በንጹሀን ሰዎች ላይ የተፈጸሙ ግድያዎች፡
በጋምቤላ ክልል ሰኔ 07 ቀን 2014 ዓ.ም በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ቡድኖች ጥቃት መፈጸማቸውን እና በዚህም ጥቃት የሰዎች ህይወት ማለፉን፣ የአካል ጉዳት መድረሱን እና ንብረቶች መውደማቸውን፣ በተለያዩ አካባቢዎች በነበረው የተኩስ ልውውጥ ከመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እንዲሁም ከታጣቂ ቡድኑ በተተኮሱ ጥይቶች በርካታ ቁጥር ያላቸው ንጹሀን የአካባቢው ነዋሪዎች መሞታቸውን እና አካላቸው ላይ ጉዳት መድረሱን ኢሰመጉ ከአካባቢው ካሰባሰባቸው መረጃዎች ለመረዳት ችሏል፡፡ በጋምቤላ ክልል ሰኔ 7 ቀን 2014 ዓ.ም ጋምቤላ ከተማ ውስጥ አንድ ወጣት የጸጥታ አካላት ዩኒፎርምን በለበሱ ሰዎች አጁን ታስሮ አሰቃቂ በሆነ መንገድ በጥይት ተደብድቦ ከህግ አግባብ ውጪ በሆነ መንገድ (extra judicial killing) መገደሉን፣ በዚሁ ዕለት በተደራጁ ቡድኖች በርከት ያሉ ንጹሀን ሰዎች ከታጣቂ ቡድኑ ጋር ግንኙነት አላችሁ በሚል እንዲሁም ማንነትን መሰረት ያደረገ በሚመስል ጥቃት በአሰቃቂ ሁኔታ ተደብድበው መገደላቸውን (ከዚህም ውስጥ አባት እና ልጅ እንደሚገኙበት)፣ በጋምቤላ ከተማ የተደራጁ ቡድኖች በከተማው ባሉ አንዳንድ አካባቢዎች የዘረፋ ድርጊት እንደፈጸሙ እና መንግስት በታጣቂ ቡድኑ የተፈጸመውን ጥቃት መቆጣጠሩን የገለጸ ቢሆንም ሰኔ 9 ቀን 2014 ዓ.ም ለሊት በከተማው የተኩስ ድምጽ ይሰማ እንደነበር እንዲሁም አሁንም አንዳንድ ስጋቶች መኖራቸውን ኢሰመጉ ከአካባቢው ካሰባሰበቸው መረጃዎች ለመረዳት ችሏል፡፡ በተጨማሪም ሰኔ 11 ቀን 2014 ዓ.ም በተሰራጨ ምስል በርካታ ቁጥር ያላቸው የታጠቁ እና የጸጥታ አካል ዩኒፎርም የለበሱ ሰዎች በመኪና ላይ ተጭነው የነበሩ ሰዎችን ሲደበድቡ እና እያስወረዱ ሲረሽኑ ታይቷል። ይህ ድርጊት መቼ፣ በማን፣ ለምን፣ የት እና በማን ላይ እንደተፈጸመ ለማወቅ ባይቻልም ድርጊቱ ግን ከህግ አግባብ ውጪ የሆነ ግድያ (extra judicial killing) በመሆኑ ኢሰመጉ ይህንን ኢ–ሰብዓዊ የሆነ እየተደጋገመ የመጣ ድርጊት እጥብቆ ያወግዛል።
በአዲስ አበባ እና በድሬዳዋ ከተማ የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶች፡
በአዲስ አበባ ከተማ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በፖሊስ አባላት በቁጥጥር ስር በዋሉ ሰዎች ላይ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ሲፈጸሙ ይስተዋላል ይህንንም አስመልክቶ አሰመጉ በተደጋጋሚ ሪፖርቶችን በማውጣት የእርምት እርምጃ እንዲወሰዱ ሲወተውት ቆይቷል፡፡ ይህ ድርጊት የዜጎችን መብት ለማስከበር ከተቋቋመ አካል እና በመንግስት የጸጥታ ሀይል መፈጸሙ ጉዳዩን ይባስ አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡ ሰኔ 8 ቀን 2014 ዓ.ም በጉለሌ ክ/ከተማ ወረዳ 7 አንድ ዩኒፎርም የለበሰ ተማ ላይ በፖሊስ አባላት ድብደባ እንደደረሰበት እንዲሁም ፖሊስ ድርጊቱን የፈጸሙ የፖሊስ አባላትን ይዞ ምርመራ በማድረግ ላይ መሆኑን የሚያሳይ መረጃ ኢሰመጉ ደርሶታል፡፡ በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በሰኔ 8 ቀን 2014 ዓ.ም በድሬዳዋ ከተማ መጋላ አካባቢ አይጉጉ ተብሎ በሚጠራ ሆቴል በአንድ ግለሰብ በተወረወረ ፈንጂ ምክንያት የሰው ህይወት መጥፋቱን እና በርካታ ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት መድረሱን፣ ጥቃት አድራሹ ግለሰብም በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተከናወነ መሆኑን ኢሰመጉ ከአካባቢው ካሰባሰባቸው መረጃዎ ለመረዳት ችሏል፡፡
ተያያዥ የህግ ግዴታዎች፡
ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች መግለጫ (UDHR) አንቀጽ 3፣ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃል–ኪዳንም (ICCPR) በአንቀጽ 6(1) እና 9(1) ላይ እያንዳንዱ ሰው በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደህንነቱ የመጠበቅ መብት እንዳለው ያረጋግጣል። ይህንኑ መብት በማረጋገጥ፣ መንግሥታት በቃል–ኪዳኑ (ICCPR) የተረጋገጡትን መብቶች በግዛታቸው የማክበር፣ የማስከበርና የማሟላት ግዴታ እንዳለባቸውም በአንቀጽ 2(1) እና 2(2) ይደነግጋል። የአፍሪካ ቻርተር በሰዎች እና ህዝቦች መብቶች (ACHPR) አንቀጽ 4 ማንኛውም ግለሰብ በሕይወት የመኖር መብቱና የአካሉ ደህንነት መብቱ ሊከበርለትና ሊጠበቅለት እንደሚገባና እነዚህን መብቶቹን በዘፈቀደ ሊነፈግ እንደማይችል ተመላክቷል። የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ–መንግሥት አንቀጽ 14 “ማንኛውም ሰው ሰብዓዊ በመሆኑ የማይደፈርና የማይገሰስ በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደህንነትና የነጻነት መብት አለው” ሲል ይደነግጋል። በተመሳሳይ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ–መንግስት አንቀፅ 15 ማንኛውም ሰው በሕይወት የመኖር መብት እንዳለውና በሕግ ከተደነገገው ውጪ ሕይወቱን ሊያጣ እንደማይችል በግልፅ ደንግጓል፡፡ በተመሳሳይ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ–መንግስት በአንቀጽ 16 ላይ ማ ንም ሰው በአካሉ ላይ ጉዳት እንዳይደርስበት የመጠበቅ መብት አለው ሲል ያስቀምጣል፡፡ በተጨማሪም የኢፈ ዲሪ ህገ–መንግስት አንቀጽ 18 ማንኛውም ሰው ጭካኔ ከተሞላበት፣ ኢ–ሰብዓዊም ሆነ ወይም ክብርን ከሚያዋርድ አያያዝ ወይም ቅጣት
የመጠበቅ መብት አለው ሲል ይደነግጋል፡፡ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽንን ለማቋቋም የወጣው አዋጅ ቁጥር 720/2011 በአንቀጽ 24 ላይ ኢ–ሰብዓዊ ወይም ክብርን የሚነካ አየያያዝ ወይም ድርጊት መፈጸም የተከለከለ ነው ሲል ይደነግጋል፡፡ ይኸው አንቀጽ በአዲስ አበባ ፖሊስ ላይ ተፈጸሚ እንደሚሆን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ማቋቋሚያ የሚኒስተሮች ምክር ቤት ደንብ ደንብ ቁጥር 96/2003 ደነግጋል፡፡
የኢሰመጉ ጥሪ፡
• በጋምቤላ ክልል በጋምቤላ ከተማ የጸጥታ አካላት ዩኒፎርምን በለበሱ ሰዎች የተፈጸመው ድርጊት ከህግ አግባብ ውጪ የተፈጸመ ግድያ (extra judicial killing) በመሆኑ ይህንን አሰቃቂ ድርጊት የፈጸሙ ሰዎችን መንግስት በአፋጣኝ በጥንቃቄ በማጣራት ለህግ በማቅረብ በወንጀል ተጠያቂ እንዲያደርግ፣
• በጋምቤላ ክልል በጋምቤላ ከተማ በተደራጁ ቡኖች በንጹሀን ሰዎች ላይ በተፈጸመው ጥቃት ውስጥ እጃቸው ያለበትን ሰዎች መንግስት በአስቸኳይ ለህግ እንዲያቀርብ፣
• በጋምቤላ ክልል ያለውን የጸጥታ ሁኔታ መንግስት በአፋጣኝ እንዲያረጋጋ እና አስተማማኝ እና ዘላቂ ሰላምን የማስፈን እንዲሁም የሰዎችን ደህንነት የማሰከበር ሃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ፣
• ሰኔ 11 ቀን 2014 ዓ.ም የተሰራጨውን ምስል ምንነት መንግስት በአፋጣኝ በጥንቃቄ በማጣራት በዚህ የጭካኔ ድርጊት ውስጥ የተሳተፉ አካላትን በአስቸኳይ ለህግ እንዲያቀርብ፣
• በአዲስ አበባ ከተማ ዩኒፎርም በለበሰ ተማሪ ላይ ድብደባ የፈጸሙ የፖሊስ አካላትን መንግስት በአፋጣኝ ለህግ በማቅረብ መሰል ድርጊቶች እንዳይደገሙ አስተማሪ የሆነ ህጋዊ እርምጃ እንዲወስድ፣
• በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር መጋላ አካባቢ የደረሰውን የቦንብ ጥቃት አስመልክቶ መንግስት ፈጣንና አስተማሪ ፍትህ እንዲሰጥ እንዲሁም መሰል ድርጊቶች እንዳይፈጠሩ ተገቢው ቁጥጥር እንዲያደረግ ኢሰመጉ ጥሪውን እያቀረበ ከላይ በተዘረዘሩት ጉዳዮች ላይ ሰፋ ያለ የምርመራ ስራን በማከናወን ዝርዝር መግለጫን እንደሚያወጣ ከወዲሁ ያሳውቃል፡፡