ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው ዘመቻው የሚካሄደው ሆን ተብሎ የአንድን ማኅበረሰብ ቅስም ለመስበር፣ የኃይል ሚዛንን ለማስጠበቅ፣ ለሥልጣን ሥጋት ሲባልና ሕዝቡን መሪ ለማሳጣት ነው ብለዋል፡፡ መንግሥት በሕግ ማስከበር ስም ተቃዋሚዎችን፣ ጋዜጠኞችን፣ ምሁራንና የማኅበረሰብ አንቂዎችን እያሳደደ ነው ሲል የሦስቱ ፓርቲዎች የጋራ መግለጫ ያመላክታል፡፡ የመኢአድ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አብረሃም ጌጡ፣ ‹‹እያልን ያለነው ወንጀል የሠራ ወይም ያጠፋ ሰው በሕግ አይጠየቅ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹አሁን ያለው ዘመቻ ግን ከዚያ ይልቅ ‹‹ሰበብ አስባብ እየፈለጉ ዜጎችን ማሰር፣ ማሳደድና ማፈን ነው፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

አቶ አብረሃም አክለውም መንግሥት ራሱ ጠርቶ አገር ታደግ ያለው ፋኖን፣ ‹‹ሕገወጥና ሕጋዊ ፋኖ እያለ ዛሬ መከፋፈሉና ማሰሩ ተቀባይነት የሌለው ነው፤›› ብለውታል፡፡ መግለጫውን ከሰጡት አንዱ የኢሕአፓ ሊቀመንበር ዝናቡ አበራ (ረዳት ፕሮፌሰር) በበኩላቸው፣ አገሪቱ የምትገኝበት የጭንቅ ወቅት ሁሉንም የሚያሳስብ በመሆኑ ፓርቲዎቹ ተሰባስበው በጋራ አቋማቸውን እንዲያንፀባርቁ እንዳደረጋቸው አስረድተዋል፡፡ የትግራይን ጉዳይ በተመለከተ ከጋዜጠኞች ለቀረበ ጥያቄ መልስ የሰጡት ዝናቡ (ረዳት ፕሮፌሰር)፣ ‹‹ለመሆኑ ሕወሓት ራሱ የኢትዮጵያን ጉዳይ እንዴት ነው የሚመለከተው?›› ሲሉ ጥያቄ አንስተዋል፡፡ ‹‹ሕወሓት የሚፈልገው ወደ አራት ኪሎ ዳግም መመለስ ከሆነ የተደረገውንና ትናንት የሆነውን እናውቀዋለን፡፡ አራት ኪሎ የሚገባው በምርጫ ነው ተባብለን ጨርሰናል፡፡ አሁን የሚደረገው የጦርነት ነጋሪት ጉሰማ ለምንድነው ታዲያ የተፈለገው?›› ብለዋል፡፡

አክለውም በሰሜን ኢትዮጵያ የተካሄደው ጦርነትና ያስከተለው ሰብዓዊ ዕልቂት ሁሉንም የሚያሳስብ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ይህ የሰብዓዊ ቀውስና ውድመት ሳይጠገን ደግሞ ሕወሓትም ሆነ ሌሎች ወገኖች የጦር ነጋሪት መጎሰማቸው በእጅጉ የሚያሳስብ ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በመኢአድ ፓርቲ ዋና ጽሕፈት ቤት ማክሰኞ ግንቦት 23 ቀን 2014 ዓ.ም. በተሰጠው መግለጫ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያዎችን ከሰጡት መካከል የእናት ፓርቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ሰይፈ ሥላሴ አያሌው (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ሕግ ማስከበርን በተመለከተ በአፅንኦት ተናግረዋል፡፡ ‹‹ሕግ ማስከበር የአንድ አገር መንግሥት ተቀዳሚ ኃላፊነት ነው፡፡ መንግሥት ሕግ ሲያስከብርም ሕግና ሕጋዊ አግባብን ተከትሎ ብቻ መሆን አለበት፤›› ሲሉም አስረድተዋል፡፡

ሰዎች ሕጋዊ መብቶቻቸው ሳይከበር እየታሰሩና እየታፈኑ መሆኑን የገለጹት ሰይፈ ሥላሴ (ዶ/ር)፣ ‹‹እከሌ ከእከሌ ወይም የኅብረተሰብ ክፍል ሳይለይ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የዚህ ሕገወጥ የሕግ ማስከበር ዘመቻ ሰለባ ሆኗል፤›› ብለዋል፡፡ ሦስቱ ፓርቲዎች በመግለጫቸው የኢትዮጵያ ውስብስብ ችግሮች እየመነጩ የሚገኘው በዘርና በጎሳ ከፋፋይ ከሆነው የፖለቲካ ሥርዓት መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ‹‹በአፈናና በግድያ ሕግ ማስከበር እንደማይቻል አጠንክረን እናሳስባለን፤›› የሚለው የፓርቲዎቹ የጋራ መግለጫ ሊደረጉ ይገባል ያላቸውን ጉዳዮች በስምንት ነጥቦች በማቅረብ ነው የተጠናቀቀው፡፡

ከነጥቦቹ መካከል በዋነኝነት መንግሥት በሃይማኖት፣ በወንዝና በቡድን ማኅበረሰቡን መከፋፈልና ማፈን እንዲያቆም፣ በአፈናና በግድያ ሕግ ማስከበር እንደማይቻል፣ በሕግ ማስከበር ሰበብ የታፈነ ፍርድ ቤት ከመቅረብ ጀምሮ ሰብዓዊ መብቶቻቸው እንዲከበሩ፣ ፋኖ በጭንቅ ጊዜ ለአገር የደረሰ ባለውለታ በመሆኑ መንግሥት ሥጋቱን እንዲያስወግድ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ህልውና ወደ ባሰና ውስብስብ ችግር ከማምራቱ በፊት መንግሥት ያልተገቡ አካሄዶችን እንዲያርምና ሌሎች ጉዳዮች ተጠቅሰዋል፡፡

ምንጭ – ሪፖርተር
selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *