ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተደጋጋሚ በጋዜጠኞች፣በተፎካካሪ ፓርቲ አባላትና አመራሮች እና በማህበረሰብ አንቂዎች ላይ ህገወጥ እስር እና አፈና እየተፈጸመ ይገኛል፡፡ኢሰመጉም ይህንን የሰብዓዊ መብት ጥሰት አስመልክቶ ሚያዚያ 29 ቀን 2014 ዓ.ም እና ግንቦት 15 ቀን 2014 ዓ.ም ባወጣቸው ጋዜጣዊ መግለጫዎች መንግስት የእርምት እርምጃዎችን እንዲወስድ ሲወተውት ቆይቷል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ሕገወጥ እርምጃ በመንግስት በኩል አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡ለዚህም ማሳያነት የፍትህ መጽሄት ማኔጂነግ ዳይሬክተር የሆነው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ግንቦት 18 ቀን 2014 ዓ.ም ረፋድ ላይ ከቢሮው በጸጥታ ሀይሎች ተወስዶ መታሰሩን እንዲሁምጋዜጠኛያየሰው ሽመልስ በተመሳሳይ ቀን በጸጥታ ሀይሎች ወደ ሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ተወስዶ መታሰሩን ኢሰመጉ ካሰባሰባቸው መረጃዎች ለመረዳት ችሏል፡፡በተጨማሪም 7 የሚሆኑ የአሻራ እና የንስር ዩቲዩብ ሚዲያ ጋዜጠኞች ባሳለፍነዉ ሳምንት ከስራ ቦታቸዉ በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች የተያዙ ሲሆን የት እንደሚገኙ ሳይታወቅ የቆየ ቢሆንምይህ መግለጫ እየተዘጋጀ ባለበት ወቅት ኢሰመጉ ባገኘው መረጃ መሰረት ደቡብ ጎንደር ጋይንት ታስረዉ እንደሚገኙ ነገር ግን ፍርድ ቤት እንዳልቀረቡ ለመረዳት ተችሏል፡፡
አማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት፡
በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ከግንቦት 2014 ዓ.ም ጀምሮ መንግስት ህግ ማስከበር ዘመቻ በሚል ከ 4500 በላይ ሰዎች መታሰራቸውን መግለጹ የሚታወስ ነው፡፡ይህንንም ተከትሎ ኢሰመጉ ባሰባሰባቸው መረጃዎች በአንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች እየተፈጸሙ ያሉ እስሮች ተገቢውን የህግ ስነስርአት ያልተከተሉ እና እገታም የታከለባቸው መሆናቸውን ለመረዳት ችሏል፡፡ በተጨማሪም በዚህ ሂደት በተፈጠሩ ግጭቶች እና በተወሰዱ እርምጃዎች በክልሉ በሚገኙ አካባቢዎች ማለትም በሰሜን ወሎ ዞን ወልዲያ ከተማ ፣በምስራቅ ጎጃም ዞን ሞጣ ከተማ እና በምዕራብ ጎጃም ዞን ሰሜን ሜጫ ወረዳ መራዊ ከተማ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ላይ ሞት (የ13 አመት ታዳጊን ጨምሮ)፣ የአካል ጉዳት፣ ንብረት ውድመት፣እስራት እና እገታ መፈጸሙን ኢሰመጉ ከአካባቢዎቹ ባሰባሰባቸው መረጃዎች ለመረዳት ችሏል፡፡
እንዲሁም ተገቢውን የህግ ሂደት ሳይከተል በርካታ የተፎካካሪ ፓርቲ አባላት እና አመራሮች እየታሰሩና እየታገቱ እንደሚገኙ ከነዚህም መካከል በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ፓርቲ ፣ የእናት ፓርቲ አባላት እና አመራሮች እንዲሁም የሌሎችም ፓርቲ አባላት እና አመራሮች እንደሚገኙበት ኢሰመጉ ከፓርቲዎቹ አቤቱታ ለመረዳት ችሏል፡፡ ከላይ በተጠቀሱት ፓርቲዎች አባላት እና አመራሮች ላይ እየተፈጸመ ያለው እስር በመንግስት አካላት የሚፈጸም የእገታ ድርጊት መሆኑን እና ይህንንም ተከትሎ አብዛኛው እየታገቱ ያሉ ሰዎች ያሉበት እንደማይታወቅ እና ፍርድ ቤትም እየቀረቡ አለመሆኑን ኢሰመጉ ካሰባሰባቸው መረጃዎች ለመረዳት ችሏል፡፡
ተያያዥ የህግ ግዴታዎች፡
ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች መግለጫ (UDHR) አንቀጽ 3፣ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃል–ኪዳንም (ICCPR) በአንቀጽ 6(1) እና 9(1) ላይ እያንዳንዱ ሰው በሕይወት የመኖር፣የአካል ደህንነቱ የመጠበቅ መብት እንዳለው ያረጋግጣል። ይህንኑ መብት በማረጋገጥ፣ መንግሥታት በቃል–ኪዳኑ (ICPR) የተረጋገጡትን መብቶች በግዛታቸው የማክበር፣ የማስከበርና የማሟላት ግዴታ እንዳለባቸውም በአንቀጽ 2(1) እና 2(2) ይደነግጋል። የአፍሪካ ቻርተር በሰዎች እና ህዝቦች መብቶች (ACHPR) አንቀጽ 4 ማንኛውም ግለሰብ በሕይወት የመኖር መብቱና የአካሉ ደህንነት ሊከበርለትና ሊጠበቅለት እንደሚገባና እነዚህን መብቶቹን በዘፈቀደ ሊነፈግ እንደማይችል ተመላክቷል።
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ–መንግሥት አንቀጽ 14 “ማንኛውም ሰው ሰብዓዊ በመሆኑ የማይደፈርና የማይገሰስ በሕይወት የመኖር፣የአካል ደህንነትና የነጻነት መብት አለው” ሲል ይደነግጋል። በተመሳሳይ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ–መንግስት አንቀፅ 15 ማንኛውም ሰው በሕይወት የመኖር መብት እንዳለውና በሕግ ከተደነገገው ውጪ ሕይወቱን ሊያጣ እንደማይችል በግልፅ ደንግጓል፡፡ የሰብዓዊ መብቶች ዓለም አቀፍ መግለጫ (UDHR) እና የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃል ኪዳን (ICCPR) ሁለቱም
ስምምነቶች በአንቀጽ 9 ላይ ማንም ሰው በዘፈቀደ ሊያዝ እንደማይችል፣ ማንም ሰው ከህግ ውጪ እንደማይያዝ፣ እንደማይታሰር እና የግል ነጻነቱን እንደማያጣ ይደነግጋሉ፡፡የአፍሪካ ቻርተር በሰዎች እና ህዝቦች መብቶች ስምምነት አንቀጽ 6 ላይ በተመሳሳይ ማንም ሰው የነጻነትና የአካል ደህንነት መብት እንዳለው ይህንንም መብት ከህግ አግባብ ውጪ እንደማያጣ እና ማንም ሰው በዘፈቀደ ሊታሰር እንደማይገባ ይደነግጋል፡፡
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ መንግስትም እንዲሁ በአንቀጽ 17 ላይ የነጻነት መብትን ሲያብራራ ማንኛውም ሰው በህግ ከተደነገገው ስርዓት ውጪ ሊያዝ፣ ክስ ሳይቀርብበት ወይም ሳይፈረድበት ሊታሰር አይችልም ሲል ይደነግጋል፡፡ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ መንግስት በአንቀጽ 28 ላይ በስብእና ላይ ስለሚፈጸሙ ወንጀሎች ሲያብራራ በአስገዳጅ ሰውን መሰወር በስብዕና ላይ የሚፈጸም ወንጀል መሆኑን እውቅና ይሰጣል፡፡ ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ባታጸድቀውም ሰዎችን አስገድዶ ከመሰወር ለመጠበቅ የወጣው ዓለም አቀፍ ስምምነት (International Convention for the Protection of All Persons from Enforced Disappearance ) በአንቀጽ 5 ላይ በስፋት ወይም ስልታዊ በሆነ መንገድ የሚፈጸም አስገድዶ መሰወር በዓለም አቀፍ ህጎች ትርጉም በተሰጠው መሰረት በስብዕና ላይ የሚፈጸም ወንጀል መሆኑን ይደነግጋል፡፡
በተጨማሪም ይኸው ስምምነት በአንቀጽ 1(1) ላይ ማንም ሰው ለአስገድዶ መሰወር ተጋላጭ መሆን እንደሌለበት በመደንገግ ይህንን ወንጀል የፈጸሙ አካላትን መንግስት በወንጀል ተጠያቂ እንዲያደርጋቸው ይደነግጋል፡፡ የመገናኛ ብዙሀን አዋጅ ቁጥር 1238/2021 በአንቀጽ 48 ላይ የመገናኛ ብዙሀንን እና የጋዜጠኞችን መብቶች ሲዘረዝር ዜና ወይም መረጃን የመሰብሰብ፣ የመቀበልና የማሰራጨት፤በልዩ ልዩ ጉዳዮች ላይ አስተያየት ወይም ትችት የማቅረብ፤ በመገናኛ ብዙሃን ነጻነት ላይ የሚከሰት ጣልቃ ገብነት፣ ተፅዕኖ፣ጥቃትንና የደህንነት ሥጋትን ጨምሮ ሕገመንግሥቱን በመፃረር የፕሬስ ነፃነትን የሚያደናቅፍ አሠራር ከተፈፀመበት በፌደራል ከፍተኛ ፍር ድ ቤት ክስ ወይም አቤቱታ የማቅረብ፤መብት እንዳለው ይደነግጋል፡፡
የኢሰመጉ ጥሪ፡
እነዚህ በተለያዩየሕብረተ ሰብ አባላት ላይ እየተፈጸሙ ያሉ እስራቶች እና እገታዎች ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን፣ የመናገር መብትን፣የፕሬስ ነጻነትን የሚጋፉ እና በአጠቃላይም የፖለቲካ ምህዳሩን የሚያጠቡ በመሆናቸው ኢሰመጉ ይህንን ድርጊት እያወገዘ፤
- የፌደራል እና የሚመለከታቸው የክልል መንግስታት በጋዜጠኞች፣ በማህበረሰብ አንቂዎች፣በተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች፣ በፖለቲካ ፓርቲ አባላት እና አመራሮች እንዲሁም በተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ላይ እየተፈጸሙ ያሉ እስራቶች እና እገታዎችን በአስቸኳይ በማስቆም ይህንን ድርጊት የፈጸሙ የመንግስት አካላትን ተጠያቂ እንዲያደርግ፤
- እስር ላይ ያሉ ጋዜጠኞችን፣ የማህበረሰብ አንቂዎችን፣ ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦችን፣የፖለቲካ ፓርቲ አባላትን እና አመራሮችን ፈጣን ፍትህ የማግኘት መብታቸውን እንዲያከብር ፤
- በመንግስት የጸጥታ አካላት ከተወሰዱ በኋላ ያሉበት የማይታወቁ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ፣የእናት ፓርቲ እና የሌሎች ፓርቲዎች አባላትን እና አመራሮችን መንግስት በአስቸኳይ ያሉበትን ይፋ እንዲያደርግ እና ፈጣን ፍትህ የማግኘት መብታቸውን እንደያከብር ፤
- በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ከግንቦት 2014 ዓ.ም ጀምሮ ህግ ማስከበር ዘመቻ በሚል እየታሰሩ የሚገኙ ሰዎችን ህጉ በሚፈቅደው ጊዜ ፍርድ ቤት በማቅረብ አፋጣኝ ፍትህ የማግኘት መብታቸውን እንዲያከብር፤
- በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በተለያዩ አካባቢዎች በመንግስት የጸጥታ አካላት እንዲሁም በግለሰቦች እየተፈጸሙ ያሉ ግድያ፣ የአካል ጉዳት፣ንብረት ውድመት እና ሌሎችም የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን መንግስት በአስቸኳይ እንዲያስቆም እና ህግ የማስከበር ሀላፊነቱን በአግባቡ በመወጣት ጥሰት ፈጻሚዎችን በህግ አግባብ ተጠያቂ እንዲያደርግ ፤
- ተመሳሳይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሊያስከትሉ የሚችሉ ክስተቶች ዳግም እንዳይፈጠሩ እና አሁን በሂደት ላይ ያሉ አለመግባባቶችን በመፍታት ረገድ የፌደራል እና የክልል መንግስታት፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የማሕበረሰብ አንቂዎች፣ሲቪክ ማህበራት እና የሚመለከታቸው ሁሉ የበኩላቸውን እንዲወጡ ኢሰመጉ ጥሪውን እያቀረበ ወደፊት ተጨማሪ የምርመራ ስራዎችን በመስራት ኢሰመጉ ከላይ የተዘረዘሩትን ጉዳዮች አስመልክቶ ሰፋ ያለ ዘገባን እንደሚያቀርብ ከወዲሁ ይገልጻል።