በጋምቤላ ከተማ ታጣቂ ቡድኖች የፈጸሙትን ጥቃት ተከትሎ ከ40 በላይ ሰዎች መገደላቸውን በክልሉ የተለያዩ ኃላፊነቶች ላይ የሚገኙ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ለቢቢሲ ተናገሩ። የክልሉ መስተዳደር የኦነግ-ሸኔ እና የጋምቤላ ነጻነት ግንባር ታጣቂዎች ናቸው ያላቸው ኃይሎች ማክሰኞ ሰኔ 07/2014 ዓ.ም. ማለዳ ላይ በዋና ከተማዋ ውስጥ ጥቃት ከፍተው ለሰዓታት የቆየ የተኩስ ልውውጥ ከፀጥታ ኃይሎች ጋር መካሄዱን ነዋሪዎች ገልጸዋል። ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱ አንድ የክልሉ ከፍተኛ ባለሥልጣን ለቢቢሲ እንዳረጋገጡት ጥቃቱን ተከትሎ ከ40 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ገልጸው፤ ከዚህ ውስጥ 10ሩ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ሲሆኑ ቀሪዎቹ የታጣቂው ኃይሉ አባላት ናቸው ብለዋል።

ሌላ ባለሥልጣን በተመሳሳይ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከአርባ እንደሚልቅ ገልጸው ከመካከላቸውም ሁለት ሰላማዊ ሰዎች እንዲሁም 11 የፀጥታ ኃይል አባላት መሞታቸውንና ቀሪዎቹ ጥቃቱን የፈጸሙት ታጠቂዎች ናቸው ብለዋል። ጨምረውም የፀጥታ ኃይሉ በጫካ ውስጥና በተለያዩ ስፍራዎች አሰሳ እያካሄደ በመሆኑ፣ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ሊጨምር ስለሚችል ትክክለኛውን አሃዝ አሁን ማወቅ አስቸጋሪ ነው ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል። በጥቃቱ ሕይወታቸው ከጠፋው ሰዎች በተጨማሪ 36 ሰዎች ደግሞ የመቁሰል ጉዳት ደርሶባቸው ህክምና እያገኙ መሆናቸውን ባለሥልጣኑ አመልከተዋል።

ትናንት በከተማዋ ላይ የተከፈተው ጥቃት በተለይ በክልሉ ምክር ቤት እና በክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ጽህፈት ቤት አካባቢ ላይ አትኩሮ የነበረ በመሆኑ፣ ቁልፍ የክልሉን ተቋማት ለመቆጣጠር ያለመ ይመስል እንደነበር ቢቢሲ ያነጋገራቸው የክልሉ ባለሥልጣንና ነዋሪ ተናግረው ነበር። ታጣቂዎቹ የጋምቤላ ከተማን ከፊል ተቆጣጥረው እንደነበረና እስከ እኩለ ቀን ድረስ በዘለቀው የተኩስ ልውውጥ በርካታ የታጣቂው ቡድን አባላት መገደላቸው ተነግሯል።

ካርታ

የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ማክሰኞ አመሻሽ ላይ በሰጡት መግለጫ ላይም የፀጥታ ኃይሉ በወሰደው እርምጃ በታጣቂዎቹ ላይ “ከፍተኛ ሰብአዊና ቁሳዊ ኪሳራ መድረሱን፣ በወገን ጦር ላይም መጠነኛ ጉዳት መድረሱን” ተናግረዋል። የከተማው ነዋሪዎች ለቢቢሲ እንደተናገሩትና በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የተሰራጩ ምስሎች እንዳሳዩት በርካታ የታጠቂው ቡድን አባላት ናቸው የተባሉ አስከሬኖች በጋምቤላ ከተማ መንገዶች ላይ ታይተዋል።   ዛሬ ረቡዕ ረፋድ ላይ ቢቢሲ ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪ እንደሚሉትም፣ ከተማዋ ሰላም መሆኗንና ከጠዋት ጀምሮ በመንገዶች ላይ ወድቀው የነበሩ አሰከሬኖች እየተሰበሰቡ ናቸው።

ነገር ግን ከጥቃቱ ጋር ተያይዞ ማክሰኞ ዕለት ተዘግተው የዋሉት የመንግሥት ተቋማት እና የግል የሥራ እንቅስቃሴዎች መልሰው እንዳልተጀመሩ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል። ከማክሰኞ ዕኩለ ቀን በኋላ በከተማዋ ውስጥ የተኩስ ድምጾች መቆሙን፣ ነገር ግን ከከተማው ወጣ ባሉ አካባቢዎች አሁንም የተኩስ ድምጽ አልፎ አልፎ እንደሚሰማ ተናግረዋል። ማለዳ ላይ በድንገት ጥቃት ከፍተው የነበሩት ታጣቂዎቹ በርከት ያለውን የጋምቤላ ከተማን ክፍሎች ለመቆጣጠር ችለው የነበረ ሲሆን፣ የክልሉ የፀጥታ ኃይል በወሰደው እርምጃ ረፋድ ላይ ታጣቂዎቹን ከአብዛኛው የከተማዋ ክፍሎች ለማስወጣት መቻሉን ነዋሪዎች ለቢበሲ ተናግረው ነበር።

የክልሉ መንግሥት ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ማክሰኞ አመሻሽ ላይ በሰጡት መግለጫ “የክልሉ የፀጥታ ኃይሎች ባካሄዱት ቅንጅታዊ ማጥቃት ከተማዋን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር እንደቻሉ” ገልጸዋል። መንግሥት በሽብርተኛ ቡድንነት የፈረጀው እና ሸኔ በሚል የሚጠራው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት፣ ዓለም አቀፍ የሕዝብ ግንኙነት እንደሆነ የሚነገረው ኦዳ ተርቢ፣ በትዊተር ገጹ ላይ የቡድኑ ታጣቂዎች ከጋምቤላ ነጻነት ግንባር ጋር ተቀናጅተው ጥቃት መፈጸማቸውን አረጋግጧል።

ማክሰኞ ዕለት በጋምቤላ ከተማ ውስጥ የተከሰተውን ጥቃት በተመለከተ የፌደራል መንግሥት አስካሁን በይፋ ያለው ነገር የለም። ከደቡብ ሱዳን ጋር በሚዋሰነው የምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የሆነው የጋምቤላ ክልል ታጣቂዎች ከሚንቀሳቀሱባቸው የምዕራብ ኦሮሚያ እና የከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ጋር ይዋሰናል።

ምንጭ – ቢቢሲ

 

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *