በአማራ ክልል የሚገኙ 10 ዩኒቨርሲቲዎች የትግራይ ኃይሎች ወደ አማራ ክልል ገብተው በቆዩባቸው ወራት አደረሱት ያሉትን የጥናት ውጤት ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ ይፋ አድርገዋል።
ሪፖርቱ የትግራይ ኃይሎች የክልሉን የተወሰኑ አካባቢዎች ተቆጣጥረው በነበሩበት ወቅት ወደ 7000 የሚጠጉ ሰላማዊ ሰዎችን ገድለዋል ይላል። የህወሓት ወታደሮች ካለፈው ዓመት ሰኔ ወር መጨረሻ ጀምሮ ወደ አማራ ክልል መግባት የጀመሩ ሲሆን ሰባት ዞኖችን ተቆጣጥረው ቆይተዋል። ሰሜን ጎንደር፣ ደቡብ ጎንደር፣ ዋግ ኽምራ፣ ሰሜን ወሎ፣ ደቡብ ወሎ፣ ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር እና ሰሜን ሸዋ የህወሓት ወታደሮች ተቆጣጥረዋቸው የነበሩ አካባቢዎች ናቸው። ይህ ከአስር ዩኒቨርስቲዎች በተውጣጡ ባለሙያዎች የተሰራው ጥናት በዚህ ሳምንት መጨረሻ ላይ ይፋ የተደረገ ሲሆን ለማጠናቀቅም አምስት ወር መፍጀቱ ተገልጿል።
የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ሁለቱም ተዋጊ ኃይሎች ሰላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃት መሰንዘራቸውን፣ ከሕግ አግባብ ውጪ ሰዎች መገደላቸውን እና መድፈርን ጨምሮ የተለያዩ የጾታዊ ጥቃት አድርሰዋል ሲሉ ይወነጅሏቸዋል። የህወሓት ቃል አቀባይ የሆኑት ጌታቸው ረዳ ሪፖርቱን በተመለከተ ለብሎምበርግ የሚዲያ ተቋም በሰጡት ምላሽ “ፈጠራ” ሲሉ አጣጥለውታል። አቶ ጌታቸው ረዳ “በአማራ ክልል ሰላማዊ ዜጎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት አልሰነዘርንም” ሲሉ ለብሉምበርግ ምላሻቸውን ሰጥተዋል።
ጥናቱ ምን ይፋ አደረገ?
ከጥናቱ አስተባባሪዎች አንዱ የሆኑት የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንትና በክልሉ የሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ሰብሳቢ ታፈረ መላኩ (ዶ/ር) ጥናቱ የተከናወነው ከህወሓት ተዋጊዎች ነጻ በወጡ አካባቢዎች ብቻ ላይ የተወሰነ መሆኑን ለቢቢሲ ገልጸዋል። ይህ በአማራ ክልል በሚገኙ 10 ዩኒቨርስቲዎች ጥምረት ይፋ የሆነው ጥናት 6 ሺህ 985 ንፁሃን ዜጎች በጦርነቱ ምንም ዓይነት ተሳትፎ ሳይኖራቸው በህወሓት ኃይሎች ተገድለዋል ሲል ያትታል። 7 ሺህ 460 ዜጎች ደግሞ በኃይል ታፍነው በመወሰዳቸው የት እንዳሉ አድራሻቸው አለመታወቁን ጠቅሷል።
1 ሺህ 797 የሚሆኑት ደግሞ በጅምላ ተጨፍጭፈዋል የሚለው ይህ ጥናት፣ በተለይ በጭና፣ ቀወት፣ መንዝ ጌራ፣ አንጾኪያ ገምዛ፣ አጋምሳ፣ ኮምቦልቻ፣ እና መርሳ የተፈፀሙት “የጅምላ ግድያዎችን” በአብነት ጠቅሷል። ከእነዚህ መካከል 579 የሚሆኑት ዜጎች ደግሞ በድብደባ ብዛት የሞቱ መሆናቸውን በጥናቱ ተመልክቷል። የህወሓት ኃይሎች በአማራ ክልል ጭና እና ቆቦ በተባሉ አካባቢዎች በርካታ ንጹሃን ሰዎችን በጅምላ መግደላቸውን የሰብዓዊ መብት ድርጅቱ ሂዩማን ራይትስ ዋች ማስታወቁ ይታወሳል። በትግራይ ክልል ውስጥ ተቀስቅሶ ወደ አማራና አፋር ክልሎች ተስፋፍቶ በነበረው ጦርነት ውስጥ ከባድ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት እንደደረሰ ከተለያዩ ወገኖች የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ።

