በምዕራብ ኦሮምቢያ ዞን፣ ጊምቢ ወረዳ፣ ቶሌ ቀበሌ ቅዳሜ ሰኔ 11፣ 2014 በታጣቂዎች በተፈጸመው ጥቃት የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ260  እስከ 320  እንደሚሆን ሮይተርስ የአካባቢውን ነዋሪዎች ዋቢ አድርጎ ዘግቧል። በመንደሮቹ የተገደሉ ነዋሪዎችን አስከሬን በመሰብሰብ በትናንትናው ዕለት በጅምላ መቀበራቸውን ቢቢሲ ከጥቃቱ ከተረፉ ነዋሪዎች ሰምቷል። በቅዳሜው ጥቃት አብዛኛው ሰለባዎች በክልሉ የሚኖሩ የአማራ ብሄር ተወላጆች መሆናቸውም ተገልጿል። አንድ የከተማዋ ነዋሪ ለሮይተርስ 260 ሰዎች ተገድለዋል ያሉ ሲሆን ሌላ ነዋሪ ደግሞ የሟቾቹ ቁጥር 320 ይደርሳል ብለዋል። ነዋሪዎቹ ለደህንነታቸው በመስጋት ስማቸውን ለመግለፅ ፈቃደኛ አለመሆናቸውም በዘገባው ተካቷል።

ቅዳሜ ዕለት በጊምቢ የተፈጸመው በዓመታት ውስጥ በሰላማዊ ዜጎች ላይ ከተፈጸሙት አስከፊ ጥቃቶች አንዱ ነው ። “እስካሁን አስከሬናቸውን ሰብስበን የቀበርናቸው 260 ሰዎች ናቸው። በእርሻ ቦታ ላይ ነው የቀበርናቸው። በአንድ መቃብር ላይ ከ50 እስከ 60 የሚሆኑ ሰዎችን ደራርበን ነው የቀበርነው” ብለዋል ነዋሪው።  ነዋሪው በጉድጓድ ውስጥ ተደብቆ ቢተርፍም በጥቃቱ አራት ወንድሞችና እህቶች እንዲሁም ሦስት የአጎት ልጆች ተገድለውበታል። ሌላኛው ነዋሪ ጥቃቱን የፈጸሙት የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አባላት መሆናቸውን ጠቅሷል።

“በአማራዎች ላይ የተፈጸመ ጭፍጨፋ ነው” ያለው ግለሰቡ፣ ጫካ ውስጥ ተደብቆ መትረፍ መቻሉንም ሮይተርስ በዘገባው አስነብቧል ። የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጥቃቱን በማስመልከት ሰኞ ከሰዓት በኋላ ባወጣው መግለጫ፣ ታጣቂዎቹ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት እንደማይፈጽሙና የጊምቢው ጥቃትም መንግሥት አደራጅቶታል ባለው ኢ-መደበኛ ኃይል የተፈጸመ ነው ብሏል። ጨምሮም ይህ ክስተት በገለልተኛ ወገን እንዲጣራ ጠይቋል።

ከጥቃቱ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥታቸው ድርጊቱን እንደማይታገስ በመግለፅ በትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል። “በንጹሃን ዜጎች ላይ በሕገ ወጥ እና በኢ-መደበኛ ኃይሎች የሚደርስ ጥቃት እና መተዳደሪያን ማውደም ተቀባይነት የለውም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቤኒሻንጉል እና ኦሮሚያ ክልሎች፣ ዋና ዓላማቸው ኅብረተሰቡን ማሸበር በሆነ አካላት የተፈጸመው የሰው ልጆችን ሕይወት የሚቀጥፍ ዘግናኝ ድርጊት የምንታገሰው አይደለም” ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም “ጥቃት በደረሰባቸው አካባቢዎች ሰላም እና ደህንነትን መመለስ አሁንም ቅድሚያ የምንሰጠው ተግባራችን ነው” ሲሉ በትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል። ጥቃቱን ተከትሎም የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት በትናንትናው ዕለት ሰኔ 13፣ 2014 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ የሽብር ጥቃት ሲል የፈረጀው ሲሆን ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖችና ለደረሰው ጉዳት የተሰማውን ሃዘን ገልጿል። መንግሥት ይህንን ጥቃት የፈጸመው ሸኔ ብሎ የሚጠራው ወይም የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ሲሆን “የሕግ የበላይነትን የማስከበር ተልዕኮ ያነጣጠረበት የሸኔ የሽብር ቡድን እየደረሰበት የሚገኘውን ከፍተኛ ሽንፈት ለመሸፈን የጥፋት በትሩን ወደ ንጹሃን አዙሯል” ብሏል።

በዚህም በቅርቡ በጋምቤላ በደምቢዶሎና በጊምቢ ከተሞች ላይ ጥቃቶች መሰንዘሩንና ይህም ጥቃት በመክሸፉ በጊምቢ ወረዳ ላይ የበቀል ጥቃት መፈጸሙን ገልጿል። የመንግሥት ኮሚዪኒኬሽን መግለጫ የሞቱ ሰዎችን ቁጥር ባይጠቅስም የበርካታ ንጹሃን ሕይወት በግፍ ተቀጥፏል እንዲሁም ንብረትም ወድሟል ብሏል። ይህ ጥቃት የቡድኑን ትክክለኛ ማንነት ያሳያል ያለው የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን መግለጫ የሕግ የበላይነት የማስከበር ተልዕኮው እንደሚቀጥልም አፅንኦት ሰጥቷል። “የጥፋት ኃይሉ ሙሉ በሙሉ እንዲደመሰስ በመላው የክልልና የፌደራል የጸጥታ ኃይሎች የተጀመረው የተቀናጀ ተልዕኮ ተጠናክሮ ይቀጥላል” ብሏል።

በቶሌ አጎራባች ቀበሌ ብሔርንና ሃይማኖትን መሰረት ያደረገ የጅምላ ግድያ መድረሱን በመግለፅ ያወገዘው ደግሞ የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ነው። በዚህ ጥቃት በመስጂዶች የተጠለሉትም ጭምር የጥቃቱ ሰለባ ሆነዋል ብሏል ምክር ቤቱ። በአሁኑ ወቅት ለሕይወታቸው ፈርተው የሚገኙ ዜጎችም መንግሥት በአስቸኳይ ከለላ እንዲያደርግላቸው እንዲሁም መንግሥት በተደጋጋሚ የሚደርሰውን ጥቃት እንዲያስቆምና ወንጀሉን የፈጸሙ አካላት ወደ ፍርድ እንዲቀርቡ መደረግ አለበት በማለት አሳስቧል።

በተጨማሪም ምክር ቤቱ መንግሥት የሕዝቦችን ደህንነት የማረጋገጥ ኃላፊነቱን ይወጣም ሲልም ምክር ቤቱ ጠይቋል። በተለያየ ጊዜ በአማራ ሕዝብ ላይ የሚደርሰውን ጭፍጨፋ እንደ ተፈጥሯዊ እና መደበኛ ክስተት እየተወሰደ ነው ያለው ደግሞ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ነው። በባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት መዋቅራዊ እና ሥርዓታዊ በሆነ መንገድ በአማራ ሕዝብ ላይ ግድያ፣ መፈናቀል፣ ሃብት እና ንብረቱን ማውደም እና መንጠቅ ሲፈጸም ቆይቷል ብሏል። በአሁኑም ወቅት በተለይ በኦሮሚያ እና በቤንሻንጉል ክልሎች በተከታታይ መጠነ ሰፊ ጭፍጨፋ ደርሷል ያለው አብን እነዚህንም ጥቃቶች “የዘር ማፅዳት ወንጀል ናቸው” ሲል ፈርጇቸዋል።

