አሜሪካ ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሦስተኛውን የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛዋን መሰየሟን የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊው ይፋ አደረጉ። አንቶኒ ብሊንከን እንዳሳወቁት ፖለቲካዊ አለመረጋጋት በሚንጠው የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ እንዲሆኑ የሾሟቸው አምባሳደር ማይክ ሐመርን ነው። ላለፉት አምስት ወራት ያህል በልዩ መልዕክተኝነት ቦታው ላይ የቆዩት አምባሳደር ዴቪድ ሳተርፊልድ ኃላፊነታቸውን ለማስረከብ እየተዘጋጁ መሆናቸው ተገልጿል። ብሊንከን የአዲሱ መልዕክተኛ ሐመር ሹመት፣ አሜሪካ ለአካባቢው ዲፕሎማሲያዊ አስተዋጽኦ ለማበርከት ያላትን ቁርጠኝነት ያመለክታል ብለዋል።
“በኢትዮጵያ ውስጥ ወደ ሰላም፣ የጋራ ደኅንነት እና ሁሉንም የአገሪቱን ዜጎች ወደ ብልጽግና የሚያደርስ ሁሉን አቀፍ ፖለቲካዊ ሁደትን መደገፍ” ትኩረት የሚሰጠው መሆኑን ብሊንከን አመልክተዋል። አዲሱ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር በዲሞክራቲክ ኮንጎ እና ቺሊ ውስጥ የአሜሪካ አምባሳደር ሆነው የሰሩ ሲሆን፣ በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት እና በዋይት ሐውስ ውስጥ በተለያዩ ኃላፊነቶች አገልግለዋል። አሜሪካ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ከጥቂት ወራት በኋላ መጀመሪያ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባል የሆኑትን ክሪስን በመላክ የጀመረችው ጥረት፣ ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሦስት ጉምቱ አምባሳደሮች ተቀባብለውታል። በዚህ ወቅት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ሆነው የተሰየሙት መልዕክተኞች እነማን ነበሩ? ምን ጥረት አደረጉ?
ሴናተር ክሪስ ኩንስ

በትግራይ ውስጥ ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ በኋላ ባሉት ጥቂት ወራት ውስጥ ዋነኛ አሳሳቢ ጉዳይ የነበረው የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት እና ጦርነቱ በአፍሪካ ቀንድ የሚያስከትለው ቀውስ ያሰጋቸው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በቀዳሚነት መልክተኛቸው አድርገው የላኩት ሴናተር ክሪስ ኩንስን ነበር። መጋቢት ወር 2013 ዓ.ም. ላይ የአሜሪካ መንግሥት መልዕክተኛ ሆነው የተላኩት የሕግ ሙያተኛውና ፖለቲከኛው የዴላዌር ግዛት ተወካዩ ክሪስቶፈር አንድሪው ኩንስ የረጅም ጊዜ የአሜሪካ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባል ሲሆኑ፣ ባይደን ለፕሬዝዳንትነት ሲወዳደሩ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊነትን ይይዛሉ ተብለው ከታሰቡት መካከል አንዱ ነበሩ።
ኩንስ ኃላፊነቱን ተቀብለው ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ፕሬዝዳንቱ የአፍሪካ ቀንድ የልዩ መልዕክተኝነቱን ቦታ በዋናነት ይዞ የሚሰራ ሰው እስኪሰይሙ ድረስ ነበር። ኩንስ በመጀመሪያ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ በትግራይ ክልል ስለተከሰተው ቀውስ፣ ስለተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችና በሱዳንና ኢትዯጵያ መካከከል ያለው የድንበር ውዝግብ በተመለከተ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር ከመወያየታቸው በተጨማሪ ከአፍሪካ ሕብረት ባለሥልጣንት ጋርም ተገናኝተው ነበር።
አምባሳደር ጄፍሪ ፌልትማን

ለአጭር ጊዜ የፕሬዝዳንት ባይደን የአፍሪካ ቀንድ መልዕክተኛ ሆነው የሰሩት ክሪስ ኩንስን በመተካት፣ አሜሪካ በኢትዮጵያና በአካባቢው ባሉ አገራት ውስጥ ያሉ ጉዳዮችን በቅርበት እንዲከታተሉ አምባሳደር ጄፍሪ ፌልትማንን ልዩ መልዕክተኛ አድርጋ የሾመችው ባለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር መጨረሻ ላይ ነበር። በወቅቱ ፌልትማን የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ሲሆኑ በተለይ በኢትዮጵያና በዙሪያዋ ስላሉ ሁኔታዎች የተለየ ትኩረት እንደሚሰጡ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት አመልክቶ ነበር። በዚህም መሠረት በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል ስላለው ጦርነት እንዲሁም በአገሪቱ ስላለው ተለዋዋጭ ሁኔታ፣ ከሱዳን ጋር ስላለው የድንበር አለመግባባት እንዲሁም በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ያለው ውዝግብ የልዩ ልዑኩ ቀዳሚ ሥራ ይሆናል ተብሎ ነበር።
በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ውስጥና በተባበሩት መንግሥታት ውስጥ በከፍተኛ የኃላፊነት ደረጃ የሰሩት ጄፍሪ ፌልትማን በአፍሪካና በመካከለኛው ምሥራቅ ጉዳዮች ላይ ለረጅም ዘመን ልምድ ያካበቱ ናቸው። በተጨማሪም ፌልትማን በርካታ አገራትን ባካተቱ የዲፕሎማሲ ጉዳዮች ላይ እንዲሁም በተለያዩ አካባቢያዊ ጉዳዮች ዙሪያ በሚደረጉ ድርድሮችና ሽምግልናዎች ውስጥ የአሜሪካንን ተያያዥ ስትራቴጂን በማስፈጸም ልምድ ባላቸው ልምድ በአፍሪካ ቀንድ ሰላም ለማምጣት ያግዛሉ ተብሎ ነበር። የአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ሆነው ለዘጠኝ ወራት የቆዩት ፌልትማን፣ በተለይ በሰሜን ኢትዮጵያ የሚካሄደው ጦርነት እልባት እንዲያገኝ ወደ አፍሪካ ቀንድ አገራት እና መካከለኛው ምሥራቅ ተደጋጋሚ ጉዞ አድርገው ነበር።
አምባሳደሩ ፌልትማን ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይን ጨምሮ ከፍተኛ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናትን በአዲስ አበባ፣ የህወሓት ተወካዮችን ደግሞ በኬንያ ናይሮቢ ውስጥ አግኝተው ማነጋገራቸውን ከስንብታቸው በፊት ዋሽንግተን ላይ ተናግረው ነበር። ይሁን እንጂ ፌልትማን እንደ ጥረታቸው በትግራይ ጦርነት ተሳታፊ የሆኑ አካላትን በጠረጴዛ ዙሪያ ለንግግር እንዲቀመጡ በማድረግ ጦርነቱን የሚያስቆም ውጤት ማስገኘት አልተቻላቸውም።
አምባሳደር ዴቪድ ሳተርፊልድ

አምባሳደር ጄፍሪ ፌልትማንን በመተካት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ በመሆን ኃላፊነቱን የተረከቡት፣ ሌላው ጉምቱ የአሜሪካ ዲፕሎማት አምባሳደር ዴቪድ ሳተርፊልድ ናቸው። በጥር ወር ላይ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ በመሆን የተሰየሙት በቱርክ የአሜሪካ አምባሳደር ሆነው ያገለገሉት ዴቪድ ሳተርፊልድ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ ዲፕሎማሲ ዙሪያ ለአራት አስርት ዓመታት የዘለቀ ልምድ እንዳካበቱ ይነገራል። ሳተርፊልድ በሥራቸው መጀመሪያ ላይ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ኃላፊ ከሆኑት ሞሊ ፊ ጋር በመሆን ወደ አዲስ አበባ፣ ካርቱም እና ሪያድ በመጓዝ ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል።
ከዚያም በኋላ ልዩ መልዕክተኛው አምባሳደር ዴቪድ ሳተርፊልድ ወደ ኢትዮጵያ ለሁለት ቀናት በመምጣት ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት፣ ከተባበሩት መንግሥት ኃላፊዎች እና ከሰብዓዊ እርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች ተወካዮች ጋር ውይይት አድርገው ነበር። ለአምስት ወራት ያህል የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ሆነው ያገለገሉት አምባሳደር ዴቪድ ሳተርፊልድ እንደ ቀዳሚዎቻቸው ሁሉ በተልዕኳቸው ይህ ነው የሚባል ውጤት ሳያስገኙ፣ ቦታቸውን ለአምባሳደር ማይክ ሐመር እንደሚያስረክቡ የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት አመልክቷል።
የአሜሪካ ጥረት
አሜሪካ ጦርነቱ በድርድር መቋጫ እንዲያገኝ ልዩ መልዕክተኛ በመሰየም ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋር ግንኙነት ስታደርግ ቆይታለች። ከጥቂት ወራት በፊት አምባሳደር ፌልትማንን በመተካት የአሜሪካ መንግሥት ልዩ መልዕክተኛ ሆነው የተሾሙት አምባሳደር ስተርፊልድ፣ ብዙም ሳይቆዩ በአምባሳደር ማይክ ሐመር እንደሚተኩ ይፋ ሆኗል። ከአምስት ወራት በኋላ ሁለት ዓመት የሚደፍነው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት መቀስቀስ ተከትሎ አሜሪካ በያዘችው አቋምና በወሰደቻቸው እርምጃዎች ምክንያት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የነበረው መልካም ግንኙነት ሻክሮ ቆይቷል። ከጦርነቱ መቀስቀስ ከጥቂት ወራት በኋላ የአሜሪካ መንግሥት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ሆነው የተሾሙት የአገሪቱ ጉምቱ ዲፕሎማቶች በአፍሪካ ቀንድ በተለይም በኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ጦርነት እንዲሁም በሱዳን ፖለቲካዊ ቀውስ ላይ መፍትሔ ለማስገኘት ያግዛሉ ተብሎ ቢጠበቁም ሳይሳካላቸው ቆይተዋል።
በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል የሚካሄደው ጦርነት አስከ ታኅሣሥ ወር ድረስ ተፋፍሞ ቀጥሎ አሁን ጋብ ያለ ቢመስልም አሁንም ሌላ ዙር ጦርነት ይነሳል የሚል ስጋት እንዳለ ነው። በሱዳን ውስጥም ቢሆን አገሪቱን ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ያደርሳታል የተባለው የሽግግር መንግሥት በወታደሮች መፈንቅለ መንግሥት ተደርጎበት በመፍረሱ ፖለቲካዊ ቀውሱ ተባብሶ ቀጥሏል። አዲሱ የአሜሪካ መንግሥት ልዩ መልዕክተኛ በእነዚህ በትልልቆቹ የአፍሪካ ቀንድ አገራት ውስጥ ያለው ጦርነትና ፖለቲካዊ ቀውስ መቋጫ እንዲያገኝ ማድረግ ዋነኛ ኃላፊነታቸው ይሆናል። አምባሳደር ማይክ ሐመር ምን ይዘው እንደሚመጡ ባይታወቅም፣ የአፍሪካ ቀንድ ጉዳይ የአሜሪካን ትኩረት ያገኘ መሆኑ እረሳቸውን ጨምሮ የቀደሙት መልዕክተኞች አሜሪካ ካሏት ዲፕሎማቶች መካከል አንቱ የተባሉትን ደጋግማ መሰየሟ ያመለክታል።