የትግራይ ኃይሎች ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ከ18 ወራት በላይ ሲያደርጉት የነበረውን ጦርነት ለማብቃት በኬንያ መንግሥት አሸማጋይነት በሚካሄድ ድርድር ላይ ለመሳተፍ ዝግጁ መሆናቸውን አስታወቁ። በህወሓት ሊቀመንበር እና በክልሉ ፕሬዝዳንት ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል ተፈርሞ የተሰራጨው ደብዳቤ የወጣው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ዐሕመድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው መንግሥታቸው ጦርነቱን በሰላም ለማብቃት ፍላጎት እንዳለው ካሳወቁ በኋላ ነው። ከህወሓት በኩል የወጣው ደብዳቤ ከዚህ በፊት ቡድኑ ለድርድር ያቀረባቸውን ቅድመ ሁኔታዎች አላካተተም።

የኬንያውን ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ላደረጉት ጥረት አድናቆቱን የገለፀው ህወሓት፣ በድርድሩ ላይ ለመሳተፍ የሚችል ከፍተኛ የመልዕክተኞች ቡድን ወደ ኬንያዋ መዲና ናይሮቢ ለመላክ ዝግጁ መሆኑን አመልክቷል። ደብዳቤው የአፍሪካ ሕብረት የሚጠበቅበትን ያህል አለማከናወኑን በመግለጽ አጥብቆ የተቸ ሲሆን፣ ባለፉት ወራት ሰላም ለማውረድ ከመቀለ አዲስ አበባ ሲመላለሱ በነበሩት የአፍሪካ ሕብረት ልዩ መልዕክተኛ ላይም ጥያቄ አንስቷል። ለድርድር ዝግጁ መሆናቸውንም በተመለከተ “ለሰላም ተጨማሪ ርቀት ለመሄድ ዝግጁ መሆናችን ከደካማነት ወይም ከስግብግብነት በመነጨ የቆምንለትን መርህ ለመተው እንደ መዘጋጀት ተደርጎ መታየት የለበትም” ብሏል።

በዚህ ድርድርም በኬንያ መንግሥት መሪነት የአፍሪካ ሕብረት፣ የተባበሩት መንግሥታት፣ አሜሪካ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ተሳታፊ እንዲሆኑም ጠይቋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ማክሰኞ ሰኔ 07/2014 ዓ. ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው እንደተናገሩት፣ መንግሥታቸው ከየትኛውም ወገን ጋር ሰላም ማውረድ እንደሚፈልግ ለዚህም ኮሚቴ ተዋቅሮ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል። ኮሚቴው በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የሚመራ እንደሆነና በገዢው ብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ መሰየሙን አመልክተው፤ ሰላሙን በተመለከተ መሳካት ያለባቸው ተግባራትን፣ እንዲሁም ስለሚጠበቁ ነገሮች እያጠና መሆኑን አመልክተዋል።

“ከህወሓትም ይሁን ከማንኛውም ሰላም ፈላጊ ጋር የምንፈልገው ሰላም ነው፤ የሚቻል ከሆነ ለሰላም መቆም ችግር የለውም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ጦርነት እንደማያተርፍና ከሁለቱም ጎን የሚያለማ ወጣት እየረገፈና አገሪቱም የምታወጣው ገንዘብ ከፍተኛ እንደሆነ ተናግረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከህወሓት ጋር በሚደረገው ድርድር ይኸው ኮሚቴ ተደራዳሪ መሆኑን እና ኮሚቴው በቅርቡ የደረሰበትን ለፓርቲው ሲያቀርብ በይፋ ለሕዝብ በዝርዝር የሚቀርብ ይሆናል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆኑ የህወሓት ፕሬዝዳንት ደብረጽዮን (ዶ/ር) በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ድርድር እየተካሄደ መሆኑን በሚመለከት የወጡ ዘገባዎችን አስተባብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ማከሰኞ ዕለት ለሕዝብ ተወካዮች በሰጡት ማብራርያቸው ላይ “ሰላም እንፈልጋለን ማለታችን የድብቅ ድርድር እናደርጋለን ማለት አይደለም” ሲሉ ድርድር ሲኖር ምክር ቤቱም ሆነ ሕዝቡ እንዲያውቅ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

አወዛጋቢ ጉዳይ

ከአንድ ዓመት ተኩል በላይ ሲካሄድ በነበረው ጦርነት ከባድ ሰብዓዊ ቀውስ በሰሜን ኢትዮጵያ በሚገኙ ክልሎች ውስጥ ያስከተለ ሲሆን፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ለከባድ የምግብ እጥረት መጋለጣቸውን የረድኤት ድርጅቶች ሲገልጹ ቆይተዋል። ባለፉት ወራት ጦርነቱ ጋብ ያለ ቢሆንም ሰላም ባለመውረዱ ተመልሶ ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ስጋት አለ። አሁን ሁለቱም ወገኖች ለድርድር ዝግጁ መሆናቸውን መግለጻቸው ቀጣይ ጦርነት እንዳይኖር ያደርጋል የሚል ተስፋን ፈጥሯል። ነገር ግን በመንግሥትና በህወሓት በኩል በሚደረገው ድርድር ላይ ከስምምነት ለመድረስ እንቅፋት ከሚሆኑት ጉዳዮች መካከል በትግራይ በኩል ምዕራብ ትግራይ፣ በአማራ በኩል ደግሞ ወልቃይት ጠገዴ በተባለው አካባቢ ላይ ያለው የይገባኛል ጥያቄ እንደሚሆን ተሰግቷል።

ባለፈው ሳምንት አንድ የፈረንሳይ ጋዜጣ ያወጣው ዘገባ ላይ በትግራይ መሪዎችና በፌደራል መንግሥቱ መካከል ድርድር ሊጀመር መሆኑንና ህወሓትም የወልቃይት ጉዳይን የመተው አዝማሚያ አሳይቷል ማለቱን ተከትሎ በሁለቱም ወገኖች በኩል ጠንከር ያለ ምላሽ ተሰጥቷል። በህወሓት በኩል ዘገባው ሐሰት መሆኑንና የምዕራን ትግራይ ጉዳይ በምንም መልኩ ሊተወዉ የማይችለው ጉዳይ በመሆኑ፣ በሰላምም ሆነ በሌላ አማራጭ ከትግራይ ክልል ጋር የመካተቱ ሁኔታ አይቀሬ እንደሆነ ባወጣው መግለጫ ላይ አመልክቷል። በአሁኑ ወቅት አካባቢው በቁጥጥሩ ስር የሚገኘው የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት የሆኑት ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) ጎንደር ውስጥ በተደረገ አንድ ሕዝባዊ ስብሰባ ላይ የወልቃይት አካባቢን በተመለከተ በተናገሩበት ጊዜ፣ ጉዳዩ አስተዳደራቸው ለድርድር የማያቀርበው “ቀይ መስመር ነው” በማለት ተናግረው ነበር።

ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) ማከሰኞ ዕለት ለክልሉ መገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ ደግሞ የትግራይ ኃይሎች ጉዳይ፣ ሪፍረንደም፣ የትግራይ ክልል ሉዓላዊ ግዛት ጥያቄ፣ የኤርትራ ሠራዊት ከትግራይ ለቅቆ መውጣት እና በጦርነቱ ወቅት ወንጀል የፈፀሙትን ተጠያቂ ማድረግ ጉዳይ ለድርድር የማይቀርቡ ብለው ከዘረዘሯቸው መካከል ናቸው። ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ማብቂያ ላይ በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት ኃይሎች መካከል ጦርነት ከተቀሰቀሰ ከወራት በኋላ የአፍሪካ ሕብረት እና አሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ሰይመው ሰላም ለማውረድ ቢጥሩም ውጤት ሳያገኙ ቆይተዋል።

የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታም በተለያዩ ጊዜያት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር አዲስ አበባ እና ናይሮቢ ላይ ተገናኝተው ጦርነቱን ለማስቆም የበኩላቸውን ሲጥሩ መቆየታቸው ይታወሳል። በመጪው ነሐሴ ወር በሚደረገው ምርጫ የሥልጣን ዘመናቸውን የሚያጠናቅቁት ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ አሁን በሁለቱም ወገን ተቀባይነት ያላቸው አሸማጋይ የሆኑ ይመስላል።