ከሰሞኑም በጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአማራ ብሔር ተወላጆች፣ ሕፃናት እና ሴቶችን ጨምሮ መጨፍጨፋቸውን እና ከሞት የተረፉትም ነዋሪዎች በከፍተኛ ስጋት እንደሚገኙ ገልጿል። የፌደራሉ መንግሥትም ሆነ ጥቃቱ የሚፈጸምባቸው የክልል መንግሥታትም እርምጃዎችን ለመውሰድም ሆነ ጥቃቱን በዘላቂነት ለማስቆም ዝግጁነት እና ፈቃደኝነት የላቸውም ሲልም አብን በትናንትናው ዕለት ባወጣው መግለጫ ወቅሷል። መንግሥት በአሁኑ ወቅት የተሻለ አቅም ገንብቻለሁ ቢልም በሕዝቡ ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ማስቆም አልቻለም ብሏል።

“ መንግሥት ተደጋጋሚ ጥቃት በሚፈጸምባቸው አካባቢዎች ዜጎችን ከጥቃት ለመከላከል የሚያስችል አቅም የሌለው ከሆነ ደግሞ ፣ ችግሩን አምኖ ሊቀበል እና ለጥቃት ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎችን በማደራጀት ፣ በማስታጠቅ እና አመራር በመስጠት ራሳቸውን እንዲከላከሉ የሚያስችል አስቻይ ሁኔታዎችን መፍጠር ይጠበቅበታል።” ብሏል አብን በመግለጫው። በተጨማሪም አብን በዚህ ጥቃት የተሳተፉ ታጣቂዎች እና በመንግሥት ውስጥ መዋቅር አሉ ያላቸው ተባባሪዎቻቸው ለሕግ እንዲቀርቡ ጠይቋል። ከጥቃቱ የተረፉ ነዋሪዎችም በከፍተኛ ስጋት ውስጥ የሚገኙ ስለሆነ አፋጣኝ ድጋፍ እና ሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርሳቸውም አሳስቧል።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)ም በተለያዩ አካባቢዎች በዜጎች ላይ እየደረሱ ያሉ ጭፍጨፋዎችን በማውገዝ በትናንትናው ዕለት መግለጫ አውጥቷል። “የመንግሥት ተቀዳሚ ተግባር የዜጎችን ደኅንነት ማስጠበቅ ሲሆን በዚህ ወቅት መንግሥት የዜጎችን ደኅንነት ማስጠበቅ ሥራውን በጥንቃቄ እንዲሰራ እንጠይቃለን።” ብሏል። በተጨማሪም በዜጎች ሕይወት ላይ እንዲህ አይነት ጥቃት የሚፈጽሙ አካላት ላይ የማያዳግም እርምጃ መንግሥት ሊወስድ ይገባል ሲልም አሳስቧል።

ኢትዮጵያ ውስጥ በብሔር ላይ ያተኮረ ግድያ በቅርብ አመታት ውስጥ ባይጀመርም ባለፉት አራት አመታት በሰላማዊ ዜጎች ላይ የደረሰውን ያህል ግፍ እንዳልታየ በመጥቀስ ደግሞ መግለጫ ያወጣው እናት ፓርቲ ነው። በባለፉት ጥቂት ቀናት በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የደረሱ ጭፍጨፋዎች አገሪቱ ያንዣበባት ትልቅ አደጋ ማሳያ ነው ያለው እናት ፓርቲ ብሔራዊ የሃዘን ቀን ሊታወጅ ይገባል ብሏል።

የጥቃቱ ሰለባዎች የድረሱልን ጥሪ በክልል አስተዳደሮች ችላ ተብሏል ያለው ፓርቲው፣ እነዚህ ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ አካላት ከሥልጣናቸው እንዲነሱና ተጠያቂም እንዲደረጉ ጠይቋል። በተለያዩ ጊዜዎች በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች አለመቆማቸውንም በማየት መፍትሔ ያለውን ሃሳብ ጠቁሟል። “መንግሥት እንዲህ ያሉ ዘር ተኮር ፍጅቶች በአገራችን እየተፈጸሙ መሆናቸውን አምኖ መከላከል ካልቻለ እገዛ ለሚያደርጉ ዓለም አቀፍ አካላት ጥሪ ያድርግ” ሲል አሳስቧል።

ምንጭ – ቢቢሲ

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *