የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባለፈው ሳምነት መጀመሪያና መጨረሻ በጋምቤላ ክልልና በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ የተፈጠሩ ሁነቶችን በተመለከተ ማጣራት እንዲደረግ ለሦስት አካላት ትዕዛዝ አስተላለፈ፡፡ የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ ጽሕፈት ቤት ለጤና፣ ማኅበራዊ፣ ባህልና ስፖርት ቋሚ ኮሚቴ ሰኔ 16 ቀን 2014 ዓ.ም. በጻፈው ደብዳቤ፣ በሁለቱ ክልሎች ለሚደረገው ምርመራ ሁለት ቡድኖች ማዋቀሩን አስታውቋል፡፡ በምዕራብ ወለጋው ጭፍጨፋ ‹‹እጅግ አሰቃቂ፣ አሳዛኝና በሰው ልጆች ላይ መፈጸም የሌለበት ግፍ ተፈጽሟል›› ያለው ምክር ቤቱ፣ ሒደቱን ማጣራትና ድጋፍ ማድረግ አስፈላጊ ነው ብሎ እንደሚያምን አስታውቋል፡፡ ይኼንን ለማድረግም ለቋሚ ኮሚቴው፣ ለብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽንና ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡
ቋሚ ኮሚቴው የተሰጠው ኃላፊነት በሒደቱ የደረሰው ጉዳትና የሚያስፈልገው መጠን ምን ያህል እንደሆነና አጣርቶ እንዲያቀርበ ነው፡፡ የፀጥታ አካላት ቋሚ ኮሚቴው ለሥራ በሚንቀሳቀስበት ሰዓት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ አሳስበዋል፡፡ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ደግሞ በቋሚ ኮሚቴው የሚቀርበው የጉዳት መጠን መረጃን መነሻ በማድረግ፣ አስፈላጊውን ድጋፍ በአስቸኳይ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ተላልፏል፡፡ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በአንጻሩ በሒደቱ የታዩና ከሰብዓዊ መብቶች ጋር የሚያያዙ ጉዳዮችን በማጣራት ለምክር ቤቱ እንዲያቀርብ ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡
ምክር ቤቱ ማጣራት እንዲደረግባቸው ያዘዛቸው የጋምቤላና የምዕራብ ኦሮሚያ ክልሎች ሁነቶች የተፈጸሙት በአንድ ሳምንት ውስጥ ነው፡፡ በመጀመሪያ የተከሰተው የጋምቤላ ነጻነት ግንባር (ጋነግ) እና ‹‹ኦነግ ሸኔ›› ሰኞ ሰኔ 7 ቀን 2014 ዓ.ም. የጋምቤላ ከተማን ለመቆጣጠር ከከፈቱት ጥቃት ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ ከንጋት 12 ሰዓት አንስቶ እስከ ማምሻው 11 ሰዓት በዘለቀው ጥቃት የመንግሥት ኃይሎችና ሁለቱ ታጣቂዎች ከተማ ውስጥ የተኩስ ልውውጥ ሲያደርጉ ነበር፡፡ ታጣቂዎቹ ለተወሰኑ ሰዓታት የከተማውን የተወሰኑ ክፍሎች ተቆጣጥረው የነበረ ቢሆንም በመጨረሻ የመንግሥት ኃይሎች ሙሉ ከተማውን መልሰው መቆጣጠር ችለዋል፡፡ በዚህ ክስተት ንጹኃን ሕይወታቸው ማለፉ ቢነገርም ምን ያህል ሰዎች እንደሞቱ እስካሁን ይፋ አልተደረገም፡፡
የመንግሥት ኃይሎች በታጣቂዎች የተከፈተውን ጥቃት ከተከሰተ በኋላ በየቤቱ ተደብቀዋል ያሏቸውን ታጣቂች ለመፈለግ ፍተሻ አድርገዋል፡፡ በዚህም ሒደት ከሕግ ወጪ የተፈጸመ ግድያን ጨምሮ ነዋሪዎች ለተለያዩ ለመብት ጥሰት መጋለጣቸውን የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሰኔ 10 ቀን 2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡ ኮሚሽኑ በመግለጫው ‹‹ቤት ለቤት በመሄድ ጭምር ግድያዎች እንደተፈጸሙ›› ከምስክሮችና በተንቀሳቃሽ ምስልን ጨምሮ ካሰባሰባቸው መረጃዎች እንደተረዳ ገልጿል፡፡ ሌላኛው ማጣራት እንዲደረግበት ትዕዛዝ የተላለፈበት ክስተት ከጋምቤላው ጥቃት አምስት ቀናት በኋላ ቅዳሜ ሰኔ 11 ቀን 2014 ዓ.ም. በምዕራብ ወለጋ ዞን ግምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ የተፈጸመ ነው፡፡ በዚህ ቀን ታጣቂዎች የቀበሌው ነዋሪ በሆኑ ነዋሪዎች ላይ ባደረሱት ጭፍጨፋ ከ400 በላይ ሰዎችን ስለመግደላቸው ሪፖርተር ከዓይን እማኞች ሰምቷል፡፡
ከጠዋት 2፡30 በተጀመረው ጥቃት በአብዛኛው ሴቶችና ሕጻናት ተገድለዋል፡፡ እንደ የዓይን እማኞቹ ገለጻ ታጣቂዎቹ ንፁኃንን ለመግደል ጥይትና ገጀራን የተጠቀሙ ሲሆን፣ ቤት ውስጥ ተዘግቶባቸው ከነሕይወታቸው የተቃጠሉ ሰዎች ስለመኖራቸውም እማኞች አስረድተዋል፡፡ ሪፖርተር ያነጋገራቸውና የተገደሉ ንፁኃንን የመቅበር ሥራ ላይ ተሰማርተው እንደነበር የገለጹ አንድ እማኝ ቢያንስ 582 ሰዎች አስከሬን መቀበሩን አስረድተዋል፡፡ የጊምቢው ጥቃት በአገር ውስጥ ባሻገር ዓለም አቀፍ ውግዘትንም አስከትሏል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽር ሚሼል ባችሌት ሐሙስ ሰኔ 16 ቀን 2014 ዓ.ም. ባወጡት መግለጫ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ፈጣን፣ ገለልተኛና የተሟላ ምርመራ እንዲያካሂዱ ጠይቀዋል፡፡ በመግለጫው ላይ ኮሚሽነሯ በቶሌ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑ የዓይን እማኞችን ማነጋገራቸው የተጠቀሰ ሲሆን በዚህም በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ስለመገደላቸውና ቢያንስ ሁለት ሺሕ ሰዎች ስለመፈናቀላቸው እንደተረዱ ተገልጿል፡፡
ከዚህም ባሻገር ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰዎች በጥቃቱ ጊዜ ስለ መታገታቸውና ያሉበት አለመታወቁ በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል፡፡ ኮሚሽነሯ፣ ‹‹ባለሥልጣናት ታፍነው የተወሰዱ ሰዎች ነጻነታቸውን እንዲያገኙ አስፈላጊውንና ሕጋዊ ዕርምጃ እንዲወስዱ እጠይቃለሁ፤›› ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል የምዕራው ወለጋውን ጥቃት ያወገዙ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ዓርብ ሰኔ 17 ቀን 2014 ዓ.ም. በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ውስጥ ተቃውሞ ስለማሰማታቸው ተሰምቷል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት አስራት አጸደወይን (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንደተናገሩት ተቃውሞው ከጥዋቱ 2፡30 አንስቶ ለአንድ ሰዓት የዘለቀ ነው፡፡ ተቃውሟቸውን ያሰሙ ተማሪዎች ብሔር ተኮር ጥቃቶች እንዲቆሙና መንግሥት ሕግ እንዲያስከብር መጠየቃቸውን ገለጸዋል፡፡
ምንጭ – ሪፖርተር