ከህግ አግባብ ውጪ የተፈጸመ እስር

ግንቦት 8 ቀን 2014 .ም ብርጋዴር ጄነራል ተፈራ ማሞ ከቤታቸው ከሰዎች ጋር ቀጠሮ አለኝ ብለው በወጡበት መታፈናቸውን እንዲሁም በዛው እለት ተንቀሳቃሽ ስልካቸው ላይ በተደጋጋሚ ቢደወልም ሊመልሱ አለመቻላቸውን፣ በማግስቱ ቤተሰቦቻቸው በተለያዩ ፖሊስ ጣቢያዎችና የደህንነት ጽ/ቤቶች ያሉበትን እንዲያሳውቋቸው ቢጠይቁም ሊያገኟቸው እንዳልቻሉና በመጨረሻም ወደ ባሕርዳር ከተማ ዘጠነኛ ፖሊስ ጣቢያ ተወስደው መታሰራቸውንና የባህርዳር ፖሊስ መምሪያ እና የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ፖሊስ ኮሚሽን ለባህርዳር ከተማ ዘጠነኛ ፖሊስ ጣቢያ በጻፉት ደብዳቤ በግንቦት 12 ቀን 2014 .ም በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ጠቅላይ ፍርድቤት መደበኛ ወንጀል ችሎት መቅረባቸውን እና ፍርድ ቤቱም ለግንቦት 22 ቀን 2014 .ም ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱን ኢሰመጉ ከብርጋዴር ጄነራል ተፈራ ማሞ ቤተሰቦች ካሰባሰበው መረጃ ለመረዳት ችሏል፡፡

አቶ ናፖሊዮን ገ/እየሱስ ገብሩ ግንቦት 1 ቀን 2014 .ም በአዲስ አበባ ከተማ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 ልዩ ስሙ ጀሞ ኮንደሚኒየም ከቀኑ 10 ሰዓት አካባቢ በታጠቁ ሁለት ሲቪሎች እና አራት ፖሊሶች ያለ ፍርድ ቤት ማዘዣ በመያዝ ወደ ለቡ አካባቢ የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት ጣቢያ ተወስዶ ታስሮ እንደነበር፣ ፖሊስ ጣቢያ ከገባበት ሰዓት ጀምሮ ቤተሰቡን እንዳያነጋግር ተከልክሎ እንደነበር፣ ከ02/09/2014 .ም ጀምሮ በነበረበት ፖሊስ ጣቢያ አለመኖሩ ለቤተሰቦቹ እንደተነገራቸው እና ወደ ሰበታ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ ተወስዷል የሚል መረጃ ደርሷቸው ወደ ተባለው ፖሊስ ጣቢያ ቢሄዱሙ የሰበታ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ አቶ ናፖሊዮን ወደ መጡበት ፖሊስ ጣቢያ እንደተመለሱ አንዳሳወቋቸው ነገር ግን መጀመሪያ ታስሮ የነበረበት ፖሊስ ጣቢያን ሄደው ቢጠይቁም ወደእዚህ አለመመለሱን እና ሌሎች ፖሊስ ጣቢያዎች እየዞሩ እንዲፈልጉ ለቤተሰቦች እንደተነገራቸው፣ ይህንንም ተከትሎ ቤተሰቦቹ አቶ ናፖሊዮንን በተለያዩ ፖሊስ ጣቢያዎች ቢያፈላልጉም ይህ ሪፖርት እስከወጣበት ቀን ድረስ ሊያገኙት እንዳልቻሉ እና በህይወት ይኑር አይኑር ማወቅ እንዳልቻሉ ለኢሰመጉ ገልጸዋል፡፡

ኢሰመጉ ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በደብዳቤ ቁጥር በቀን የአቶ ናፖሊዮን ገ/እየሱስ ገብሩን ሁኔታ እና ያለበትን ቦታ የሚያሳውቅ መረጃ እንዲሰጠው የጠየቀ ቢሆንም ይህ መግለጫ እስከወጣበት ቀን ድረስ ኮሚሽኑ ምንም አይነት መረጃ አልሰጠም፡፡ በተጨማሪም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተደጋጋሚ በተለያዩ ጋዜጠኞች ላይ እስራት እየተፈጸም ይገኛል። በአንዳንድ ጋዜጠኞች ላይ ሲፈጸሙ የነበሩ እስራቶች ተገቢውን የህግ ስነስርእት ያልተከተሉ እንዲሁም ከህግ አግባብ ውጪ የተፈጸሙ ሲሆን ከእነዚህም መካከል በጋዜጠኛ ታምራት ነገራ እና በጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ ላይ የተፈጸሙ እገታ እገታዎችን ኢሰመጉ በማውገዝ መንግስት አፋጣኝ የማስ ተካከያ እርምቶችን እንዲወስድ ሲወተውት ቆይቷል። ኢሰመጉ በዚህም ወቅት ጋዜጠኛ ሰለሞን ሹምዬ፣ በ አቶ ታዲዮስ ታንቱ፣ ቲና በላይ፣ አቶ አሸናፊ አካሉ እና መስከረም አበራ እና ሌሎችም መታሰራቸውን ካሰባሰባቸው መረጃዎች ለመረዳት ችሏል። እነዚህ በተደጋጋሚ እየተፈጸሙ ያሉ እስራቶች እያንሰራሩ የነበሩትን ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ፣ የንግግር ነጻነት እና የፕሬስ ነጻነት መብቶችን አላግባብ የሚገድብ እና አደጋ ላይ የሚጥል መሆኑን ኢሰመጉ ያምናል።

ኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት፡

በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በተደጋጋሚ ጊዜ በሸኔ ታጣቂዎች እና በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች በሚወሰዱ እርምጃዎች በበርካታ ንጹሀን ዜጎች ላይ ሞት፣ የአካል ጉዳት፣ የንብረት ውድመት፣ ዝርፊያ እና መፈናቀል ሲደርስ ቆይቷል፡፡ ኢሰመጉ ባሰባሰባቸው መረጃዎች መሰረት እነዚህ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች በሁለቱም አካላት የተፈጸሙ መሆናቸውን ኢሰመጉ ለመረዳት ችሏል፡፡

ደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል፡

በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል በኮንሶ ዞን፣ በደራሼ ልዩ ወረዳ፣ ሰገን ዙሪያ ወረዳ ባሉ ቀበሌዎች እና በአሌ ልዩ ወረዳከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተፈጠሩ ባሉ ግጭቶች በርካታ ንጹሀን ዜጎች ላይ ሞት፣ የአካል ጉዳት፣ ንብረት ውድመት እና ዘረፋ እንዲሁም በሐይማኖት ቦታዎች ላይ ዝርፊያዎች እና የንብረት ውድመት እየተፈጸመ ይገኛል፡፡ ይህንን አስመልክቶ ኢሰመጉ በተደጋጋሚ ሲያወጣቸው በነበሩ መግለጫዎች የሚመለከተው የመንግስት አካል ማስተካከያዎችን እንዲያደርግ ሲወተውት የቆየ ቢሆንም ችግሮቹ ከጊዜ ወደጊዜ እየተባባሱ መጥተዋል፡፡ በተጨማሪም በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል አማሮ ልዩ ወረዳ በተደጋጋሚ ጊዜ በርካታ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች በታጣቂ ሀይሎች ሲፈጸሙ የቆዩ ሲሆን አሁንም ከኦሮሚያ ክልል ምዕራቢ ጉጂ ዞን ጋላና ወረዳ በሚነሱ ታጠቂዎች በአካባቢው ከግንቦት 2 ቀን 2014 .ም ጀምሮ በደረሰ ጥቃት ሞት(ሁለት ህጻናትን ጨምሮ)፣ የአካል ጉዳት፣ ንብረት ውድመት እና ዘረፋ መፈጸሙን ኢሰመጉ ካሰባሰባቸው መረጃዎች ለመረዳት ቸሏል፡፡

ሀገራዊ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች፡

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የኑሮ ውድነት በሰዎች ኑሮ ላይ ከፍተኛ የሆነ ተጽዕኖ እየፈጠረ ይገኛል፡፡ መሰረታዊ የሆኑ የምግብ አቅርቦቶች ዋጋ በየዕለቱ እየጨመረ መምጣቱ እንዲሁም በቤት ኪራይ ላይ እየተስተዋለ ባለው ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ጭማሪ ምክንያት ዜጎች ካላቸው ገቢ አንጻር የኑሮ ውድነቱን መቋቋም ባለመቻላቸው ለከፋ ሰብዓዊ ጉዳት ተዳርገዋል፡፡ በአዲስ አበባና በሃገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የትራንስፖርት ችግር በከፍተኛ ሁኔታ ህብረተሰቡ ላይ ችግር እየፈጠረ እንደሆነ እና ነዳጅ ጨምሯል በሚል ከታሪፍ ውጪ የትራንስፖርት ተጠቃሚው ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ እየተደረገ እንደሚገኝ ኢሰመጉ ካሰባሰባቸው መረጃዎች ለመረዳት ችሏል፡፡ 

ተያያዥ የህግ ግዴታዎች፡

የሰብዓዊ መብቶች ዓለም አቀፍ መግለጫ(UDHR) እና የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃልኪዳን(ICCPR) ሁለቱም ስምምነቶች በአንቀጽ 9 ላይ ማንም ሰው በዘፈቀደ ሊያዝ እንደማይችል፣ ማንም ሰው ከህግ ውጪ እንደማይያዝ፣ እንደማይታሰር እና የግል ነጻነቱን እንደማያጣ ይደነግጋሉ፡፡ የአፍሪካ ቻርተር በሰዎች እና ህዝቦች መብቶች ስምምነት አንቀጽ 6 ላይ በተመሳሳይ ማንም ሰው የነጻነትና የአካል ደህንነት መብት እንዳለው ይህንንም መብት ከህግ አግባብ ውጪ እንደማያጣ እና ማንም ሰው በዘፈቀደ ሊታሰር እንደማይገባ ይደነግጋል፡፡ የኢ...ሪ ህገመንግስትም እንዲሁ በአንቀጽ 17 ላይ የነጻነት መብትን ሲያብራራ ማንኛውም ሰው በህግ ከተደነገገው ስርዓት ውጪ ሊያዝ፣ ክስ ሳይቀርብበት ወይም ሳይፈረድበት ሊታሰር አይችልም ሲል ይደነግጋል፡፡ የኢ...ሪ ህገመንግስት በአንቀጽ 28 ላይ በስብእና ላይ ስለሚፈጸሙ ወንጀሎች ሲያብራራ በአስገዳጅ ሰውን መሰወር በስብዕና ላይ የሚፈጸም ወንጀል መሆኑን እውቅና ይሰጣል፡፡

ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ባታጸድቀውም ሰዎችን አስገድዶ ከመሰወር ለመጠበቅ የወጣው ዓለም አቀፍ ስምምነት(International Convention for the Protection of All Persons from Enforced Disappearance ) በአንቀጽ 5 ላይ በስፋት ወይም ስልታዊ በሆነ መንገድ የሚፈጸም አስገድዶ መሰወር በዓለም አቀፍ ህጎች ትርጉም በተሰጠው መሰረት በስብዕና ላይ የሚፈጸም ወንጀል መሆኑን ይደነግጋል፡፡ በተጨማሪም ይኸው ስምምነት በአንቀጽ 1(1) ላይ ማንም ሰው ለአስገድዶ መሰወር ተጋላጭ መሆን እንደሌለበት በመደንገግ ይህንን ወንጀል የፈጸሙ አካላትን መንግስት በወንጀል ተጠያቂ እንዲያደርጋቸው ይደነግጋል፡፡

ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች መግለጫ (UDHR) አንቀጽ 3፣ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃልኪዳንም (ICCPR) በአንቀጽ 6(1) እና 9(1) ላይ እያንዳንዱ ሰው በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደህንነቱ የመጠበቅ መብት እንዳለው ያረጋግጣል። ይህንኑ መብት በማረጋገጥ፣ መንግሥታት በቃልኪዳኑ(ICPR) የተረጋገጡትን መብቶች በግዛታቸው የማክበር፣ የማስከበርና የማሟላት ግዴታ እንዳለባቸውም በአንቀጽ 2(1) እና 2(2) ይደነግጋል። የአፍሪካ ቻርተር በሰዎች እና ህዝቦች መብቶች (ACHPR) አንቀጽ 4 ማንኛውም ግለሰብ በሕይወት የመኖር መብቱና የአካሉ ደህንነት ሊከበርለትና ሊጠበቅለት እንደሚገባና እነዚህን መብቶቹን በዘፈቀደ ሊነፈግ እንደማይችል ተመላክቷል። የኢ...ሪ ሕገመንግሥት አንቀጽ 14 “ማንኛውም ሰው ሰብዓዊ በመሆኑ የማይደፈርና የማይገሰስ በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደህንነትና የነጻነት መብት አለውሲል ይደነግጋል።በተመሳሳይ የኢ...ሪ ሕገመንግስት አንቀፅ 15 ማንኛውም ሰው በሕይወት የመኖር መብት እንዳለውና በሕግ ከተደነገገው ውጪ ሕይወቱን ሊያጣ እንደማይችል በግልፅ ደንግጓል፡፡

ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች መግለጫ(UDHR) አንቀጽ 17 ማንኛውም ሰው ብቻውንም ሆነ ከሌሎች ጋር በመተባበር የንብረት ባለቤት የመሆን መብት እንዳለውና ማንም ሰው በዘፈቀደ ንብረቱን እንዲያጣ እንደማይደረግ ያረጋግጣል፡፡ የአፍሪካ ቻርተር በሰዎች እና ህዝቦች መብቶች(ACHPR) በአንቀጽ 14 ላይ የንብረት ባለቤትነት መብት እንደሚረጋገጥ እና ሊጣስ የሚችለው ለህዝብ ፍላጎት ወይም ለህብረተሰቡ አጠቃላይ ጥቅም እና አግባብ ባላቸው ህጎች በተደነገገው መሰረት ብቻ እንደሆነ ይደነግጋል፡፡ ይኸው ቻርተር በአንቀጽ 1 ላይ በዚህ ቻርተር ውስጥ የተካተቱት ሀገሮች በቻርተሩ ውስጥ የተካተቱትን መብቶች፣ ተግባሮች እና ነፃነቶች ተገንዝበው ተግባራዊ ለማድረግ የሕግ አውጭ ወይም ሌሎች እርምጃዎችን መውሰድ እንዳለባቸው ይደነግጋል፡፡ የኢ...ሪ ሕገመንግሥት በአንቀጽ 40 ሥር ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የግል ንብረት ባለቤት መሆኑ እንደሚከበርለት ይደነግጋል፡፡ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች መግለጫ(UDHR) አንቀጽ 25 ላይ ማንም ሰው ለራሱና ለቤተሰቡ ጤንነትና ደህንነት በቂ በሚሆን የኑሮ ደረጃ የመኖር መብት አለው፤ ይህም ምግብን፣ ልብስን፣ መጠለያን፣ የሀክምና አገልግሎትን፣ አስፈላጊ የሆኑ የማህበራዊ አገልግሎቶችን የማግኘት መብት አለው ሲል ይደነግጋል፡፡ በተመሳሳይ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና የባህላዊ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃል ኪዳን (ICESCR) በአንቀጽ 11 ላይ ተመሳሳይ መብትን ከማስቀመጥ በተጫማሪ መንግስታት ይህንን መብት ሙሉ ለሙሉ በስራ ለመተርጎም ተገቢውን እርምጃ ይወስዳሉ ሲል ይደነግጋል፡፡

የኢሰመጉ ጥሪ፡

ኢሰመጉ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተበራከተ የመጣውን በመንግስት አካላት የሚፈጸም አስገድዶ የመሰወር ድርጊት እያወገዘ፤

  • የፌደራል እና የሚመለከታቸው የክልል መንግስታት ከጊዜ ወደጊዜ አየጨመረ የመጣውን በመንግስት የጸጥታ አካላት ሰዎችን አስገድዶ የመሰወር ድርጊት በአስቸኳይ አንዲያስቆሙ እና ይህንን ህገ ወጥ ድርጊት ፈጻሚዎችን ለህግ እንዲያቀርቡ፣
  • ብርጋዴር ጄነራል ተፈራ ማሞን በሚመለከት በህግ አግባብ ተገቢውን የፍትህ ስርአት በመከተል ፈጣን ፍትህ እንዲሰጣቸው እና መንግስት ያላቸውን መብቶች እንዲያከብር እና እንዲያስከብር፣
  • አቶ ናፖሊዮን ገ/እየሱስ ገብሩ ያለበትን ይፋ በማድረግ ተገቢውን የህግ ስነስርዓት በተከተለ መልኩ ፍርድ ቤት እንዲያቀርብ እና ይህንን እገታ የፈጸሙ የፖሊስ አካላት እና አመራሮችን ተጠያቂ እንዲያደርግ፣
  • በጋዜጠኞች፣ በማህበረሰብ አንቂዎች እና ተፅዕኖ ፈጣሪ በሆኑ ሰዎች ላይ እየተፈጸሙ ያሉ እስሮች ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ፣ የንግግር ነጻነት እና የፕሬስ ነጻነት መብቶችን አላግባብ የሚገድብ እና አደጋ ላይ የሚጥል እንቅስቃሴ በመሆኑ ከዚህ ድርጊት እንዲቆጠብ እና በእስር ላይ ያሉትንም ያሏቸውን መብቶች በማክበር አፋጣኝ ፍትህ እንዲሰጥ፣
  • በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በመንግስት የጸጥታ አካላት እና በሸኔ የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች በአስቸኳይ እንዲቆሙ እና ጥሰት ፈጻሚዎቹ ለህግ እንዲያቀርቡ፣
  •  የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት አንዳንድ አካባቢዎች ያሉ የጸጥታ ስጋቶችን በቂ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ሰላምን እንዲያረጋግጥ፣
  •  የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል መንግስት በኮንሶ ዞን፣ በደራሼ ልዩ ወረዳ፣ ሰገን ዙሪያ ወረዳ ባሉ ቀበሌዎች ፣ በአሌ ልዩ ወረዳእና በአማሮ ልዩ ወረዳ በተደጋጋሚ ጊዜ እየተፈጸሙ ያሉ መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶቸን በአስቸኳይ በቂ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ዘላቂ የሆነ መፍትሄን እንዲሰጥ፣
  • በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል በኮንሶ ዞን፣ በደራሼ ልዩ ወረዳ፣ ሰገን ዙሪያ ወረዳ ባሉ ቀበሌዎች ፣ በአሌ ልዩ ወረዳእና በአማሮ ልዩ ወረዳ በተደጋጋሚ ጊዜ እየተፈጸሙ ያሉ መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶቸ ላይ እጃቸው ያለበትን አካላት በአፋጣኝ ለህግ እንዲያቀርብ፣
  • በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል አማሮ ልዩ ወረዳ በታጣቂዎች በተደጋጋሚ የሚፈጸመውን ጥቃት ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ዘላቂ መፍትሄ እንዲያበጅ እና ጥቃት አድራሾችን ለፍርድ እንዲያቀርብ፣
  • መንግስት ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ የመጣውን የኑሮ ውድነት በቂ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት እና ዘላቂ የመፍትሄ መንገዶችን በማበጀት ዘላቂ መፍትሄን እንዲያቀርብ፣
  • በህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎቶች ላይ ከታሪፍ ውጪ ጭማሪ በሚያደርጉ አካላት ላይ በቂ ቁጥጥር እንዲደረግ እና በህግ አግባብ ተጠያቂ እንዲያደርግ፣
  • መንግስት፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የማሕበረሰብ አንቂዎች፣ ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆኑ ግለሰቦች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሲቪክ ማህበራት፣ ሕብረተሰቡ በአጠቃላይ እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ በሀገራችን ኢትዮጵያ ለዘመናት የኖረውን የመቻቻል የመከባበር እና አብሮ የመኖር ባህልን በመዘንጋት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተነሱ ያሉ ግጭቶች እና እየደረሱ ያሉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን በመፍታት ረገድ የበኩላቸውን እንዲወጡ እና መሰል ችግሮች ወደፊት እንደዳይፈጠሩ አስቀድሞ በመከላከሉ ላይ ምትክ የሌለውን ሰፊ ድርሻቸውን በአግባቡ እንዲወጡ እንዲሁም በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ያለውን የጸጥታ ችግር በሰላምና በእርቅ የሚፈታበትንና የዜጎች ሰብዓዊ መብቶች የሚጠበቁበትን ሁኔታ እንዲያመቻቹ ኢሰመጉ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *