በኢትዮጵያ የአፋር እና የአማራ ክልሎች የተፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች እና ዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ሕግ ጥሰቶች ላይ የተደረገ ምርመራ ሪፖርት የቀጠለ

88.ጦርነቱ በተካሄደባቸውና ኢሰመኮ በዚህ ምርመራ በሸፈናቸው አካባቢዎች ብቻ ቢያንስ 346 ሲቪል ሰዎች ከሕግ አግባብና ከፍርድ ሂደት ውጪ በጦርነቱ ተሳታፊ ኃይሎች ተገድለዋል፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችም ቀላል እና ከባድ የአካል እንዲሁም የሥነ ልቦና ጉዳት ደርሶባቸዋል። በተለይ የትግራይ ኃይሎች እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት (በተለምዶ ኦነግ ሸኔ በማለት የሚጠራው ታጣቂ ቡድን) በጦርነት ውስጥ ተሳትፎ ያልነበራቸውን በርካታ ሲቪል ሰዎች ላይ ሕገወጥ እና የፍርድ ሂደትን ያልተከተለ ግድያ ፈጽመዋል፤ የአካል እና የሥነልቦና ጉዳት አድርሰዋል። የመከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይል እና የፋኖ ታጣቂዎችም የትግራይ ኃይሎች እና ኦነግ ሸኔ በአማራ እና አፋር ክልሎች የሚገኙ ስፍራዎችን ተቆጣጥረው በነበረበት ወቅት ከታጣቂ ኃይሎቹ ጋር ተባብረዋል ወይም ደጋፊ ናቸው ያሏቸው ሲቪል ሰዎች ላይ ግድያዎችን መፈጸማቸውን ኮሚሽኑ ያሰባሰባቸው መረጃዎች ያሳያሉ።

የሕግ ማዕቀፍ
89.ከፍርድ ውጪ የሚፈጸሙ ግድያዎች ቃሉ እንደሚያመለክተው ሆን ተብሎ ከፍርድ ቤት ሂደት እና ውሳኔ ውጪ በሰዎች ላይ የሚፈጸሙ ግድያዎች ሲሆኑ ከመብቶች ሁሉ መሰረታዊ ተደርጎ የሚወሰደውን በሕይወት የመኖር መብት የሚጥሱ ናቸው።
በሕይወት የመኖር መብት ኢትዮጵያ ፈርማ ባጸደቀቻቸው እንደ ዓለም አቀፍ የሲቪል እና ፖለቲካ መብቶች ቃልኪዳንና የአፍሪካ የሰዎች እና ሕዝቦች መብቶች ቻርተር ያሉ በርካታ ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች እንዲሁም እንደ ሁሉን አቀፍ የሰብአዊ መብቶች መግለጫ ያሉ ልማዳዊ ዓለም አቀፍ ሕግ (International Customary Law/Jus Cogens) ደረጃን የያዙና ሁሉንም ሀገራት የሚገዙ የሕግ ማዕቀፎች ላይ በከፍተኛ ደረጃ ጥበቃ የተደረገለት መብት ነው። በሀገር አቀፍ ደረጃም በሕገመንግስቱ አንቀጽ 15 ጥበቃ የተደረገለት ሲሆን፣ መብቱን በመጣስ የሚፈጸም ከፍርድ ውጪ ሰዎችን የመግደል ድርጊት የወንጀል ተጠያቂነትን እንደሚያስከትል ተደንግጓል።

90.ይህ ምርመራ በለያቸው ከፍርድ ውጪ የተፈጸሙ ግድያዎች በጦርነት አውድ ውስጥ የተፈጸሙ እንደመሆናቸው ከመደበኛው የሰብአዊ መብቶች ሕግ እና የወንጀል ሕግ በተጨማሪ የዓለም አቀፍ የሰብአዊነት/የጦርነት ሕግም ከሌሎቹ የሕግ ማዕቀፎች ጋር ተመጋጋቢ የሆነ ተፈጻሚነት ይኖረዋል። በመንግሥት፣ በትግራይ ኃይሎች እና በኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች መካከል የተካሄደው ጦርነት በዓለም ዓቀፍ የሰብአዊነት ሕግ መሰረት ዓለም አቀፋዊ ያልሆነ ጦርነት ተብሎ የሚመደብ እንደመሆኑ፣ በጦርነቱ ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም ኃይሎች ሲቪል ሰዎችን ጨምሮ በሕጉ ልዩ ጥበቃ የተደረገላቸውን ሰዎች ከሞት እና ከአካል ጉዳት የመጠበቅ ግዴታ አለባቸው።39 ጦርነትን በሚያካሂዱበት ወቅትም
እነዚህኑ ዒላማ ከማድረግ መቆጠብ፣ ጉዳት እንዳይደርስባቸው ተገቢ የሆነ ጥንቃቄ ማድረግ፣ ጥበቃ የተደረገላቸውን ሰዎች ከተዋጊ ኃይሎች መለየትን እና ኃይል ለመጠቀም አስገዳጅ ሁኔታዎች በሚኖሩበት ጊዜም ቢሆን ተመጣጣኝነትን ታሳቢ ባደረገ ሁኔታ እርምጃ መውሰድ ይጠበቅባቸዋል። እነዚህን መስፈርቶች ባልተከተለ መልኩ በሚወሰድ እርምጃ የሚከሰት የሲቪል ሰዎች እና ሌሎች ጥበቃ የተደረገላቸው ሰዎች ሞት በሕይወት የመኖር መብትን የሚጥስ ሲሆን በሰብአዊነት ሕግ መሰረት የጦር ወንጀል (war crime) ሊሆንም ይችላል። 

የምርመራው ግኝቶች
91.የትግራይ ኃይሎች ወደ አማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ዳባት ወረዳ ጭና ቀበሌ ነሃሴ 24 ዕለት ሌሊቱን በመግባት እስከ ነሃሴ 29 ቀን 2013 ዓ.ም. ቀበሌውን ተቆጣጥረው በቆዩበት ወቅት ቢያንስ 47 ሲቪል ሰዎችን (ወንድ 41 ሴት 6) ገድለዋል። ሟቾች በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ እንዲሁም ከተያዙ በኋላ እጆቻቸው ወደኃላ ታስረው የተገደሉ ሲሆን፣ በተለይም የመንግሥት ኃይሎች ወደ ቀበሌው እየተቃረቡ በመምጣታቸው የትግራይ ኃይሎች ሲያፈገፍጉ በየቤቱ እና በየሰፈሩ ያገኟውን ነዋሪዎች እየገደሉ መሄዳቸውን ኮሚሽኑ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል። የተጎጂዎች ቤተሰብ የሆኑ የሃይማኖት አባት ስለሁኔታው ሲያስረዱ፦

“ነሃሴ 24 ሌሊት (2013 ዓ.ም) ቤት ለቤት እየዞሩ፣ የት ትወጣላችሁ?፣ የት ትሄዳላችሁ? እያሉ እንዳንወጣ ከለከሉን። ነሃሴ 25ቀን (2013 ዓ.ም.) ጠዋት ሸሽተው የቆዩ አንድ ልጄ እና የወንድሜ ልጅ እኔን ለመጠየቅ ወደ ቤት ተመለሱ። ይህንን ያዩ የትግራይ ኃይሎች ታጣቂዎች የቤቱን በር እንድከፍት አዘዙኝ። በር ከፍቼ፣ 2 ወጣት ልጆች ቤት ውስጥ አሉኝ ብዬ አስረዳሁ። እነሱም ልጆቹ ምንም ትጥቅ እንደ ሌላቸው አጣርተው ከቤት እንዲቀመጡ አስጠንቅቀውን ወጡ። በዚሁ መሰረት እስከ ነሃሴ 27 ቀን (2013 ዓ.ም.) ቤት ውስጥ ያለ ምግብ ቆየን። ነሃሴ 27 ቀን (2013 ዓ.ም.) 6፡00 ሰዓት ሲሆን ልጆቹ እርቧቸው ከቤት ወጥተው ከጎረቤት ምግብ ወስደው ሲመለሱ ምግቡን ተቀብለዋቸው በጥይት መትተው ገደሏቸው። በእለቱ ቀብር ስለተከለከልን በማግስቱ ሌሊት 8፡00 ሰዓት በጭና ተክለኃይማኖት ቤተክርስቲያን ቀብራቸው ተፈጸመ።” ብለዋል።

92.ልጃቸው እና ጨቅላ ሕፃን የልጅ ልጃቸው በትግራይ ኃይሎች የተገደሉባቸው አንድ ነዋሪ ሁኔታውን ለኮሚሽኑ ሲያስረዱ፦

“በግጭቱ ጊዜ የአዕምሮ ጭንቀት የጤና ችግር ያለባት እና ሕፃን ልጅ ያላት ልጄ ከኔ ጋር ነበረች። በጦርነቱ ምክንያት ተረብሻ ወጥታ ነበር። ነገር ግን ልጄ ከእነ 11 ወር ሕፃን ልጇ በጥይት ተገድላ በሜዳ ወድቃ ተገኘች። ባለቤቴ ደግሞ መጀመሪያ እንደወጣ አልተመለሰም። የት እንደተወሰደ አላውቅም።” ብለዋል።

93.ኮሚሽኑ ያነጋገራቸው አንዲት የቀበሌው ነዋሪ እንዳስረዱት የትግራይ ኃይሎች የቤታቸውን በር እንዲከፍቱ ሲያዟቸው እምቢተኛ በመሆናቸው በበር ቀዳዳ ተኩሰው እግራቸውን በጥይት ያቆሰሏቸው ሲሆን ከሁለት ቀናት በኃላ ደግሞ የሃይማኖት አባት የሆኑ ባለቤታቸውን ቤታቸው በር ላይ በጥይት መተው ከገደሉ በኋላ አስከሬናቸው ለሦስት ቀናት ቆይቶ ተቀብሯል። ይህ ከሆነ በኋላም የ7 ዓመት ሕፃን ልጃቸውን “ይህ አድጎ ነው የሚወጋን” በማለት ገድለውት እንደሄዱ ገልጸዋል። በጭና ቀበሌ በትግራይ ኃይሎች በተፈጸመው ጥቃት የሞቱ ነዋሪዎች በጭና ተክለኃይማኖት እና ዲና ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያናት ቀብራቸው ተፈጽሟል። ኮሚሽኑ በጭና ተክለኃይማኖት ቤተክርስቲያን የጅምላ መቃብሮችን የተመለከተ ሲሆን፣ በሃይማኖት አባቶች እና በተጎጂዎች ቤተሰቦች በአንድ መቃብር እስከ 12 ሰዎች የተቀበሩ መሆኑን ገልጸዋል።

94.የትግራይ ኃይሎች ከሸዋ ሮቢት ከተማ አቅራቢያ በምትገኘው በቀወት ወረዳ የለን ቀበሌ ሲደርሱ የአካባቢው የሚሊሺያ ኃይል ውጊያ ገጥሞ አንድ የትግራይ ኃይሎች አመራር፣ አንድ ታጣቂ፣ እና ከእነርሱ ጋር የመጡ የጤና ባለሙያዎች መገደላቸውን ተከትሎ፤ የትግራይ ኃይሎች ታጣቂዎች ኅዳር 10 ቀን 2014 ዓ.ም. ዕድሜያቸው ከ12 እስከ 55 ዓመት የሚሆናቸው 19 ወንዶችና 1 ሴት አጠቃላይ 20 ሲቪል ሰዎችን በመንገድ ላይ፣ በቤታቸው አካባቢና በቤታቸው ውስጥ እንዳሉ በመያዝ እና አንዳዶችን እጃቸውን ወደኃላ በማሰር በጥይት መትተው ገድለዋል። አንድ የዓይን ምስክር በሚከተለው መልኩ ያየችውን አስረድታለች፦

“ኅዳር 10 ቀን (2014 ዓ.ም.) ከሸሸሁበት ተመልሼ ነበር። ተኩስ ሲጀመር ከአንድ ሰው ጋር ማሽላ ውስጥ ተደብቀን ቆይተን ወደሌላ ቦታ ለመሸሽ ስንወጣ [የትግራይ] ታጣቂዎች እኛን እና ሌሎች ሁለት ሰዎችን ያዙን። ከኔ ጋር የነበሩትን ሦስቱን ሰዎችን ጫማ አስወልቀው ከደበደቧቸው በኋላ ዓይኔ እያየ ሦስቱንም ሰዎች በጥይት ደረታቸውን መትተው ገደሏቸው። እነርሱ ከተገደሉበት ቦታ ሌሎች ሦስት ሰዎች ተገድለው አስከሬናቸውን ወድቆ አይቻለሁ። እኔን መረጃ ስጪን ብሎ አንዱ ከመታኝ በኋላ ተነጋግረው ለቀቁኝ።” ብላለች።

ሌላ የአንድ ሟች ቤተሰብ እና ምስክር ስለድርጊቱ ለኮሚሽኑ ሲያስረዳ፦

“ኅዳር 10 ቀን (2014 ዓ.ም.) እኔ ከሸሸሁበት ቦታ 11፡00 ሰዓት ላይ ተመልሼ ስመጣ አንድ ወንድሜን እና አንድ የአጎቴን ልጅ ጨምሮ 8 ሰዎች አባዙር የውሀ መተላለፊያ ቦይ አካባቢ በሽርጣቸው እጃቸውን ወደ ኃላ ታስረው የተለያየ አካላቸው በጥይት ተመትተው ተገድለው አገኘኋቸው። የሁሉንም አስከሬን ከአንድ ሰው ቤት አሳድሬ በማግስቱ ስድስቱን ማሪያም ቤተ ክርስቲያን እና ሁለቱን ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ቀበርናቸው።” ብሏል።

95.በሰሜን ሸዋ ዞን በአንፆኪያ ገምዛ ወረዳ አሰለሌ ቀለበት ወንበር ቀበሌ ወደሚገኘው አምቦውሃ ጎጥ ኅዳር 23 ቀን 2014 ዓ.ም. ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የትግራይ ኃይሎች ታጣቂዎች በ3 አቅጣጫ ሲገቡ፣ የአካባቢው አርሶ አደሮች እና የሚሊሺያ ውጊያ ገጥመዋል። የትግራይ ኃይሎች ከተማውን እንደተቆጣጠሩ በሼህ አብደላ መካነ መቃብር ቦታ በዕለቱ በሕመም ምክንያት የሞቱ አንዲት የመንደሩን ነዋሪ ለመቅበር የተሰበሰቡ ሲቪል ሰዎች ላይ በከፈቱት ተኩስ 13 ለቀብር የወጡ ሲቪል ሰዎችን (ሁሉም ወንዶች ናቸው) ገድለዋል። ከዚህ ቀጥሎም የትግራይ ኃይሎች ታጣቂዎች ቤት ለቤት በመግባት 27 ሲቪል ሰዎችን በጥይት ገድለዋል። በዚህም በአሰለሌ ቀለበት ወንበር ቀበሌ ብቻ በኅዳር 23 ቀን 2014 ዓ.ም. በጠቅላላው 40 ሲቪል ሰዎችን የትግራይ ኃይሎች መግደላቸውን ኮሚሽኑ ከተጎጂዎች፣ ከቤተሰቦቻቸው እና ከምስክሮች ተረድቷል። ከተገደሉት ሲቪል ሰዎች በተጨማሪ የትግራይ ኃይሎች በ85 ሲቪል ሰዎች ላይ የተለያየ መጠን ያለው የአካል ጉዳት ማድረሳቸውን ከወረዳው አስተዳደር ጽሕፈት ቤት የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

96.ነሐሴ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. በአፋር ክልል በበርሀሌ ወረዳ አላ ቀበሌ የትግራይ ኃይሎች ባደረሱት ጥቃት ዕድሜያቸው ከ3 ወር እስከ 15 ዓመት የሆኑ 6 ሕፃናትን ጨምሮ 13 ሲቪል ሰዎች ተገድለዋል። አንዲት 6 የቤተሰብ አባሎቿ በጥቃቱ የተገደሉባት ነዋሪ ስለሁኔታው እንደሚከተለው አስረድታለች፦

“ የመንደሩ ብዙ ሰዎች ከገበያ ውለን ስንመለሰ የወታደር ልብስ የለበሱ የትግራይ ታጣቂዎች ቤታችን አካባቢ ተሰብስበው አየናቸው። ወዲያው ወደ እኛ ጥይት መተኮስ ጀመሩ። ቦምብ ወረወሩብን። እኛም መሸሽ ጀመርን። ከእኔ ጋር ሲሸሹ የነበሩ ቤተሰቦቼ በቦምብ እና ጥይት እየተመቱ ወደቁ። በእህቴ ጀርባ ላይ ታዝሎ የነበረ የ3 ወር ሕፃን ልጅም በጥይት ተመቶ ተገደለ። ኃዘኔን በጣም ያከፋውና ያመመኝ ሳይቀበሩ መቅረታቸው ነው።” ብላለች።

97.የትግራይ ኃይሎች አፋር ክልል ደራይቱ ከተማ መግባታቸውን ተከትሎ የከተማው ነዋሪ ወደ ተለያየ ቦታ ሲሸሽ በወቅቱ በነበረባት ህመም መሸሽ ያልቻለች አንዲት እናት ተገድላ የተገኘችበትን ሁኔታ የሟች ቤተሰብ ለኮሚሽኑ እንደሚከተለው አስረድቷል፦

“ሟች የእናቴ ዘመድ ናት። ጎረቤት ነበርን። 5 ልጆች ነበሯት። አንደኛው ልጅ የሚጠባ ሕፃን ነው። ጦርነቱ ተጀምሮ ማታ ሁሉም ሰው ሲሸሽ እኛም አሴላ ወደሚባል ቦታ ሸሸን። እሷ ግን ሰውነቷ መንቀሳቀስ ስላልቻለ እርሷን፣ የሚጠባው ልጇን እና ከሱ ከፍ የሚለውን ልጅ እዛው ትተን መሄድ የሚችሉትን ልጆቿን ብቻ ይዘን ወደ ገጠር ሸሸን። አካባቢው ተረጋግቷል ተብሎ ስንመለስ እሷ ሞታ ሕፃኑ ልጇ ጡቷን እየጠባ አገኘነው። እኔ ከሷ ልጆች ሁለቱን እያሳደግሁ ነው።”

98.ጥቅምት 24 ቀን 2014 ዓ.ም. በግምት ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት ሲሆን በአፋር ክልል ካሳጊታ ከተማ አትኮማ አካባቢ የዘጠኝ ዓመት ሕፃን እና የ18 ዓመት ሴት ታዳጊ ውሃ ለመቅዳት ወደ አስኤላ ወንዝ በሄዱበት በትግራይ ኃይሎች በተተኮሰ ጥይት እንደተገደሉ ምስክሮች እና የተጎጂ ቤተሰቦች ገልጸዋል። ኮሚሽኑ ያነጋገረው የዓይን እማኝ እንደገለጸው ልጆቹ ውሃ እየቀዱ እያሉ ሦስት የትግራይ ኃይሎች ታጣቂዎች አንደኛዋን አንገቷ ላይ ሁለተኛዋን ደግሞ በግንባሯ ላይ በጥይት በመምታት ገድለዋቸዋል። በወቅቱ ድርጊቱን የተመለከቱ ግለሰብ ለኮሚሽኑ ሲያስረዱ፦

“የዘጠኝ ዓመት ሕፃኗን አስከሬን ተሸክሜ ወደ ቤት ስወስድ የትግራይ ታጣቂዎች መንገድ ላይ አግኝተውን “ወደ የት ነው የምትወስዳት? አፋሮች ሁሉ አንድ ናቸው” በማለት በእኔም ላይ ተኩሰውብኝ እጄ ቆስሏል።” በማለት አስረድተዋል።

99.በሰሜን ወሎ ዞን የሚገኘው የጋሸና ከተማ በመንግሥት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል በተለያያ ወቅት ከፍተኛ ውጊያ ተካሂዶበታል። ከሐምሌ 28 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ የትግራይ ኃይሎች ከተማዋን ለአራት የተለያዩ ጊዜያት ተቆጣጥረው ቆይተዋል። በነዚህ ጊዜያት “መከላከያ ሠራዊትን አግዛችኋል፣ ምግብ ውሃ ሰጥታችኋል፣ አስጠልላችኋል፣ የፋኖ፣ የልዩ ኃይል ወይም የሚሊሺያ አባል ናችሁ፣ መሳሪያ ስጡን” በሚሉ እና ሌሎች ምክንያቶች ቢያንስ 57 ሲቪል ሰዎችን ገድለዋል። ነሐሴ 16 ቀን 2014 ሌሊት በጋሸና ከተማ ቀበሌ 13 ልዩ ቦታው ዳና ጊዮርጊስ አካባቢ በመንግሥት ወታደሮችና በትግራይ ኃይሎች መካከል ውጊያ ሲካሄድ ቆይቶ በአካባቢው የነበሩ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ወደ አንድ ቤተሰብ ቤት በመምጣት ምግብ እንዲሰጧቸው ጠይቀው ከተመገቡ በኋላ አስቀድመው ማርከው ይዘዋት የነበረች አንድ የትግራይ ኃይሎች ታጣቂን ሌሊቱን ከቤታቸው በር ላይ ገድለዋት ሄዱ። በነጋታው ነሐሴ 17 ቀን ጠዋት የትግራይ ኃይሎች ታጣቂዎች ወደ አካባቢው ሲደርሱ የሟቿን አስክሬን በራቸው ላይ በማየታቸው መኖሪያ ቤታቸውን አስከፍተው የቤቱን አባወራ ከደበደቡ እና ካሰቃዩ በኋላ ወደ ጓሮ በመውሰድ በሚስትና በልጆቻቸው ፊት ገድለዋቸዋል። የ21 እና የ25 ዓመት ወጣት የሆኑ ሁለት የሟች ወንድ ልጆችን ደግሞ አስረው ወደ ኮን (የዋድላ ወረዳ ዋና ከተማ) ከወሰዷቸው በኋላ በዚያው ገድለዋቸው፣ አስክሬናቸው ተመልሶ ዳና ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን መቀበሩን የሟቾች ቤተሰቦች ለኮሚሽኑ አስረድተዋል።

100. በአማራ ክልል ደባርቅ ወረዳ ቦዛ ቀጠና በሚባሉ የአዲጋግራ፣ የአብርሃም እና የአዳጋት ቀበሌዎችን ከነሐሴ 12 እስከ ነሐሴ 29 ቀን 2013 ዓ.ም. የትግራይ ኃይሎች ተቆጣጥረው ቆይተዋል። በቀበሌዎቹ በቆዩባቸው ቀናት የትግራይ ኃይሎች 20 ሲቪል ሰዎችን (17 ወንድ 3 ሴት) ተኩሰው ገድለዋል። ኢሰመኮ ያነጋራቸው ምስክሮች ሟቾች በቤታቸው እያሉ፣ በመንገድ ላይ ሲንቀሳቀሱ እና ከብት በመጠበቅ ላይ እንዳሉ በጥይት ተመትተው የተገደሉ መሆኑን አስረድተዋል። በተጨማሪም የትግራይ ኃይሎች የመቄት ወረዳን ተቆጣጥረው በነበሩበት ወቅት 74 ሲቪል ሰዎችን መግደላቸውን የአካባቢው አስተዳደር አካላት ይገልጻሉ። ኮሚሽኑ በምርመራው በመቄት ወረዳ በደብረዘቢጥ ቀበሌ ብቻ የ7 ዓመት ሕፃንን ጨምሮ 5 ሰዎች በትግራይ ኃይሎች መገደላቸውን አረጋግጧል።

101. በሰሜን ወሎ ዞን በዋድላ ወረዳ ሐሙሲት ከተማ ጥቅምት 6 ቀን 2014 ዓ.ም. ከምሽቱ 1፡00 ሰዓት ገደማ ለሌሊት የቤተክርሲቲያን አገልግሎት ቤተ-ክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውስጥ የተቀመጡ 12 አገልጋዮችን የትግራይ ኃይሎች ታጣቂዎች “የቆሰሉ የአብይ ወታደሮችን ደብቃችኋል፤ አሳዩን” በሚል ከቤተ-ክርስቲያኑ ቅጥር ግቢ ካስወጡ በኋላ በደረታችው እንዲተኙ አደርገው ደብድበዋል። ሰዎቹም ወደ ቤተ-ክርስቲያን የመጡት ለአገልግሎት ብቻ እንደሆነና የመንግሥት ወታደር እንዳልደበቁ ቢገልጹም የቤተ-ክርስቲያኑን ቄሰ-ገበዝ እና የዕቃ ቤት ኃላፊ ተኩሰው ገድለዋቸዋል። በስፍራው የነበሩ አንድ ካህን ሁኔታውን ሲያስረዱ፦

“ቄስ [ስም]ን ከገደሉት በኋላ እኔን ከአስከሬኑ ጎን አስተኝተው እንደዚህ ቄስ ከምናደርግህ እውነቱን ተናገር አሉኝ። እኔም ለአገልግሎት ነው የመጣሁት የማውቀው ነገር የለም አልኳቸው። ሌሎችንም እንደዛ አደረጓቸው ግን የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ነገሯቸው። ከዚያም የቀረነውን አገልጋዮች እዚያው ሐሙሲት ከተማ ከቅዳሜ ምሽት 5፡00 ሰዓት ጀምሮ እስከ እሁድ ከሌሊቱ 5፡00 ሰዓት ድረስ ባዶ ቤት ውስጥ ያለ ምግብና ውሃ አስረው አቆይተውን ለቀቁን” ብለዋል።

102. ኮሚሽኑ በደሴ ከተማ ከተጎጂ ቤተሰቦች፣ ምስክሮች እና ከመንግሥት አካላት ባገኘው መረጃ መሰረት የትግራይ ኃይሎች በከተማው ከጥቅምት 20 ቀን 2014 ዓ.ም. እስከ ኅዳር 28 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ በቆዩበት አንድ ወር ከስምንት ቀን ጊዜ በርካታ ሲቪል ዜጎች መግደላቸውን አረጋግጧል። ደሴ ከተማ በገቡባቸው የመጀመሪያ ሁለት ቀናት ማለትም ጥቅምት 20 እና 21 ቀን 2014 ዓ.ም. በከተማው ልዩ ስሙ ጢጣ በሚባለው አካባቢ የትግራይ ኃይሎች ታጣቂዎች ወደ ደሴ ከተማ ሲገቡ መንገድ ላይ በመገኘታቸው ብቻ እድሜያቸው ከ20-50 ዓመት የሆኑ ስድስት ሰዎችን (5 ወንድ ፣ 1 ሴት) በጥይት ተኩሰው ገድለዋል። ኮሚሽኑ ያነጋገራቸው ምስክሮች ትክክለኛ ቀኑን በማያስታውሱት ዕለት በከተማው ሀገር ግዛት ቀበሌ ልዩ ቦታው ወ/ሮ ስህን ኮሌጅ አካባቢ አንድ የትግራይ ኃይሎች ታጣቂ በአካባቢው ተቀምጦ የሕዝቡን እንቅስቃሴ ሲያይ ቆይቶ ድንገት መተኮስ በመጀመሩ ውሃ በመቅዳት ላይ የነበረ አንድ የ14 ዓመት ወንድ ሕፃን ሕይወቱ ያለፈ ሲሆን በተገደለው ልጅ ሰውነት አልፎ የወጣው ጥይት የ9 ዓመት ሴት ሕፃን ቁርጭምጭሚት ላይ በማረፍ የአካል ጉዳት አድርሷል። በደሴ ከተማ የምርመራ ስራ እያከናወኑ የሚገኙ የፌዴራል ዐቃብያነ ሕግ የትግራይ ኃይሎች ደሴ ከተማን ተቆጣጥረው በቆዩባቸው ጊዜያት 40 ሰዎችን መግደላቸውን እንዲሁም በ85 ሰዎች ላይ ከባድ እና ቀላል የአካል ጉዳት ማድረሳቸውን ለኮሚሽኑ ገልጸዋል።

103. የትግራይ ኃይሎች ከጥቅምት 21 እስከ ኅዳር 25 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ የኮምቦልቻ ከተማን ተቆጣጥረው ቆይተዋል። ኮሚሽኑ ባደረገው ምርመራ የትግራይ ኃይሎች በከተማው በርካታ ሲቪል ሰዎችን መግደላቸውን እና ማቁሰላቸውን ከዓይን እማኞች፣ ከሟቾች እና ተጎጂዎች ቤተሰቦች፣ ከሕክምና ተቋማት እንዲሁም ከመንግሥት አካላት አረጋግጧል። ጥቅምት 21 ቀን 2014 ዓ.ም. በግምት ከቀኑ 8 ሰዓት ዲዳ በሚባል አካባቢ በመንገድ ላይ ሲሄድ የነበረ የ26 ዓመት ወጣት ቁም ሲሉት ሮጦ ሌላ ሰው ቤት በመግባቱ ወጣቱ የገባበት ቤት ተከትለው በመግባት ወጣቱን እና ቤት ውስጥ የነበረች አንዲት ሴትን ተኩሰው የገደሉ ሲሆን፣ ሌላ የ6 ዓመት ሕፃን ታፋዋ ላይ በጥይት ተመትታ የአካል ጉዳት ደርሶባታል። ጥቅምት 21 ቀን 2014 ዓ.ም. ቀበሌ 03 ልዩ ቦታው በርቸሌ በሚባል ቦታ ከሌሊቱ 7፡00 ሰዓት አካባቢ “የትግራይ ኃይሎች ታጣቂዎች የተደበቀ ስንቅ እና መሳሪያ አለ አምጪ በተጨማሪም በሆቴል ቤትሽ ውስጥ የሚሰሩ ሴት ሰራተኞችን አቅርቢልን” በማለት እድሜዋ 35 ዓመት የሚሆናትን የቤቱን ባለቤት ሦስት ቦታ ላይ በጥይት በመምታት ከባድ የአካል ጉዳት ማድረሳቸውን እንዲሁም በ12 ዓመት ሴት ልጃቸው (ግራ እግር ባት) ላይ በጥይት በመምታት ቀላል የአካል ጉዳት ማድረሳቸውን፤ በተጨማሪም ጥቅምት 23 ቀን 2014 ዓ.ም. ከቀኑ 9፡00 ሰዓት አካባቢ ተመልሰው ወደ ቤቱ በመምጣት 55 ዓመት የሆናቸውን አባት “መሳሪያ ደብቀሀል አምጣ” በሚል ጭንቅላታቸውን በመደብደብ ጉዳት አድርሰውባቸዋል። 

104. የትግራይ ኃይሎች አጣዬ ከተማን ኅዳር 6 ቀን 2014 ዓ.ም. እንደተቆጣጠሩ በከተማው 01 ቀበሌ ነዋሪ የነበሩ አንድ ነጋዴ ቤት ውስጥ ከገቡ በኋላ የግለሰቡን እንቅስቃሴ በማገት ቤት ውስጥ አብረው ለ5 ቀናት ከቆዩ በኋላ ኅዳር 10 ቀን 2014 ዓ.ም. አጣዬ ከተማ ቀበሌ 01 ልዩ ስሙ ኤፌሶን ቁጥር 2 ትምህርት ቤት ውስጥ “ፋኖ ትቀልባለህ፣ ወታደር ታበላለህ፣ ቤትህ ካምፕ ነው” በሚል አስረው በማቆየት ለኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች አሳልፈው ሰጥተዋቸዋል። የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች “ሁለተኛውን አብይ አግኝተናል” እያሉ በከተማ ውስጥ የመከላከያ ሠራዊትን ዩኒፎርም አስይዘው ካስዞሯቸው በኋላ ኅዳር 13 ቀን 2014 ዓ.ም. ልዩ ስሙ ጃራ ዎታ ከሚባል ቦታ ላይ ገድለዋቸዋል። አስከሬናቸው ከ16 ቀናት በኋላ ተነስቶ ኅዳር 28 ቀን 2014 ዓ.ም. አጣዬ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ-ክርስቲያን የተቀበረ መሆኑን የሟች ቤተሰቦች ለኮሚሽኑ ገልጸዋል።

105. በአጣዬ ከተማ የ01 ቀበሌ ኅዳር 14 ቀን 2014 ዓ.ም. የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች የቀበሌው አመራር የነበሩ ግለሰብን አባት እና ወንድም ከቤታቸው በመያዝ “ልጃችሁን አምጡ” ካሏቸው በኋላ በባጃጅ በማሳፈር ልዩ ስሙ ቆሮ ከሚባል ቦታ ላይ በመውሰድ ገድለዋቸዋል። ኮሚሽኑ ያነጋገራቸው የቀበሌው አመራር እንደገለጹት በኅዳር 17 ቀን 2014 ዓ.ም. የሟች ወንድማቸውን አስከሬን በተገደለበት ቦታ ላይ ማግኘት ቢችሉም የአባታቸው አስክሬን ግን በጅብ የተበላ በመሆኑ ሳያገኙት መቅረታቸውን ገልጸዋል።

106. በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ደዋ ጨፋ ወረዳ ልዩ ቦታው እንቶሊ አካባቢ በታኅሣሥ ወር 2014 ዓ.ም የመጀመሪያ ሳምንት (ቀኑ በትክክል ያልታወቀ) የመከላከያ ሠራዊት አባላት ወታደሮች በሁለት አይሱዙ መኪኖች ተጭነው የመጡ ቁጥራቸው ወደ 30 የሚጠጉ የኦነግ ሸኔ አባሎች ናቸው ያሏቸውን ሰዎች በጅምላ በጥይት ደብድበው ገድለዋል። ኮሚሽኑ ያነጋገራቸው ምስክሮች ስለተገደሉት ሰዎች ሲያስረዱ “ወጣቶች እና ረጃጅም ጺም የነበራቸው ትላልቅ ሰዎች” በማለት የገለጿቸውን ሰዎች የመከላከያ ሠራዊት አባላቱ በተሽከርካሪ ጭነው ወደስፍራው ካመጧቸው በኋላ ግድያ በተፈጸመበት ቦታ ለ 3 ቀናት ያክል ድብደባ እየፈጸሙባቸው ቆይተው በጥይት ደብድበው ገድለዋቸዋል፤ ግድያውን ከፈጸሙ በኋላ ወታደሮቹ በቦታው የሟቾች አስከሬን እንዳይነሳ ክልከላ ሲያደርጉ ቆይተው የሔዱ በመሆኑ አስክሬኖቹ እየሸተቱ ከ10 ቀናት በላይ ሳይቀበሩ እንደቆዩ ተናግረዋል። 

107. ታኅሣሥ 14 ቀን ኢሰመኮ በስፍራው ከመድረሱ ሶስት ቀናት አስቀድሞ የአካባቢው ነዋሪዎች ሟቾችን አፈር አልብሰዋቸዋል። አስከሬኖቹ አፈር ከመልበሳቸው በፊት የተመለከቱ ግለሰብ ለኮሚሽኑ እንዳስረዱት የተገደሉት ሰዎች ከደዋጨፋ ወደ ካራቆሬ ከተማ በሚወስደው የአስፋልት መስመር ዳር ላይ ሳይቀበሩ ለረጅም ቀናት የቆዩ በመሆኑ ለንግድ ስራ በመንገዱ በሚመላለሱበት ወቅት የተገደሉት ሰዎችን ማንነት ለማጣራት ሲሞክሩ የኦነግ ሸኔ አባላት እንደሆኑና ባቲ ከተማ አካባቢ ተይዘው መጥተው የተገደሉ መሆኑን ከአካባቢው ሰዎች መስማታቸውን ገልጸዋል። በተጨማሪም አንድ የደዋጫፋ ከተማ ነዋሪ የሆነ ወጣት ለንግድ ስራ ከደዋ ጨፋ ወደ ሰንበቴ ከተማ በመሄድ ላይ እያለን ከዚህ አካባቢ የተረሸኑ የአነግ ሸኔ አባላት ሳይቀበሩ አሉ እንያቸው ተብሎ ተሳፋሪው ከመኪና በመውረድ ሲመለከት አብሮ የነበረ መሆኑን በመግለጽ መቼ እና በማን እንደተገደሉ እንዳላየ ይሁን እንጅ በመከላከያ ሠራዊት እርምጃ የተወሰደባቸው ሰዎች ናቸው ሲባል እንደሰማ እና አስከሬናቸው ወድቆ መመልከቱን ገልጿል። ኮሚሽኑ ግድያው የተፈጸመበት ስፍራ በተገኘበት ወቅት አፈር ያልለበሰ የአንድ ሰው አስከሬን፣ የሌላ ሟች የተቆረጠ ጭንቅላትን ጨምሮ የተቆራረጠ የሰውነት ክፍል እና የተለያዩ የሲቪል ሰዎች ልብሶችን በስፍራው ተመልክቷል።

108. በሰንበቴ ከተማ ቆደማ የገጠር ቀበሌ ኅዳር ወር 2014 ዓ.ም ረቡዕ ዕለት ከምሽቱ 1፡00 ሠዓት ሲሆን 5 ሰዎች ከመኖሪያ ቤታቸው የሸኔ አባል ናችሁ ተብለው ተጠርጥረው በመከላከያ ከተያዙ በኋላ አንዱ ሮጦ ማሽላ ማሳ ውስጥ በመግባት ሲያመልጥ የቀሩት 4 ሰዎች (ሦስት ወንድማማቾች እና አንድ የአጎታቸው ልጅ) ከመኖሪያ ቤታቸው አቅራቢያ በጥይት ተገድለው ተገኝተዋል። የአካባቢው የሀገር ሽማግሌዎች እነዚህን ልጆች የት እንዳደረሷቸው የመከላከያ ሰራዊቱን ጠይቀው የነበረ ቢሆንም “ወደ ሸዋሮቢት ልከናቸዋል” የሚል መልስ ማግኘታቸውን፤ ነገር ግን ሟቾቹ መኖሪያ ቤታቸው አቅራቢያ ተገድለውና ተቀብረው እንደተገኙና አስከሬናቸው በቤተሰብ ወጥቶ በመቃብር ስፍራ የተቀበሩ መሆኑን ምስክሮች አስረድተዋል።

109. ኅዳር 20 ቀን 2014 ዓ.ም. በአማራ ክልል አርቢት ከተማ አካባቢ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ጤፍ ሲያጭዱ የነበሩ ሰዎችን አስቁመው እንዴት “በዛሬው ቀን ጤፍ ታጭዳላችሁ የጁንታ ተባባሪ ናችሁ” በማለት ከደበደቧቸው በኋላ ከመካከላቸው አንድ ሰውን ገድለው ሌሎች ሦስት ሰዎችን እንዳቆሰሉ በወቅቱ ቦታው ላይ ነበሩ እማኞች ለኮሚሽኑ አስረድተዋል።

110. ኅዳር 21 ቀን 2014 ዓ.ም. በአማራ ክልል በሰሜን ወሎ ዞን በላስታ ወረዳ 024 ቀበሌ ዳቦ ከተማ ውስጥ ከቀኑ 8፡00 አካባቢ የአማራ ልዩ ኃይል አባላት በቤት ለቤት ፍተሻ ላይ በነበሩበት ወቅት ጦርነቱን በመፍራት በሯን ዘግታ በቤት ውስጥ ሕፃን ቃቅፋ የተቀመጠች አንዲት ሴት ላይ “የትግራይ ኃይሎችን ቀልባችኋል” በሚል በሩ እንደተዘጋ ተኩሰው እናትየውን ግራ እግሯ ላይ፤ ህጻኗን ደግሞ ግራ እጇ ላይ በጥይት የመቷት ሲሆን ህጻኗ ሕክምና በማጣቷ ደም ፈሷት መሞቷን ኮሚሽኑ ያነጋገራቸው እማኞች አስረድተዋል። 

111. ሰንበቴ ከተማ በመንግሥት ኃይሎች ቁጥጥር ስር ከገባች በኋላ ቢያንስ አራት ሲቪል ሰዎች በተለያየ ቀን በፋኖ ታጣቂዎች ተገድለዋል። አንድ ግለሰብ በአጣዬ ከተማ የመከላከያ ሠራዊትን የሚጫን እቃ አግዞ ሲመለስ እንደተገደለ ከዚያም የእርሱ የቀብር ስነስርአት ላይ ለመቃብር ጭቃ መመረጊያ ውሃ ሊያመጣ የሔደ አንድ ሰው በሄደበት በፋኖ ታጣቂዎች እንደተገደለ በዚህም ምክንያት የቀብር ስርአቱ ከተቋረጠ በኋላ በነጋታው በመከላከያ ሠራዊት አጋዥነት ቀብሩ መፈጸሙን ኮሚሽኑ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል። ሌሎች ሁለት የከተማው ነዋሪዎችን ደግሞ የፋኖ ታጣቂዎች ከሰንበቴ ከተማ ወደ አጣዬ ወስደው እንደገደሏቸውና አስክሬናቸው እንዳይነሳ ተከልክሎ በጅብ ከተበላ
በኋላ የሟች ቤተሰቦችን በሚያውቁ ሰዎች አማካይነት ተነግሯቸው አስክሬኖችን አንስተው መቅበራቸውን የሟች ቤተሰቦች ለኮሚሽኑ አስረድተዋል።

112. በሌላ በኩል መንግሥት የሸዋ ሮቢት ከተማን ከተቆጣጠረ በኋላ ኅዳር 23 ቀን 2014 ዓ.ም. የትግራይ ተወላጆች የሆኑ እና የትግራይ ኃይሎችን ደግፋችኋል በሚል አራት ወንድ ሲቪል ሰዎች በፋኖና የአርሶ አደር ታጣቂዎች ተገድለው አስክሬናቸው መንገድ ላይ ለሦስት ቀን ያህል ከቆየ በኋላ ኅዳር 25 ቀን 2014 ዓ.ም. ተነስቷል። በተመሳሳይ ሁኔታ የተገደሉ ተጨማሪ ሲቪል ሰዎች ስለመኖራቸው ለኮሚሽኑ መረጃዎች የደረሱት ቢሆንም ለማረጋገጥ አልተቻለም።

113. በጦርነቱ ተሳታፊ ወገኖች በተለይ ከፍርድ ውጪ ግድያ ከተፈጸመባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የአዕምሮ ሕሙማን ይጠቀሳሉ። በዚህ ላይ የኮሚሽኑ የምርመራ ግኝቶች በአረጋውያን እና የአካል ጉዳተኞች በሚለው የዚህ ሪፖርት ክፍል ውስጥ በዝርዝር ቀርቧል።

ተፅዕኖ
114. በጦርነቱ ተሳታፊ የነበሩ ተዋጊ ኃይሎች በቁጥጥራቸው ስር በነበሩ አካባቢዎች በሲቪል ሰዎች ላይ በተለያዩ ምክንያቶች በፈጸሟቸው ግድያዎች ሳቢያ ከደረሰው የሕይወት መጥፋት በተጨማሪም በርካታ ቤተሰቦች ያለ አስተዳዳሪ፣ ጧሪ እና ደጋፊ እንዲቀሩ፤ ለከፍተኛ የሥነልቦና ጉዳትም እንዲዳረጉ ምክንያት ሆኗል።

መደምደሚያ
115. ጦርነቱ በተካሄደባቸው የአማራ እና አፋር ክልል አካባቢዎች በጦርነቱ ተሳታፊ በሆኑ ታጣቂ ኃይሎች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሲቪል ሰዎች ተገድለዋል፤ የአካል እና የሥነ ልቦና ጉዳት ደርሶባቸዋል። የትግራይ ኃይሎች በዋናነት ለግድያዎቹ ምክንያት ሲያደርጉ የነበረው “ለመንግሥት ኃይሎች ሰላይ ናችሁ፤ መሳሪያ አምጡ፣ ንብረት እንዳይወሰድ ተከላክላችኋል፤ በአካባቢያችሁ የመከላከያን፣ ልዩ ኃይልን ወይም ፋኖ ታጣዊዎችን አግዛችኋል ወይም የት እንዳሉ ታውቃላችሁ ወይም የነዚሁ አባላት ሆኑ ሰዎች ቤተሰብ ናችሁ” በሚል እንዲሁም አካባቢዎቹን በሚቆጣጣሩበት ወቅት በትግራይ ኃይሎች ላይ ለደረሰባቸው ጥቃት ወይም የትግራይ ታጣቂዎች እና ትግራይ ላይ ለደረሰ ሞት እና ጉዳት የበቀል/አጸፋ እርምጃ መሆኑን ጭምር በግልጽ እየተናገሩ ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆኑ ሲቪል ሰዎችን በጅምላ እና በነጠላ ገድለዋል። የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች በዋናነት በተቆጣጠሯቸው ስፍራዎች በነበሩ የመንግሥት አስተዳደር ኃላፊዎች እና ቤተሰቦቻቸው ላይ እንዲሁም መንግሥትን ይደግፋሉ ያሏቸው ሲቪል ሰዎች ላይ ያነጣጠረ ግድያን ፈጽመዋል። የመከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይል፣ ፋኖ እና ሚሊሺያዎችም የትግራይ ኃይሎች እና ኦነግ ሸኔ አባላት ናቸው ያሏቸው ወይም ድጋፍ አድርገዋል በሚል የጠረጠሯቸው ሰዎች ላይ ከፍርድ ውጪ ግድያዎችን ፈጽመዋል፤ የአካል ጉዳትም አድርሰዋል። በጦርነቱ ተሳታፊ በሆኑ ኃይሎች የተፈጸሙ ድርጊቶች በጦርነት ወቅት ሲቪል ሰዎችን ተጠቂ ወይም ዒላማ እንዳይሆኑ የመጠበቅ ግዴታን አስመልክቶ በዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ሕግም ሆነ በሰብአዊ መብቶች ሕግ እንዲሁም በኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ የተቀመጡ ክልከላዎችን በግልጽ የሚጥስ እና የጦር ወንጀል እንዲሁም በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል ሊሆን የሚችል ነው። 

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *