በተያዙ ሰዎች ላይ የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶች፡
የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ ስንታየሁ ቸኮል ለፓርቲው የስራ ጉዳይ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ባህርዳር ከተማ በነበሩበት በ19/09/2014 ዓ.ም ከቀኑ 9፡00 ሰዓት አካባቢ ካረፉበት ቦታ ፊታቸውን በሸፈኑና የደህነት ሰዎች ነን ባሏቸው ግለሰቦች ያለምንም የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ለጥያቄ ትፈለጋለህ በሚል እንደያዟቸው እና በዚህም መሀል በነበረ አለመግባባት የእጅ ስልካቸው እንደተሰበረ፣ ተጨማሪ የፖሊስ ሀይል ከአንደኛ ፖሊስ ጣቢያ በመምጣት ወደ ፖሊስ ጣቢያው እንደወሰዷቸው እና አቶ ስንታየሁ ከተያዙበት ከ19/09/2014 ዓ.ም ጀምሮ ይህ ሪፖርት እስከተዘጋጀበት ጊዜ ድረስ ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውን፣ የተያዙበት ምክንያትና እነማን እንደያዟቸው ግልጽ አንዳልተደረገላቸው እና አሁን ላይ ያሉበት ባህርዳር አንደኛ ፖሊስ ጣቢያ ለተጠርጣሪዎች ምቹ ባለመሆኑ ጤናቸው ላይ ጉዳት ሊደርስ እንደሚችል ስጋት እንዳላቸው፣ የተከናወነው ኢ-ሰብዓዊ አያያዝ እንደሆነ እና ያሉበትን ሁኔታ በመቃወም ከ30/09/2014 ዓ.ም ጀምሮ የርሀብ አድማ መጀመራቸውን ኢሰመጉ በቦታው በመገኘት እና ግለሰቡን በማነጋገር ካገኘው መረጃ ለመረዳት ችሏል፡፡
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የህግ ማስከበር በሚል ተይዘው ከነበሩ ተጠርጣሪዎች ውስጥ የተወሰኑት ምስራቅ ጎጃም ደጀን ወረዳ የትኖራ ቀበሌ እና ደቡብ ጎንደር ዞን ነፋስ መዉጫ /ጋይንት/ ከተማ ላይ ለይቶ ማቆያ ተብሎ በሚጠራ ቦታ በእስር ላይ ያሉ ሲሆን እነዚህ ተጠርጣሪዎች ቤተሰብን ጨምሮ ከማንም ጋር መገናኘት እንደማይችሉ ኢሰመጉ ካሰባሰባቸው መረጃዎች ለመረዳት ችሏል፡፡ በተጨማሪም በባህር ዳር ከተማ ዘጠነኛ ፖሊስ ጣቢያ ጋዜጠኛ አቶ ያለለት ወንድዬ ከ22/09/2014 ዓ.ም ጀምሮ አንዲሁም የዘመራ መልቲ ሚዲያ ጋዜጠኛ የሆነው አቶ ደምስ አያሌዉ ከ26/09/2014 ዓ.ም ጀምሮ ትፈለጋላችሁ በሚል ከተያዙ በኋላ እስከ አሁን ድረስ ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውንና የተያዙበት ምክንያት እንዳልተነገራቸው ኢሰመጉ ለመረዳት ችሏል፡፡
በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ለገጣፎ (ኬላ አካባቢ) ነዋሪ የሆኑት አቶ ደመቀ አያሌው ባልከው በ20/09/2014 ዓ.ም መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ከሚገኘውና ከሚሰሩበት ሱቃቸው አንድ የፖሊስ አባል ለጥያቄ ትፈለጋለህ በሚል ያለምንም የፍርድ ቤት ማዘዣ ወደ ለገጣፎ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ወስደው እንዳሰሯቸው፣ የተያዙበት ምክንያትም እንዳልተነገራቸው፣ ያሉበት ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ በጠባብ ቦታ በርካታ ታሳሪዎች ታስረው እንደሚገኙ፣ ፖሊስ ጣቢያው ምንም አይነት ምግብ እና መጠጥ ለታሳሪዎች እያቀረበ ባለመሆኑ ቤተሰቦቻቸው እየተመላለሱ እያቀረቡላቸው መሆኑን እና ይህ ሪፖርት እስከተዘጋጀበት ጊዜ ድረስ ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውን ኢሰመጉ ከቤተሰቦቻቸው ለመረዳት ችሏል፡፡
በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ደራሼ ልዩ ወረዳ ከፍተኛ የሆነ ከህግ አግባብ ውጪ የሆነ እስራት እየተፈጸመ መሆኑን፣ በእዚህ አካባቢ የሚያዙ ሰዎችን በአብዛኛው ወደ አርባ ምንጭ በሚገኙ ሲቀላ ፖሊስ አዳራሽ፣ ሴቻ ፖሊስ መምሪያ፣ የትነበርሽ እና ቆላ ሻራ በመውሰድ ከፍተኛ የሆነ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች እንደሚፈጸሙ እንዲሁም ማንም ሰው የታሰሩትን ሰዎች መጠየቅ እንደማይፈቀድለት ኢሰመጉ ካሰባሰባቸው መረጃዎች ለመረዳት ቸሏል። በመጨረሻም ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፣ ጋዜጠኛ መዓዛ መሀመድ እና ጋዜጠኛ ሰለሞን ሹምዬን የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት በዋስ ከእስር እንዲፈቱ ወስኖ ፖሊስ ይዞ ማቆየቱ የህግ አግባብን ያልተከተለ በመሆኑ ኢሰመጉ ይህንን ድርጊት እያወገዘ መሰል ድርጊቶች ወደፊት እንዳይፈጸሙ ፖሊስ ሃላፊነቱን በህግ አግባብ እንዲወጣ ይጠይቃል፡፡
ተያያዥ የህግ ግዴታዎች፡
የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃል-ኪዳንም (ICCPR) በአንቅጽ 10(1) ላይ ሁሉም ነጻነታቸውን የተነፈጉ ሰዎች በሰብአዊነትና የሰውን ተፈጥሮአዊ ክብር በጠበቀ መልኩ ይያዛሉ ሲል ይደነግጋል። ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች መግለጫ (UDHR) አንቀጽ 5፣ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃል- ኪዳንም (ICCPR) አንቀጽ 7 ማንም ሰው ጭካኔ ወይም ስቃይ አይደርስበትም ወይም ከሰብአዊነት ውጪ የሆነ የሚያዋርድ ተግባር ወይም ቅጣት አይፈጸምበትም ሲሉ ይደነግጋሉ። የአፍሪካ ቻርተር በሰዎች እና ህዝቦች መብቶች (ACHPR) አንቀጽ 5 ባርነት፣ የባሪያ ንግድ፣ ማሰቃየት፣ ጭካኔ የተሞላበት፣ ኢሰብዓዊ የሆነ ወይም ክብርን የሚያዋርድ አያያዝ ወይም ቅጣት የተከለከለ መሆኑን ይደነግጋል። በተመሳሳይ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 18 ማንኛውም ሰው ጭካኔ ከተሞላበት፣ ኢሰብዓዊ ከሆነ ወይም ክብርን ከሚያዋርድ አያያዝ ወይም ቅጣት የመጠበቅ መብት አለው ሲል ይደነግጋል።
የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃል-ኪዳንም (ICCPR) በአንቀጽ 9 ላይ ማንኛውም ሰው በሚያዝበት ጊዜ የተያዘባቸውን ምክንያቶችና የቀረቡበትን ክሶች ምንነት ወዲያውኑ የማወቅ መብት አለው ሲል ይደነግጋል፡፡ በተጨማሪም የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ-መንግስት አንቀጽ 19 ንዑስ አንቀጽ 1 እና 3 ወንጀል ፈጽመዋል በመባል የተያዙ ሰዎች የቀረበባቸው ክስና ምክንያቶቹ በዝርዝር ወዲያውኑ በሚገባቸው ቋንቋ እንዲነገራቸው መብት እንዳላቸው እና የተያዙ ሰዎች በአርባ ስምንት ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት የመ ቅረብ መብት አላቸው ሲል ይደነግጋል፡፡ ይኸው ህገ-መንግስት በአንቀጽ 21 ላይ በጥበቃ ስር ያሉ ሰዎች ከትዳር ጓደኞቻቸው፣ ከቅርብ ዘመዶቻቸው፣ ከሐኪሞቸው እና ከሕግ አማካሪዎቻቸው ጋር ለመገናኘትና እንዲጎበኟቸው ዕድል የማግኘት መብት አላቸው ሲል ይደነግጋል፡፡
የኢሰመጉ ጥሪ፡
- መንግስት የባልደራስ ለእዉነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ከፍተኛ አመራር የሆኑትን አቶ ስንታየሁ ቸኮልን በአስቸኳይ የቀረበባቸውን ክስና የተያዙበትን ምክንያት በማሳወቅ እና ፍርድ ቤት በማቅረብ ፈጣን ፍትህ የማግኘት መብታቸውን እንዲያስከበር፣እንዲሁም በፖሊሰ ጣቢያ ውስጥ ያሉበትን ሁኔታ እና አያያዛቸውን ሰብዓዊ ክብርን በሚመጥንና ጤናቸውን አደጋ ላይ በማይጥል መልኩ እንዲያሻሽል፣
- ጋዜጠኛ ያለለት ወንድዬን እና ጋዜጠኛ ደምስ አያሌዉን በአስቸኳይ የቀረበባቸውን ክስና የተያዙበትን ምክንያት በማሳወቅ እና ፍርድ ቤት በማቅረብ ፈጣን ፍትህ የማግኘት መብታቸውን እንዲያስከበር፣
- በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ለገጣፎ ነዋሪ የሆኑት አቶ ደመቀ አያሌው ባልከውን ፖሊስ በአስቸኳይ ፍርድ ቤት በማቅረብ አፋጣኝ ፍትህ የማግኘት መብታቸውን ወይንም የአካል ነጻነታቸውን እንዲያከብር፣
- በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ደራሼ ልዩ ወረዳ እየተፈጸሙ ያሉ ህገ-ወጥ እስሮች በአስቸኳይ እንዲቆሙ እንዲሁም ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ደራሼ ልዩ ወረዳ ተይዘው በአርባ ምንጭ የተለያዩ እስር ቤቶች ውስጥ የሚገኙ እስረኞችን ፍርድ ቤት በማቅረብ ፈጣን ፍትህ የማግኘት መብታቸውን ወይንም የአካል ነጻነታቸውን እንዲያከብር፣
- በፍርድ ቤት ነጻ የተባሉ ሰዎችን እና የዋስ መብታቸው የተከበረላቸውን ሰዎች ፖሊስ ከህግ አግባብ ውጪ በእስር የማቆየት ድርጊትን በአስቸኳይ እንዲያቆም፣
- ምስራቅ ጎጃም ደጀን ወረዳ የትኖራ ቀበሌ እና ደቡብ ጎንደር ዞን ነፋስ መዉጫ /ጋይንት/ ከተማ ላይ ታስረው የሚገኙ ሰዎችን ከትዳር ጓደኞቻቸው፣ ከቅርብ ዘመዶቻቸው፣ ከሐኪሞቻቸው እና ከሕግ አማካሪዎቻቸው ጋር የመገናኘትና የመጎብኘት መብቶቻቸውን እንዲያከበር ኢሰመጉ ጥሪውን እያቀረበ የዚህ አይነት ክልከላዎች የተለያዩ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች እንዲፈጸሙ በር ከፋች በመሆናቸው ኢሰመጉ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ እያሳሰበ፤ ጥልቅ የምርመራ ስራዎችን በመስራት ከላይ የተዘረዘሩትን ጉዳዮች አስመልክቶ ሰፋ ያለ ዘገባን እንደሚያቀርብ ከወዲሁ ይገልጻል፡፡