሚል ስጋትን ፈጥሯል።
በህወሓት በኩል የድርድሩን ሂደት የኬንያ መንግሥትን በመሪነት ያቀረበ ሲሆን በተጨማሪም የአፍሪካ ኅብረት፣ የተባበሩት መንግሥታት፣አሜሪካ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ተሳታፊ እንዲሆኑ መጠየቁ ይታወሳል። የብልጽግና ፓርቲ ሃያ ወራትን ያስቆጠረውን ጦርነት በሰላም ለማብቃት ቅድሚያ ሰጥቶ ጥረት እንደሚያደረግ በገለጸበት መግለጫው ላይ፣ “ማንኛውም ፀብ ጫሪነትና ትንኮሳዎች ካሉ አፀፋ የሚሰጡ ተቋማት ዝግጁነት እንዲጠናከር” በመወሰን የአገሪቱ የፀጥታና የደኅንነት ተቋማት በሙሉ ዝግጁነት በተጠንቀቅ እንዲቆሙ ውሳኔ ማሳለፉም ተገልጿል።
ከዚህ በተጨማሪም የፓርቲው ከፍተኛ ውሳኔ ሰጪ ኮሚቴዎች በአገሪቱ የሰላም፣የደኅንነት፣ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣በማህበራዊ፣የውጭ ግንኙነት እና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ መወያየቱን ባለሥልጣናቱ ገልጸዋል። በተጨማሪም በጋምቤላ እና በምዕራብ ወለጋ የተፈጸመው በርካታ ሰዎች በተገደሉባቸው ክስተቶች ላይ የተነጋገረው ፓርቲው፣ “የተጀመረው የሕግ ማስከበር ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል” መወሰኑንና እስካሁን በተወሰደው እርምጃም “በርካታ የሽብር ቡድኑ አባላት መደምሰሳቸውን” አቶ አደም ተናግረዋል።
ምንጭ – ቢቢሲ