ጦርነቱ ከትግራይ ክልል ወጥቶ ወደ አማራ ክልል ከተስፋፋ በኋላ ‘ዘ ቴሌግራፍ’ የተባለው ጋዜጣ አማጺያን በሐምሌ ወር 2013 ዓ.ም መጨረሻ ላይ አማራ ክልል ውስጥ ቆቦ ውስጥ አጋምሳ በሚባለው አካባቢ በአንድ ቀበሌ ላይ በፈጸሙት የጅምላ ጥቃት ከባድ ጉዳት መድረሱን ዘግቦ ነበር። ጋዜጣው እንዳለው በጥቃቱ የከባድ መሳሪያ ድብደባ መፈጸሙንና በርካታ መኖሪያ ቤቶችም ሆን ተብለው በእሳት እንዲቃጠሉ መደረጋቸውን ዘግቧል። ዘገባውን ተከትሎ ህወሓት ጥቃቱን አለመፈፀሙን ያስተባበለ ሲሆን በአካባቢው በሰላማዊ ሰዎች ላይ ተፈጽመዋል በተባሉ ጥቃቶች ዙሪያ ገለልተኛ ማጣራት እንዲደረግ ጠይቆ ነበር።
ቢቢሲ ስለ ክስተቱ ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት ጥረት አድርጎ በጥቃቱ ወቅት በስፍራው የነበሩ እንዲሁም ጉዳት ደርሶባቸው በህክምና ላይ የሚገኙ ነዋሪዎችን በማነጋገር የደረሰውን ማረጋገጥ ችሏል። በአማራ ክልል የሚገኙ አስር ዩኒቨርሲቲዎች በሰሩት በዚህ ጥናት ላይ የትግራይ ኃይሎች ወደ አማራ ክልል ገብተው በቆዩባቸው ወራት በአጠቃላይ ከ10 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ሰብዓዊ ጉዳት እንደደረሰባቸው ጠቅሰዋል። ከ240 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ በተለያየ መንገድ የሰብዓዊ ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑን ያመለክታል።
ጦርነቱ ካደረሳቸዉ አስከፊ የሰብዓዊ ጉዳቶች መካከል አስገድዶ መድፈር አንዱና ዋነኛው እንደሆነ ጥናቱ አመላክቷል። የተለያዩ አገር በቀል እና ዓለም አቀፍ ተቋማትም በሁለቱም ወገኖች አስገድዶ መድፈር መፈጸሙን ሪፖርት አድርገዋል። ይህ ጥናት እንደሚያሳየው ደግሞ በእነዚህ 7 ዞኖች ውስጥ ብቻ የህወሓት ተዋጊዎች በቆዩባቸው ወራት 1 ሺህ 782 ሴቶች የአስገድዶ መድፈር ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል ይላል። ጥቃቱም በቡድን፣ በትዳር አጋር እና በቤተሰብ አባላት ፊት፤ የሃይማኖት አባቶች ሚስቶችን ጨምሮ የተፈጸመ ነው ተብሏል። የአስገድዶ መድፈር ጥቃት ከተፈጸመባቸው መካከል 22 የሚሆኑት ወንዶች ናቸው ብሏል ጥናቱ።
ዶ/ር ታፈረ እንደሚሉት ይህ ጥናት ሲካሄድ አንዱ መስፈርት የነበረው ጥናቱ ሥነ ምግባር በተሞላበት አግባብ እንዲከናወን ማድረግ ነው። በመሆኑም አስገድዶ መደፈር የተፈጸመባቸው ሴቶች መገለል እና መድሎን በመፍራት መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆኑትን አላካተተም። ከእዚህ አንጻር ጥናቱ ፈቃደኞችን ብቻ ያካተተ በመሆኑ ቁጥሩ ሊጨምር ይችላል ብለዋል።

ጥናቱ እንዴት ተሰራ?
የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንትና በክልሉ የሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ሰብሳቢ ታፈረ መላኩ (ዶ/ር) በአማራ ክልል ከሚገኙ አስር የፌደራል ዩኒቨርሲቲዎች የተወጣጡ ከ4 ሺህ በላይ ባለሙያዎች መሳተፋቸውን ገልፀዋል። ከእዚህም በተጨማሪ ከስታቲክስ ኤጀንሲ የተወጣጡ 300 የሚጠጉ ሙያተኞች መሳተፋቸውንም ፕሬዝዳንቱ ለቢቢሲ ጠቅሰዋል። ይህንን ጥናት ለማከናወን ከተካተቱት 10 የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውጪ የፌደራልም ሆነ የክልል መንግሥታት ተሳትፎም ሆነ ፖለቲካዊ ጫና የለበትም ይላሉ ዶ/ር ታፈረ።
ጥናቱ በዋናነት የቤት ለቤት እና የተቋማት ሙሉ ቆጠራ (Census) ሥነ-ዘዴን የተጠቀመ ሲሆን፤ የሰብአዊ እና ሥነ ልቦናዊ ጉዳቶችን በተመለከተ ጥልቅ መረጃ ለማግኘት ደግሞ የቡድን ውይይት፣ ጥልቅ ቃለ-መጠየቅ፣ የመስክ ምልከታ እንዲሁም ፎቶ እና ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ተጠቅሟል ብለዋል ዶ/ር ታፈረ። እንደ ሩዋንዳ ያሉ አገራትን ተሞክሮ መነሻ በማድረግ ሳይንሳዊና ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያለው ጥናት ለማድረግ መስራታቸውን ዶ/ር ታፈረ ተናግረዋል። የጥናት ሰነዱ እንደሚለው በከተሞች የሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳት ከደረሰባቸዉ 429 ሺህ 443 ግለሰቦች መካከል የሥነ ልቦና ቀውስ ያለባቸዉ ስለመሆኑ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት መልስ መሰረት 73.6 በመቶ ያህሉ አንድ እና ከዚያ በላይ ለሆኑ ተደራራቢ የሥነ-ልቦና ችግሮች ተጋልጠዋል።
በቀበሌ ደረጃ የሚገኙ የመንግሥት ሠራተኞችና ሙያተኞች ቤቶችን እና ቦታዎችን በማሳየት ብቻ ለጥናቱ አስተዋጽኦ ማድረጋቸው ተገልጿል። ቁሳዊ ውድመትን በተመለከተ የህወሓት ወታደሮች በቤተሰብ ጥሪት፣ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት፣ የግል ድርጅቶች እንዲሁም የመሰረተ-ልማት አውታሮች ላይ መጠነ ሰፊ ጉዳት አድርሰዋል ሲል ጥናቱ አስቀምጧል። ይህ ውድመትም በጥቅሉ በገንዘብ ሲተመን ከ288 ቢሊዮን ብር በላይ መሆኑ ተገልጿል። ጥናቱ የህወሓት ተዋጊዎች በማኅበራዊ ፍትህ ተቋማት ላይም ከፍተኛ ጉዳት ማድረሳቸውን ጠቅሶ፣ በእዚህም መሰረት 1 ሺህ 145 የትምህርት ተቋማት እና 2 ሺህ የሚጠጉ የጤና ተቋማት ጉዳት እንደደረሰባቸውም አመልክቷል።
በጥናቱ የክልሉ በዋናነት ሃብት የሆኑ ሁሉም የመንግሥትና የግል ተቋማት የተካተቱ ሲሆን የግለሰቦች ጥሪትና ሃብቶችም የጥናቱ አካል መሆናቸው ተገልጿል። ከእነዚህ መካከልም ከ50 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመተው ንብረት የግለሰቦች ሃብት መሆኑን ጥናቱ ገልጿል። የፌደራል ተቋማት በከፊል የተካተቱ ሲሆን የፋይናንስ ተቋማት፤ ደረቅ ወደብ፤ የባቡር መስመር፣ የአየር ትራምስፖርት እና መሰል ተቋማት ውድመት በጥናቱ አልተካተቱም ተብሏል።