የኤርትራ መንግሥት ህወሓት ለዳግም ጦርነት በዝግጅት ላይ እንደሆነ በመግለጽ እራሷን ለመከላከል አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ መሆኗን ገለጸች።
የኤርትራ መንግሥት በማስታወቂያ ሚኒስቴሩ በኩል ዛሬ ግንቦት 09/2104 ዓ.ም. ባሰፈረው መልዕክት ህወሓት በኤርትራ ድንበር በኩል እና በምዕራብ ትግራይ አቅጣጫ በሁለት ግንባሮች ጦርነት ለመክፈት እየተዘጋጀ ነው ብሏል። ጨምሮም በዚህ በህወሓት ሊሰነዘር ይችላል ላለው ጥቃት የመጀመሪያው ዒላማ “ኤርትራ እና የኤርትራ ሕዝብ ናቸው” ሲል አቋሙን አንጸባርቋል። ከወራት በፊት ከተደረገው ከባድ ውጊያ በኋላ ጋብ ብሎ የቆየው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ዳግም ሊያገረሽ ይችላል የሚል ስጋት እየጨመረ በመጣበት ጊዜ ነው የኤርትራ መንግሥት ይህንን ያለው።
ከቀናት በፊት የአማራ ክልል ከህወሓት በኩል ሊሰነዘር ይችላል ላለው ሌላ ዙር ወረራ የክልሉ የፀጥታ መዋቅር ዝግጁ እንዲሆን ትዕዛዝ አስተላልፎ ነበር። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በበኩሉ በሰሜን ኢትዮጵያ በትግራይ ኃይሎች እና በፌደራል መንግሥት ኃይሎች መካከል ውጥረት እየጨመረ መምጣቱ እንዲሁም አልፎ አልፎም ግጭቶች ሪፖርት መደረጋቸው እንዳሳሰበው ገልጾ ነበር። እያየለ ከመጣው የዳግም ጦርነት ስጋት በተጨማሪ ባለፈው ሳምንት የትግራይ ኃይሎች ከኤርትራ ድንበር አቅራቢያ ለጥቂት ሰዓታት የቆየ ጥቃት ሰንዝረው የከባድ መሳሪያ ተኩስ ልውውጥ እንደነበረ ቢቢሲ መዘገቡ ይታወሳል።
ዛሬ በኤርትራ መንግሥት የማስታወቂያ ሚኒስቴር ድረ-ገጽ ላይ የወጣው ጽሑፍ ላይ ግን ሚያዚያ 30/2014 ዓ.ም. ራማ እና ባድመ አካባቢ ከህወሓት ኃይሎች ጋር ግጭት አጋጥሞ ነበር ስለመባሉ ያለው ነገር የለም። የኤርትራ መንግሥት ባስተላለፈው መልዕክት በዓለም አቀፍ ሕግ የኤርትራ ሉዓላዊ ግዛት እንደሆነ ያረጋገጠወን አካባቢ ህወሓት ዳግም ለመውረር በዝግጅት ይገኛል ሲል ከሷል። ከዚህ በተጨማሪም፤ ህወሓት ሊከፍት ነው ላለው አዲስ ጥቃት በምዕራብ ወልቃይት፣ ጸገዴ እና ሑመራን መልሶ በመቆጣጠር ከሱዳን ጋር የሚያዋስነውን ድንበር ለመክፈት አቅዷል ብሏል።
በመጨረሻም ከህወሓት ሊሰነዘር የሚችልን ጥቃት የኤርትራ ሕዝብ እና መንግሥት እራሱን መከላከል ይችላል በማለት ዝግጁ መሆኑን ገልጿል። ለዚህ ከኤርትራ መንግሥት በኩል በይፋ ለቀረበው ወረራ ለመፈጸም የመዘጋጀት ክስ ከህወሓት በኩል አስካሁን የተባለ ነገር የለም። የፌደራል መንግሥት ኃይሎች፣ የክልል ልዩ ኃይሎች እና የኤርትራ ጦር በአንድ ወገን ሆነው ከትግራይ ኃይሎች ጋር ለ17 ወራት የዘለቀ ደም አፋሳሽ ጦርነት አድርገዋል። ይህ ጦርነት ከፍተኛ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ኪሳራ አድርሷል። በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ በጦርነቱ ምክንያት ሳይሞቱ እንደማይቀር ይገመታል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ከቀያቸው ተፈናቅለዋል። በሕዝብ ንብረት ላይም ከፍተኛ ጉዳት ድርሷል።
የጦርነቱ ተሳታፊዎች ልዩነቶቻቸውን በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲፈቱ የአፍሪካ ሕብረት እና ምዕራባውያን ለወራት የዘለቀ ጥረት ሲያደርጉ የቆዩ ቢሆንም አስካሁን ይህ ነው የሚባል ውጤት አላስገኘም። ከጥቂት ወራት በፊት የፌደራል መንግሥቱ እና የትግራይ ኃይሎች በትግራይ የሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ ያስችል ዘንድ ለሰብዓዊነት ሲባል የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ ላይ ደርሰው ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ለሰብዓዊነት ሲባል የተኩስ አቁም ውሳኔ፤ የተፈለገውን ያክል የሰብዓዊ እርዳታ ወደ ክልሉ ማድረስ አልቻለም። እንዲሁም ተዋጊ ኃይሎችን ወደ ድርድር ማምጣት አልቻለም።
የህወሓት ሊቀመንበር ደብረፂዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) ባለፈው ሳምንት ለዓለም አቀፍ ተቋማት በጻፉት ይፋዊ ደብዳቤ ላይ በሰሜን ኢትዮጵያ ላለው ጦርነት አስቸኳይ መፍትሔ በማፈላለግ እንዲያግዙ እና በትግራይ ላይ ተጥሏል ያሉት ከበባ እንዲያበቃ ካልተደረገ “ሌላ አማራጭ” ለመፈለግ እንደሚገደዱ ገልፀው ነበር። ነገር ግን ይህ “አማራጭ” ያሉት ምን እንደሆነ በደብዳቤው ላይ አልተብራራም። ከአንድ ዓመት ተኩል በላይ ባስቆጠረው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ውስጥ የኤርትራ ሠራዊት ተሳታፊ የነበረ ሲሆን፣ በጦርነቱ ጅማሬ ወቅት የህወሓት ኃይሎች ተደጋጋሚ የሮኬት ጥቃቶችን በኤርትራ ላይ መፈጸማቸው ይታወሳል።